አዲስ አበባ፡- ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ በድህረ ምረቃ ያሠለጠናቸውን 410 ተማሪዎችን አስመረቀ።
በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ የእንኳን ደስ አላችሁ ንግግር ያደረጉት የኮሌጁ ፕሮቮስት ዶክተር ሲሳይ ስርጉ እንዳሉት፤ ኮሌጁ ለ11 ጊዜ የምረቃ ሥነሥርዓት አካሂዷል። ሁሉም ተመራቂዎችም የድህረት ምረቃ ተማሪዎች ናቸው። ከህክምና ትምህርት ቤት ሶስት መቶ ተመራቂዎች፣ ሁለት መቶ ሃያ በስፔሻሊቲ ሥልጠና፣ 36 ተማሪዎች በ11 ሰብ ስፔሻሊስት ስልጠና፣ 14 ተማሪዎች በሁለት የሁለተኛ ዲግሪ ሥልጠና መስክ ሠልጥነው መመረቅ ችለዋል።
እንዲሁም ከህብረተሰብ ትምህርት ቤት 58 ተመራቂዎች በአራት የትምህርት ዘርፎች ተመርቀዋል። እንዲሁም ከነርሲንግ ትምህርት ክፍል 52 ተመራቂዎች በስድስት የትምህርት መስክ የተመረቁ ሲሆን በአጠቃላይ 410 ተመራቂዎች በ43 የተለያዩ የትምህርት መስኮች መመረቃቸውን ጠቅሰዋል።
እንደ ዶክተር ሲሳይ ገለጻ፣ የተመራቂዎች የትምህርት መስክ ስብጥር እንደሚያሳየው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ህክምና ኮሌጅ ጤና ሚኒስቴር ያወጣውን ስፔሻሊቲና ሰብ ስፔሳሊቲ ፍኖተ ካርታ መሠረት ያደረገ ሥልጠና ነው። ይህም የህክምና ዘርፉን ለማዘመን፣ ለማሳደግ፣ ጥራቱ የጠበቀና ተደራሽ ለማድረግ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በኮሌጁ ስር በሚገኙ ሆስፒታሎችና ከኮሌጁ ጋር በጋራ በሚሠሩ ሆስፒታሎች ላይ የተግባር ልምምድ አድርገዋል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱ ወረርሽኞችን የቅኝትና ምላሽ መስጠት ላይ በመሳተፍ የተግባር ልምድ እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ሥራ ሲሰማሩ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ይችላሉ ያሉት ዶክተር ሲሳይ፣ በተደረጉ የማህበረሰብ አገልግሎቶች በመሳተፍ ትልቅ ሥራ ሠርተዋል። እንዲሁም በሀገሪቱ በተከሰቱ ሰው ሠራሽ ችግሮች፣ ድንገተኛ አደጋዎችና የወረርሽኝ ምላሽ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን በመግለጽ፣ ምስጋና አቅርበዋል።
እንደ ፕሮቮስት ዶክተር ሲሳይ ማብራሪያ፣ ኮሌጁ የትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ለማስፋፋት ባደረገው ጥረት በአሁኑ ጊዜ በ73 የቅድመ መደበኛና የድህረ ምረቅት ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል። የትምህርት መስኮችን ከማስፋፋት በተጨማሪ የሥልጠናዎች ተግባር ተኮር ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል።
አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶችን ለማስፋፋት፣ የነበሩትን ደረጃቸውንና ጥራታቸውን በማሻሻል በተለይም የነርሲንግ ሥልጠናዎችን ወደ ሪዚደንሲ የሥልጠና ስልት በመቀየር ውጤታማ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል ።
የክህምና ትምህርት ቤትን ዓለም አቀፍ እውቅና ለማሰጠት የሚያስችል ማመልከቻ ለማስገባት የመጨረሻ ዝግጅቱ ተጠናቋል። ግንባታቸው ተጠናቆ በቅርቡ ወደ አገልግሎት ለመግባት በዝግጅት ላይ የሚገኙት የካንሰር ፣ የልብ፣ የአንጀትና የጉበት የህክምና ማእከሎች ከሚሰጡት ከፍ ያለ አገልግሎት እንዲሰጡ ብቁ ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ዶክተር ሲሳይ ጠቁመዋል።
ሞገስ ጸጋየ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም