የቫይታሚን ዲ እጥረትና መፍትሄው

ዜና ሀተታ

ቫይታሚን ዲ ከ5ቱ የቫይታሚን አይነቶች ውስጥ የሚጠቀስ ሲሆን በዋነኝነት ሰውነታችን ካልሲየም እና ፎስፎረስ የተባሉትን ንጥረነገሮችን በደም አማካኝነት ከአንጀት ክፍል ወደ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችን እንዲዳረሱ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው፡፡ በተጨማሪም የበሽታ የመከላከል እና የመቋቋም አቅማችንን የሚጨምርና ለህዋሳት እድገት አስፈላጊ የሆነ የቫይታሚን አይነት እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

በዚህም ጨቅላዎች በቀን 400 አለምአቀፍ የቫይታሚን ዲ ዩኒት (IU) ልጆችና ጎልማሶች ደግሞ በቀኑ ከ600 ዓለምአቀፍ የቫይታሚን ዲ ዩኒት (IU) ማግኘት አለባቸው ይላሉ፡፡ እድሜያቸው ከ 70 በላይ ዓመት የሆናቸው ሰዎች እስከ 800 ዓለምአቀፍ የቫይታሚን ዲ ዩኒት (IU)ማግኘት እንዳለባቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ታዲያ በሰውነት ውስጥ በቂ የሆነ የቫይታሚን ዲ ክምችት አለመኖር የቫይታሚን ዲ እጥረት የሚያስከትል ሲሆን ይህም ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶችን ጨምሮ ማንኛውምን የሕብረተሰብ ክፍል ሊያጠቃ ይችላል፡፡ በዓለም ዙሪያም ከ 8 ሰዎች መካከል አንዱ የቫይታሚን ዲ እጥረት አለባቸው ተብሎም እንደሚገመት መረጃዎች ያሣያሉ፡፡

የቫይታሚን ዲ እጥረት ምንነት፣ መከላከያ መንገዶችና ስለሚያስከትለው የጤና ዕክል ኢፕድ የጤና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሞገስ አብርሃን አነጋግሯል

ዶክተር ሞገስ እንደገለጹትም፤ ቫይታሚን ዲ ለአጥንት ጥንካሬ፣ ለደም እና በአጥንት ውስጥ የካልሲየም ሚዛን ለመጠበቅ ፣ ለጤናማ ጡንቻዎች ብሎም እንደ ስኳርና ልብ የመሳሰሉ በሽታዎች መከላከያ ሥርዓቶችን ለመደገፍ የሚያስችል ለሰውነት አስፈላጊ የሆነ ንጥረ ነገር ነው፡፡

በመሆኑም አንድ ሰው በቀን ከ600 እስከ 800 ዓለምአቀፍ የቫይታሚን ዲ ዩኒት (IU)ማግኘት አለበት፡፡ በተለይም እድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች በቀላሉ ለስብራት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ የቫይታሚን ዲ በሚያስፈልገው ልክ መውሰድ አለባቸው ይላሉ፡፡

በቂ ያልሆነ የቫይታሚን ዲ ያላካተተ አመጋገብ እና በቂ የፀሀይ ብርሃን አለማግኘት በዋነኝነት ለቫይታሚን ዲ ለእጥረት የሚያጋልጡ ነው፡፡ ይህም በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ሊከሰት የሚችል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ቫይታሚን ዲ በሰውነታቸውን ውስጥ በበቂ መጠን አለመኖር ለአጥንት መሳሳት፣ ጡንቻ ህመም፣ የሰውነት መተሳሰር እና የድካም ስሜት፣ እንደ ድብርት ያሉ የስሜት ለውጦችን እንዲሁም የበሽታ የመቋቋም አቅማችንን እንዲቀንስና ቶሎ ቶሎ በበሽታ የመጠቃት እድልን የሚጨምር መሆኑንን ገልጸዋል፡፡

ቫይታሚን ዲ ከጸሀይ ብርሃን እንዲሁም እንደ ወተት፣ የዓሳ ዘይት፣ እንቁላል፣ እንደብርቱካን፣ ሙዝ እና አቮካዶ ያሉ የአትክልት ውጤቶች ፣ እርጎ፣ ዓሳ ያሉ ብዙ ቫይታሚን ዲ ያላቸው ምግቦች እና መጠጦች ማግኘት የሚቻል መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

ዶክተር ሞገስ እንደሚሉት ፤ ሰውነታችን ቆዳ ላይ የሚያርፈውን የፀሐይ ብርሃን በመጠቀም 7 ዳይሀድሮኮሌስትሮል የተባለውን በተፈጥሮ በቆዳችን ውስጥ የሚገኘውን ውህድ ወደ ቅድመ ቫይታሚን ዲ3 በመቀየር ሰውነታችን ቫይታሚን ዲን ከፀሀይ ማግኘት ይችላል፡፡

ምንም እንኳን የጸሀይ ብርሃን በሰውነታችን ውስጥ ቫይታሚን ዲ እንዲመረት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ቢሆንም አብዛኛው ሰው የጸሀይ መሞቅ ልማድ ዝቅተኛ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም ከፍተኛ በቫይታሚን ዲ እጥረት የመጋለጥ እድል እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡

በሳምንት ቢያንስ ሶስት ቀን ለ20 ደቂቃ ጸሀይ በመሞቅ በቂ ቫይታሚን ዲ ማግኘትትና በቫይታሚን ዲ እጥረት የሚከሰቱ የጤና ዕክሎችን መከላከል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በቂ ቫይታሚን ዲ ከምግባቸው ወይም ከጸሀይ ያላገኙ ሰዎች በየቀኑ ከ600 እስከ 800 IU (ዓለምአቀፍ የቫይታሚን ዲ ዩኒት) ያላቸውን ማሟያ እንክብሎች ወይም ፈሳሾች (የቫይታሚን ዲ ሰፕልመንት) የህክምና ባለሙያዎችን ጋር በመሄድ መጠቀም የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተጠቀሱት ምልክቶች በራሱ ላይ ያስተዋለ ሰው እንዲሁም በአቅራቢያው ያለ የህክምና ተቋም በመሄድ የቫይታሚን ዲ መጠንን የደም ምርመራ በማድረግ ማወቅ የሚቻል ሲሆን የመከላከያ መንገዶቹን በመጠቀም ሁሉም ዜጋ ጤናውን መጠበቅ ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You