የአእምሮ ህመምና ህክምናው

የሥነ አእምሮ ሳይንስ በዓለም በተለይም በአፍሪካ ገና በማቆጥቆጥ ላይ እንዳለ በሥነ አእምሮ ህክምና ዙሪያ የተጻፉ የተለያዩ መዛግብት ይገልጻሉ፡፡ በኢትጵያም ይህ ህመም በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው በተለያየ ጊዜ ሲነገር የሚሰማ ሲሆን ለዚህ ማሳያውም በሀገሪቱ ከ1930 ዓ.ም ጀምሮ የአእምሮ ህክምና የሚሰጠው ተቋም የአማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ መሆኑ ነው፡፡

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ገለፃ፤ በአሁኑ ጊዜ 970 ሚሊዮን የዓለማችን ሕዝብ በአእምሮ ህመም ይሰቃያል፡፡ እንዲሁም በየዓመቱ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በአእምሮ ህመም ምክንያት እራሳቸውን የሚያጠፉ ሲሆን በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ካሉ አራት ሰዎች ውስጥ ቢያንስ አንዱ በሕይወት ዘመኑ የአእምሮ ህመም ያጋጥመዋል፡፡

ለአእምሮ ህመም ምክንያት ከሚሆኑ ጉዳዮች መሀከል አንዱ የሥራ ቦታ አለመመቸት ሲሆን እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርትም ከ 10 እስከ 15 በመቶ የሚሆነው የአእምሮ ጤና መታወክ እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳል። በሥራ ላይ ከሚገኘው 60 በመቶ የዓለም ሕዝብ ለአእምሮ ጤና መታወክ መንስኤ ለሆነው የሥራ ላይ አደጋ የመከላከል ርምጃ አስቸኳይ ምላሽ የሚሻ መሆኑም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን በየዓመቱ መስከረም 30 ቀን ታስቦ የሚከበር ሲሆን የዚህ ዓመት የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን ‹‹ በሁሉም የሥራ ቦታ ቅድሚያ ለአእምሮ ጤና ›› በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ውሏል፡፡

በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና ዳይሬክተር ዶክተር ሉሉ በቃሉ እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር ለአእምሮ ጤና ህክምናና እክብካቤ የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ በርካቶች ህመሙ እየታየ በጊዜ ወደ ህክምና ተቋማት አይሄዱም፡፡

ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ቤተሰብ ፣ የሰፈር ሰው እንዲሁም የሥራ ባልደረባ ስለ ህመሜ ብነግራቸው መገለል ሊደርስብኝ ይችላል ከሚል አስተሳሰብ ፣ ምልክቶችን ባለማስተዋልና በአጠገባቸው ባሉ ሰዎች ርዳታ ማጣት መሆኑ ይገልጻሉ፡፡

ዶክተር ሉሉ፤ ደህንነቱ ያልተጠበቀና ጤናማ ያልሆነ የሥራ አካባቢ ለአእምሮ መቃወስ አንዱ ምክንያት መሆኑን በመጥቀስ፤ ባልተመቻቸ የሥራ ቦታና አካባቢ መሥራት የአእምሮ ጤናን ከማወክ ባሻገር አጠቃላይ ሕይወትን በማወክ እራሳቸውን እንዲሁም በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ላይ ተጽእኖ የሚፈጥር መሆኑ ይገልጻሉ፡፡

የተዛባ የአአምሮ ጤና ለዝቅተኛ የሥራ ውጤት ይዳርጋል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በዓለማችን በድባቴና በጭንቀት ብቻ በዓመት በአማካኝ 12 ቢሊዮን የሥራ ቀናት እንደሚባክን የተለያየ ጥናቶች እንደሚሳዩ ይጠቅሳሉ፡፡ በኢትጵያም በዚህ ስሜት ምክንያት ወደ ጤና ተቋማት እየሄዱ ፍቃድ የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

ይህም ሰዎች በሥራ ቦታዎቻቸው ደስተኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ለሚመጣ የአእምሮ መታወክ አንዱ ምልክት ነው፡፡ በሥራ ቦታ ላይ የአእምሮ ጤናን ለማጎልበት፣ የሠራተኛውን ጤናና ደህንነት መጠበቅ የቀጣሪዎች፤ የሠራተኛ ተወካዮች እንዲሁም የመንግሥት ኃላፊነት መሆን እንደሚገባው ይገልጻሉ፡፡

በሥራ ቦታ ላይ ለሚፈጠር የአእምሮ መታወክ በአብዛኛው መንስኤው የሥራ ጫና ፣ አነስተኛ ክፍያ፣ ረጅም ጊዜ መቀመጥንና የመሳሰሉት መሆናቸውን ገልጸው፤ ለዚህም መንግሥት እነዚህን ጫናዎች ሊቀንሱ የሚችሉ ፖሊሲዎች ማዘጋጀት እንደሚኖርበት ይመክራሉ፡፡

ሌላው በተቋማት ውስጥ የሚታየው ችግር ሠራተኞች የአእምሮ መታወክ ሲያጋጥማቸው ከሥራ የማሰናበት ሁኔታ እንደሚስተዋል ይጠቁማሉ፡፡ ነገር ግን የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሠራተኞች ሲኖሩ ከማግለልና ከሥራ ከማስወጣት ይልቅ ህመማቸውን በመረዳት ጫና መቀነስና መከታተል እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

ሌላው በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት የሥነልቦና ባለሙያ አቶ እንዳለ ማሞ እንደሚሉት፤ ለአእምሮ ጤና መጠበቅ ወሳኝ ጉዳዮች መካከል ደህንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የሥራ አካባቢ አንዱ ነው፡፡ ያለ አዕምሮ ጤና ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገት የማይታሰብ በመሆኑ እንደ ሀገር ለአእምሮ ህመምና ህክምና የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነው፡፡

በዚህም ሰዎች ህመሙ ሲስተዋልባቸው ወደ ጤና ተቋማት ከመውሰድ ይልቅ ወደ ተለያዩ የእምነት ቦታዎች እንዲሄዱ እንደሚደረግ ያመለክታሉ፡፡ ነገር ግን ጎን ለጎን ወደ ህክምና ተቋማት መውሰድ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

ለአእምሮ ህመም ከሚያጋልጡ ቦታዎች አንዱ የሥራ ቦታ አለመመቸት በመሆኑ የሥራ ቦታዎች ጽዱ ፣ ማረፊያ ቦታዎች ያላቸው እንዲሁም ተቋማት የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ቢኖራቸው ችግሩ ሊቃለል እንደሚችል ያብራራሉ፡፡

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You