– በህትመት ቴክኖሎጂና ግራፊክስ አርት 51 ተማሪዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ፡- በህትመት ዘርፍ የሚታየውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት እየሠራ መሆኑን ብርሃንና ሰላም የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ አስታወቀ፡፡ ኮሌጁ በህትመት ቴክኖሎጂና ግራፊክስ አርት 51 ተማሪዎችን በትናትናው ዕለት አስመርቋል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ህትመትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማከናወንና በህትመት ዘርፉ የሚታየውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት ኮሌጁ የተለያዩ የሙያ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
እንደ አቶ ሽታሁን ገለጻ፤ ኮሌጁ ከማሠልጠን ባለፈ ለህትመት ድርጅቶችና ለዩኒቨርሲቲዎች በህትመት ቴክኖሎጂ ዙሪያ የማማከርና የህትመት ማሽን ጥገና አገልግሎት በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው። ተመራቂዎቹ ለሶስት ዓመታት በህትመት ቴክኖሎጂና ግራፊክስ አርት በደረጃ ሶስት ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ለበርካታ ዓመታት ያካበተውን የህትመት ሥራ ልምድ በመጠቀም የድርጅቱ ሠራተኞችን ብቃት ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባገኘው የሥልጠና ፍቃድ መሠረት ከድርጅቱ ውጪ ለሚመጡ ሠልጣኞች ሥልጠና ዕድል በማመቻቸት ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ሶስት ሥልጠና በመስጠት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ዲን አቶ መስፍን ካሳ በበኩላቸው ኮሌጁ በአጫጭር ጊዜ ሥልጠናዎች በህትመት ቴክኖሎጂ፣ በግራፊክ ዲዛይንና አርት፣ በህትመት ዋጋ ትመና እና በሲልክ ስክሪን የሙያ ዘርፎች በርካታ ሠልጣኞችን ማስመረቁን ገልጸዋል።
ኮሌጁ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በቪዲዮ ኤዲቲንግና አኒሜሽን ሙያ አዲስ የሥልጠና ፕሮግራም ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ተናግረዋል።
ኮሌጁ በሀገር ደረጃ ብቸኛ የህትመት የሙያ ብቃትና ምዘና ማዕከል በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ኮሌጁ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ከተለያዩ ድርጅቶች የተላኩ ባለሙያዎችንና የአቅመ ደካማ ቤተሰብ ልጆች በህትመት እና በግራፊክ ዲዛይንና አርት በነጻ ሥልጠና መስጠቱን አመላክተዋል፡፡
በኮሌጁ በደረጃ ሶስት የተመረቁ ሠልጣኞች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የተሰማሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም በሙያው የሠለጠነ የሰው ኃይል ተፈላጊነትና የኮሌጁን የሥልጠና ጥራት አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ተመራቂዎቹ በበኩላቸው፤ በሀገራችን በህትመት ዘርፍ የሚታየውን የሙያ፣ የፈጠራና የንድፍ ክፍተት ለመሙላት የበኩላችሁን ለመወጣት የሚያስችላቸውን ሙያዊ ክህሎትና ዕውቀት መቅሰማቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ተመራቂዎች የህትመት ዘርፉን በማሳደግ ሂደት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በ2007 ዓ.ም እንደተቋቋመ ታውቋል፡፡
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም