ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሕዝብ ምልክት ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ የኩራት፣ የጥንካሬ፣ የአይበገሬነት መገለጫም ነው፡፡ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ሉዓላዊነትን ባስከበሩ ፍልሚያዎችና በሠላማዊ የትግል ሜዳ ሰንደቋን ከፍ ያደረጉ ጀግኖችን አፍርታለች፡፡ ጀግናው መከላከያችን ሀገራችንን ወራሪ ጠላትን ድል አድርጎ ሰንደቃችንን ሲያውለበልብ ልቡ በሐሴት የማይሞቅ፣ ጀግኖች አትሌቶቻችንም በሠላማዊው የስፖርት ትግል መድረክ ድልን ተቀዳጅተው ሰንደቃችንን ሲያነሱ የደስታ ሳግ የማይተናነቀው ኢትዮጵያዊ አይኖርም፡፡
ረዳት ኮሚሽነር ማርቆስ ገነቴ፣ ወታደርና አትሌት ለሰንደቅ ዓላማ ጠንካራ ስሜትና የጠበቀ ቁርኝት እንዳለቸው ይናገራል፡፡ “ከአትሌትነቱም በተጨማሪ ውትድርና ሙያዬ በመሆኑ ለሰንደቅ ዓላማችን ያለኝ ስሜት ጥልቅና የተለየ ነው” ይላል፡፡
በሁለቱም ሙያ የሀገሩን ሰንደቅ ለማስጠበቅ የቆመው ረዳት ኮሚሽነር ማርቆስ በአትሌቲክሱ መስክ ከጀግናው አበበ ቢቂላ ጀምሮ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ እና የአሁን ዘመን የኦሎምፒክ ጀግኖች አትሌት ታምራት ቶላ እና ትዕግስት አሰፋን ጨምሮ ሌሎችም በርካቶች በልፋት፣ በብዙ ጥረትና በሀገር ፍቅር ስሜት በዓለም አደባባዮች ላይ የሀገራቸው ሰንደቅ ከሌሎች ሀገራት ሰንደቆች ይልቅ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያስቻሉ የኢትዮጵያ ጀግኖች መሆናቸውን አንስቷል፡፡
አትሌቱ እንደገለፀው፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በባዕድ ሀገር ሀገራቸውን ወክለው ለድል ሲታገሉ በየጎዳናው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው የሀገራቸውን ልጆች የሚያበረቱ ኢትዮጵያውያንን መመልከት ጥልቅ ስሜትን የሚፈጥር ነው፡፡
በውድድር ላይ እያለን በሌሎች ሕዝቦች ምድር ላይ ኢትዮጵያውያንን እና ሰንደቃችንን መመልከት ትልቅ ብርታት የሚሰጥ ስንቅ ነው ያለው ኮሚሽነር ማርቆስ፣ ድል አድርገን ሰንደቃችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ የሚሰጠው ስሜት ደግሞ በቃላት መግለጽ የሚቻል አይደለም፡፡ ጥልቅ ስሜትን ይፈጥራል ሲል ይናገራል፡፡
አትሌቱ ሀገሩን ወክሎ በዓለም የስፖርት ውድድር ከተሳተፈባቸውና ድልን ከተቀዳጀባቸው በርካታ የውድድር መድረኮች ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀንጋሪ የዓለም ወጣቶች ሻንፒዮን ላይ ወርቅ አምጥቶ የሀገሩ ሰንደቅ ከፍ እንዲልና ብሔራዊ መዝሙራችንም እንዲዘመር ያደረገበትን ክስተት በሕይወቱ ከተቀዳጃቸው ድሎች ሁሉ ቀዳሚውን ሥፍራ የሚሰጠው እንደሆነም ተናግሯል፡፡
“ኢትዮጵያ” ከጥንት ጀምሮ ቅድመ አያቶቻችን፣ አባቶቻችን ለሰንደቃቸው ተጋድለው ያስተላለፉልን ሀገር ናት ያለው ኮሚሽነር ማርቆስ፣ ይህችን ጥንታዊትና ታሪካዊ ሀገር ከነክብሯ የማስረከብ አደራና ኃላፊነት አለብን ብሏል። በተለይም ወጣቱ ትውልድ ይህን ተገንዝቦ ይህችን በዓለም መድረክ ብዙ የሚያኮራና የሚደነቅ ገጽታዎች ያሏትን ሀገር በየተሰማራበት መስክ ሁሉ በሀገርና በሰንደቅ ዓላማ ፍቅር ስሜት ማገልገል እንደሚገባው ይመክራል፡፡
ነገ “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ ለ17 ጊዜ በመላው ሀገራችን ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ይከበራል፡፡ ቀኑን አስመልክቶም “እንደ ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን፣ እንደ ጀግኖች አትሌቶቻችን ለሰንደቃቸው ዋጋ እየከፈሉ እንዳሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በየተሰማራንበት ሙያ ለሀገራችን ክብርና ከፍታ የምንችለውን ሁሉ መስዋእትነት ለመክፈል እየተጋን ይሁን ሲል መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም