ዜና ትንታኔ
ከ11 የናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ስድስቱ የተፋሰሱን የትብብር ማዕቀፍ አጽድቀዋል፡፡ ይህም የናይል ተፋሰስ ኮሚሽንን ለማቋቋምና በዓባይ ወንዝ ዙሪያ የሚስተዋሉ ኢፍትሃዊነትና አለመግባባቶችን በማስቀረት ትብብርን መሠረት ያደረገ የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚፈጥር የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ ለመሆኑ የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ ለተፋሱ ሀገራት የሚኖረው ፋይዳ ምንድነው? ፍትሃዊነትን ከማስፈን አንጻር የሚያበረክተው አስተዋጽኦስ ምን ይመስላል?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ እንደሚሉት፤ የናይል ተፋሰስ 11 ሀገሮችን ያካትታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዘጠኙ የተፋሰሱን ማዕቀፍ ለማቋቋም እና በተፋሰሱ ስር ያሉትን የትብብር ሥርዓቶች
ለማስኬድ ተደራድረው ስድስቱ ሀገራት ማእቀፉን አጽድቀዋል፡፡ ስድስቱ ሀገራት የተፋሰሱን ማእቀፍ ስላጸደቁ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ሊቋቋም ተቃርቧል፡፡
ኮሚሽኑ ሲቋቋም የተፋሰሱ ሀገራት ውሃ አጠቃቀማቸውን ለየሀገራቱ በሚጠቅምና ሌሎችንም በማይጎዳ መልኩ በሥርዓት መጠቀም የሚቻልበትን መንገድ ለማበጀት በጋራ የሚሠሩበት መሆኑን የሚገልጹት ፕሮፌሰሩ፤ ኮሚሽኑ ሲቋቋም ለኮሚሽኑ በተዘጋጀው ሥርዓት መሠረት የልማትና ትብብር ሥራዎች ይተገበራሉ።
ከዚህ በፊት የዓይል ተፋሰስ ሀገራት በጋራ ስምምነት ያበጁት የአሠራር ማእቀፍ እንዳልነበረው አስታውሰው፤ አሁን ግን የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማዕቀፉን ያጸደቁ ሀገራት የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ለማቋቋም የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በዚህም የተፋሰሱ ሀገራት በአንድ ላይ የሚመሩበት ርእሳነ መንግሥታቱ ጉባዔ ይቋቋማል ያሉት ምሁሩ፤ በዚህ ስር ደግሞ ውሃ ሚኒስትሮች ጉባዔ ይቋቋማል፡፡ ከየሀገራቱ የተውጣጣ የውሃ ሚኒስትሮች አማካሪ ምክር ቤትም ይቋቋማል፡፡ ከዚህ በታች ደግሞ የዘርፍ አማካሪ ቡድኖች ይቋቋማሉ፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ በአንድ ላይ የውሃውን አጠቃቀም እያንዳንዱ ሀገር በግዛቱ ውስጥ ውሃውን በጥቅም ላይ ሊያውል ይችላል፡፡ ነገር ግን በየሀገራቱ ጥቅም ላይ የሚውለው ውሃ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጉልህ በሆነ መልኩ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ፡፡
ይህም ሀገሮች ውሃውን በየሀገራቸው ሚዛናዊና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንዲችሉ እና በመካከላቸው ህብረትና ትብብር እንዲኖር ያዛል፡፡
ግብጽ ማእቀፉን ለማበጀት በተደረገው ድርድር ለ11 ዓመታት አብራ ተጉዛ እንደነበር የሚቁሙት ፕሮፌሰሩ፤ መጨረሻ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ውሃውን በእኛ የበላይት ካላስተዳደርን ወይም ከዚህ በፊት የያዝነው የውሃ አጠቃቅም ካልቀጠለ በሚል ወጥተዋል፡፡
ነገር ግን ግብጾች ቢወጡም ስድስት ሀገሮች ያጸደቁትት ዘጠኝ ሀገራት ተደራድረው ያቋቋሙት የሰነድና የአሠራር ሥርዓት ስለሆነ ሌሎች የውሃውን ሀብት ፍትሃዊነት በሆነ መንገድ ከመጠቀም ወደ ኋላ ሊሉ አይችሉም ይላሉ፡፡
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ ግብጽ አኩርፋ ብትወጣም ወደ ግብጽ የሚሄድ ውሃ ስምምቱን ካጸደቁ ሀገሮች ፈልቆ የሚሄድ ስለሆነ በተለይም ከኢትዮጵያ የሚሄደው 86 በመቶ የሚሆነው ወደ ግብጽ የሚሄደው ውሃ ግብጽ ለመጠቀም ከፈለገች በትብብር እንጂ በአስገዳጅነት እንደማይሆን ሀገሮች በአጠቃላይ በተለይም ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ይህ ማለት ግብጽ ብትቃወምም ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር መሥራት የሚያስችል ሥርዓት ተፈጥሯል፡፡
ማዕቀፉን የተቃወሙ ሀገሮች በተለይ ግብጽና ሱዳን ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ እየሠራ ያለችውን ግድብ በመቃወም አፈንግጠው ቆመዋል የሚሉት ተመራማሪው፤ ይህ ደግሞ የተፋሰሱን ትብብርም ሆነ የተፋሰሱ ሀገራት የሚያደርጉትን የውሃ አጠቃቀም ሥርዓት ወደ ኋላ መቀልበስ አይችሉም። የሚኖራቸው ምርጫ በተዘረጋው ሥርዓት መሠረት በፍትሃዊነት መጠቀም እንጂ ለብቻዬ ልጠቀም የሚባልበት ዘመን አልፏል ነው ያሉት፡፡
ይህም ትብብርም በሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከርና ዘላቂ ልማታቸው ላይ አትኩረው እንዲሠሩ ያዛል ይላሉ፡፡
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሰርቬይንግና ካርታ ኢንጅነሪንግ መምህር ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን ኤርዱኖ በበኩላቸው፤ ማእቀፉ ከመኖሩ በፊት በተናጠል የተደረጉ ነገሮች ሁሉ በጥርጣሬ ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። በዚህም አንዱ አንዱን ለማጥፋት በሚደረግ የፖለቲካ ድራማ ላይ የተመሠረተ አካሄድ ሲስተዋል ቆይቷል፡፡
የትብብር ማዕቀፉ የትኛውንም ሀገር ሳይበድል ወይም ሳይጠራጠር የውሃ ዋስትናው የሚከበርበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ይህም በፖለቲካና በኢኮኖሚ ያለው ጠቀሜታ ብዙ ነው ይላሉ፡፡
ሁሉም የተፋሰሱ አባል ሀገራት በባለሙያ የተደገፈ ትንተና ተካሂዶ የየሀገራቱ ፍላጎት ምን ያህል እንደሆነ ታውቆ ውሃው ጥቅም ላይ እንዲውል መሥራት እንደሚያስፈልግ የሚጠቅሱት ምሁሩ፤ ግብጽ በዓለም ከሚታወቀው ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት፡፡ ነገር ግን ማውራት አትፈልግም ሙሉ በሙሉ በዓባይ ጥገኛ ነኝና አትንኩብኝ ትላለች፡፡ ይህን አጀንዳ ማቆምና በምን መልኩ በትብብር መጠቀም እንደሚቻል ማሰብ መቻል ይርባታል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የሌሎች ሀገሮች ሕዝብ እያደገ በሄደ ቁጥር በዓባይ ወንዝ የመጠቀም ፍላጎት እጨመረ እንደሚሄድ መገንዘብ ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ኢንጅነር ጥላሁን፤ የግብጽ ያረጀ እሳቤ የሚያበቃበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ግብጽ በዚህ ግትር አቋሟ የምትቀጥል ከሆነ ከአባል ሀገራቱ የሚገጥማት ተቃውሞ እየጨመረ መሄዱ አይቀርም ነው ያሉት፡፡
የዓባይ ውሃ 86 በመቶ አምጪ ኢትዮጵያ ናት የሚሉት ምሁሩ፤ ግብጽ በትብብር ለመሥራና በፍትሃዊነት መጠቀም ሲገባት ሁሌም ኢትዮጵያን በጠላትነት ፈርጃ ለውድቀቷ ስትሠራ መኖሯ አስገራሚ ነው፡፡
የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ትብብር መጠናከር ሀገራት ያላቸውን ሀብት በፍትሃዊነት እንዲጠቀሙ እድል የሚፈጠር መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ እውን እንዲሆን ግን ግብጽ የመሰሉ አትንኩብኝ የሚል የተሳሳተ እሳቤ ያላቸው ሀገራት የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ ያስፈልጋል። አንድ በመቶ የውሃ አስተዋጽኦ የሌላት ሀገር 86 በመቶ የውሃ አበርክቶ ያላትን ሀገር ተመልካች ለማድረግ መሞከር በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
እንደ ምሁሩ ገለጻ፤ ባለፉት ዓመታት የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማእቀፍ ባለመኖሩ አንዱ አንዱን ለማጥፋት በሚደረግ የፖለቲካ ድራማ ላይ የተመሠረተ አካሄድ ይስተዋል ነበር፡፡ የትብብር ማእቀፉ መኖሩ አንዱ ሀገር ሌላኛውን ሀገር ሳይበድል የውሃ ዋስትናው የሚከበርበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ግብጽም የምታራምደውን የእኔ ብቻ የሚል ያለፈበት እሳቤ ትታ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በትብብር መሥራት ይኖርባታል፡፡
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ለምን ተጠቀመች ተብሎ የሚመጣባትን ጠላት ለመመከት መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በትብብር መመከት እንዳለባቸው የሚጠቁሙት ምሁሩ፤ ግብጽ ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ የምታደርሰው ጫና የሚሳካላት ከሆነ ነገ ወደ ሌሎችም የተፋሰሱ ሀገራት መዞሯ አይቀርም፡፡ ከዚህ አኳያ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የትብብር ማዕቀፉ በአግባቡ እንዲተገበር መሥራትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ጎን መቆም እንዳለባቸውም ይገልጻሉ፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም