ተፈጥሮና የሰው ልጅ አይነጣጠሉም፡፡ የሰው ልጅ ለተፈጥሮ በሚያደርገው እንክብካቤ መጠን በተፈጥሮ ይካሳል፡፡ ኑሮው ምቹ ይሆናል፡፡ ተፈጥሮን ባራቆተ መጠንም ሕይወቱ የተራቆተ ይሆናል፡፡ ተፈጥሮ በሰው ልጅ ለደረሰባት በደል የተናገረችው ነገር ባይኖርም የሰው ልጅ ግን ከተፈጥሮ በተግባር እየተሰጠው ባለው ምላሽ የደረሰበት ችግር የሕልውና ስጋት ይዞ ከመጣ ሰንብቷል።
ከእነዚህም ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚከሰቱ የተፈጥሯዊ አደጋዎች /ጎርፍ ድርቅ ወዘተ/ የጤና እክሎች ተጠቃሽ ናቸው። ሀገራችን ኢትዮጵያም የችግሩ ተጠቂ ከሆኑ ሕዝቦች አንዷ ናት። በተለይም በተደጋጋሚ በሚከሰተው ድርቅ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ለረሃብ ዳርጓል፡፡
ይህ የተፈጥሮ አካባቢን በአግባቡ ተንከባክቦ ካለመጠበቅ የሚነሳው ችግር፤ በምግብ እህል እራሳችንን እንዳንችል በማድረግ በምግብ እህል ጠባቂ አድርጎናል። በቀላሉ ከጓሯችን ልናመርታቸው የምንችላቸውን ምግቦች ጭምር ከቀደሙት ዘመናት በተሻለ መንገድ ለማስቀጠል ሳንችል ቀርተናል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ለቅጠላ ቅጠልና ፍራፍሬ ምግቦች ያለን አመለካከት ዛሬ ላይ እንዳለው የዳበረ አልነበረም። እነዚህን ምግቦች የሚመገበው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ ብቻ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። በእርግጥ ዛሬም ቢሆን ለአንድ ኪሎ ሥጋና ዓሣ አልያም ወተት የሚከፈለው የገንዘብ መጠን ከአንድ ኪሎ ቆስጣና ጎመን ወይንም ሰላጣ እንደሚበልጥ መካድ አይቻልም።
የዛሬው የጽሑፌ መነሻ ሀሳብ በራሳችን አቅም ልንሠራው የምንችለውን እና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያለውን የጓሮ አትክልት ነው፡፡ የጓሮ አትክልት በትንሽ ቦታ ሊለማ የሚችል እየጨመረ ለመጣው የከተማ ነዋሪ የምግብ አቅርቦት ትልቅ አቅም የሚሆን ነው፡፡
ይህም ሆኖ ግን ከመጣንበት ሥራ ባሕል አኳያ ይህን ማድረግ ሳንችል ቀርተናል፡፡ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ውሃ እያለ ባዶ መሬት እያለ እንደ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ጎመንና ቲማቲም ያሉ ምርቶችን በውድ ዋጋ ስንገዛ እንታያለን።
በየጓሯችን በቀላሉ ልናለማችን የምንችላቸው አትክልት እና ፍራፍሬዎች ልብ ብለን ካስተዋልነው ጠቀሜታቸው ዘርፈ ብዙ ነው። እነዚህን ምርቶች ከግቢያችን ልናገኛቸው ከመቻላችን ባለፈ ወጪ ይቀንሱልናል፤ ለጤናችንም የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍያለ እንደሆነም ይታመናል።
ዛሬ በየአትክልት መደብሮችና በየጉሊቱ የሚሸጡልን አትክልት እና ፍራፍሬዎች በተሻለ መንገድ እና ቴክኖሎጂ ማምረት ወደሚያስችል ሥርዓት ብንሻገር፤ በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል ለምናደርገው ሀገራዊ ጥረት ሆነ የተመጣጣነ የምግብ አቅርቦትን ለመፍጠር ወሳኝ አቅም ሊሆኑ እንደሚችል ማሰብ የሚከብድ አይደለም።
በእርግጥ እራሱ የጓሮ አትክልት የሚለውን ስያሜ በሚፈጠርብን ስሜት የምንለያይ ይመስለኛል። የጓሮ አትክልት ልማት አነሰም በዛ የግብርና ሙያ የሚጠይቅ ነው። ለእኔ ዘመን ትውልድ ደግሞ የጓሮ አትክልት ልማት በየግቢያችን የምንከውነው ብቻ ሳይሆን አንድ የትምህርት አይነት ሆኖ የሠለጠንበትም ነው።
በዛ ዘመን የነበሩት ትምህርት ቤቶች የቦታ ችግር ስለሌለባቸው፤ መምህራኖች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው የእርሻ ትምህርት በመስክ ላይ የአትክልት መደብ/የእርሻ ቦታ ተዘጋጅቶ በተግባር ይሰጡ ነበር። በነገራችን ላይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ «ሀይስኩል» ስንማርም ዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍል የእርሻ ትምህርት ነበር።
አስረኛ ክፍል የእርሻ መምህራችን በተደጋጋሚ «ውሃ፤ አፈር፤ አየር ካለ ሕይወት አለ» በሚል ይነግሩን ነበር። ይሄ አባባል ዛሬም የሚሠራ ነው። ባጭሩ በያለንበት ቦታ በጣም በትንንሽ ቦታዎች ለይ በቀላል ወጪ የጓሮ አትክልት ማልማት እንችላለን። አንዳንድ ዕፅዋት ወዳድ ሰዎች በተጣበበ ግቢያቸው ውስጥ የተከሏቸውን ዕፅዋት ከሥራ መልስ ብቻ እየተንከባከቡ ብዙ ሲያተርፉ አይተናል።
ለዚህ ጉዳይ መንግሥትም የተለየ ትኩረት መስጠት ከጀመረ ውሎ ማደሩን ሁላችንም የምናውቀው ነው። ለዚህም የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ማንሳት ይቻላል። የሌማት ትሩፋት ዓላማው የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥና ክብርን ማስጠበቅ ነው ። በተለይም ሥጋ፣ እንቁላል፣ ማር እና ወተት ትርፍ ምርት ሆነው እንዲገኙ ማልማትና መጠቀምን መሠረት ያደረገ ነው። መርሐ-ግብሩ የኢትዮጵያን ደካማ የአምራችነት ታሪክ በመቀየር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የኢኮኖሚ እድገትን ማፋጠንን መዳረሻው ያደረገ ነው።
በሌማት ትሩፋት ገበታን በተመጣጠነ ምግብ መሙላት ከተቻለ የእናቶችንና የሕጻናትን ፍላጎት በማሟላት በአካል የዳበረና በአዕምሮ የበለፀገ ትውልድ መገንባት ይቻላል የሚለውም ቁልፍ ዓላማው ነው። በተቃራኒው ያልተመጣጠነ አመጋገብ ጤና ላይ ከሚፈጥረው ችግር ባለፈ በሰዎች መካከል ያለውን የአኗኗር ደረጃ በማስፋት፣ ማኅበራዊ ቀውስን በመፍጠርና ኢኮኖሚውን በመጉዳት ምርትና ምርታማነትን ወደ ኋላ የሚጎትት ነው።
ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በከባድ ትግል ላይ የሚገኙ ሀገራትን የልማት ግስጋሴ በመግታት ቀድሞ ወደነበሩበት የድህነት አረንቋ እንዲመለሱ የሚዳርግ ነው። የሌማት ትሩፋት የኑሮ ውድነቱን በማስከንም ሆነ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
መንግሥት እቅዱን ያስጀመረው በመንግሥት ደረጃ በትልቁ እንደ ሀገር ለመተግበር ነው። ማለትም እንደ ግለሰብ እነዚህን ነገሮች መሬት አውርዶ ለመተግበር የመኖሪያ አካባቢን ጨምሮ በሌሎች ነባራዊ ጉዳዮችም የሚወሰን ይሆናል። ለምሳሌ ንብ ማነብ፤ ከብት ማርባት በከተማ የአኗኗር ሁኔታ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
በአንጻሩ በትንንሽ ቦታዎች በቀላሉ ሊሠሩ የሚችሉ እንደ ቆስጣ፣ ሰላጣ ቃሪያና ጎመን የመሳሰሉትን ማልማት ግን ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እጃቸው ላይ ያሉ አቅሞችን በመጠቀም ሊተገብሩት የሚችሉት እንደሆነ ይሰማኛል።
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከልማት ጋር በተያያዘ ብዙ ለውጦች እየተከናወኑባት እንደሆነ ግልጽ ነው። ነገር ግን በአምስቱም በሮቿ በቅርብ የሚገኙ ከተሞች በዚህ ረገድ ብዙ ሊሠሩበት የሚያስችላቸው አቅም እንዳለ እገነዘባለሁ። አነሰም በዛ በየአካባቢው ውሃ አለ። ከየግለሰብ ጓሮ ጀምሮ በየሰፈሩ ጦም ውለው ጦም የሚያድሩ ብዙ ክፍት ቦታዎችም አሉ።
ምን አልባትም በየቤቱ አልያም በየጎረቤቱ ደግሞ አንድም ሆነ ሁለት ሥራ ፈት ማለቴ ሥራ አጥ አምራች ኃይል በየጓሮው አትክልት ሊያለማ የሚችል ይኖራል። ይህም በተለይ ልጆችን በቤት ውስጥ ሲንከባከቡ ለሚውሉ እናቶች የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል።
ይህን በጥቂቱ ጠቆም ለማድረግ ያህል አነሳሁ እንጂ ሁኔታዎች የተመቻቹለትና ትንሽ የበረታ ካለ በተያያዥነት ሊሠሩ የሚችሉ ብዙ ሥራዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይሰማኛል። ለምሳሌ ከጓሮ አትክልት ልማት ጋር በግ ማደለብ፤ ዶሮ ማርባትና የመሳሰሉት። እነዚህ ነገሮች ቋሚ መተዳደሪያ መሆን የሚችሉ ናቸው።
ቀለል አድርገው ከታዩም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ወጪዎችን ለምሳሌ ለልጆች ልብስና የትምህርት ቤት ቁሳቁስ የዓመት በዓል ግዥ የመሳሰሉትን ለመሸፈን ያስችላሉ። ይህ ደግሞ አሁን አሁን እያደገ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማቅለል እንደ አንድ ስትራቴጂክ አቅም ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
ከዚህ አንጻር፤ እያንዳንዱ ዜጋ በእጁ ያሉ ዕድሎችን አውቆ እና ተረድቶ ሊጠቀምበት ይገባል፤ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትም የዜጎችን ጥረት ከመደገፍ ባለፈ፤ ጥረቶቹ የተሻለ ውጤታማ የሚሆኑበትን አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። መልካም ግዜ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም