ኢትዮጵያ የጥቁር ዓባይ መነሻ ስትሆን 86 በመቶ የሚደርሰው የናይል ወንዝ ውሃ ታመነጫለች። ይህ የውሃ ድርሻዋም እስከ ቅርብ ዘመን ድረስ ባለሙሉ መብትና ባለብዙ ተጽዕኖ አሳራፊ ሀገር እንድትሆን አድርጓት ቆይቷል።
ሆኖም ከቅኝ ግዛት መስፋፋት ጋር በተያያዘ ያላትን መብትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጣች መጣች። በተቃራኒው ደግሞ ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ ሲገብሩና ሲማለዱ የነበሩት ግብጾችና ሱዳኖች የቅኝ ገዢዎችን፤ በተለይም የእንግሊዝን ተጽዕኖ ፈጣሪነት በመጠቀም የበላይነቱን ለመያዝ ጥረዋል። የተዛባ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብቶችን በመጥቀስ የመከራከሪያ አጀንዳ አድርገው ማቅረብ ሞክረዋል።
በታሪካዊ እና ተፈጥሮአዊ መብቶች ላይ ተመስርተው በታችኛው ተፋሰስ አገራት ከሚቀርቡ የመብት ክርክሮች መለስ ዓባይን አስመልክቶ እስካሁን ያለው የመከራከሪያ ነጥብ ከቅኝ ግዛት ጋር የተያያዙ ውሎች ናቸው። የመጀመሪያው በቅኝ ግዛት ዘመን እ.ኤ.አ ግንቦት 7 ቀን 1929 በታላቋ ብሪታኒያና በግብፅ መካከል የተደረገው ስምምነት ሲሆን፣ ሁለተኛው ከሰላሳ ዓመት ቆይታ በኋላ ማለትም ከነጻነት ወዲህ እ.ኤ.አ ሕዳር 8 ቀን 1959 በሱዳንና ግብፅ መካከል የተፈረሙ ስምምነቶች ለአብነት ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ሁለት ስምምነቶች በሚፈረሙበት ወቅት እንግሊዝ ከላይኛው ተፋሰስ አገራት ሱዳንን፣ ታንዛኒያን፣ ኡጋንዳን፣ እና ኬንያን በመወከል ግዴታ ከመግባቷ ውጪ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራት ተካፋይ አልነበሩም። በተለይም ኢትዮጵያ በወቅቱ ነፃ ሀገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በስምምነቱ ተሳታፊ መሆን ቢገባትም በሂደቱ በጋራ መብቷን እንድትወስን ምንም አይነት ጥያቄ ሳይቀርብላት ቀርቷል።
በ1929 እና 1959 በተደረጉት ስምምነቶች መሰረት ግብፅ በዓባይ ላይ የባለቤትነት መብት ስትጎናፀፍና በተጠቃሚነት ረገድም ከ55 ቢሊዮን ኪዩቢክ በላይ ውሃ ድርሻ እንዲኖራት፤ ሱዳንም 18 ቢሊዮን ኪዩቢክ የውሃ መጠን ድርሻ እንዲኖራት ተደርጓል። ከ86 በመቶ በላይ የሚሆነው የናይል ውሃ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ግን ቅንጣት ታክል የውሃ ድርሻ እንዲኖራት ሳይደረግ የበይ ተመልካች ሆና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቆይታለች።
እነዚህ ሁለቱ ስምምነቶች እስከዛሬም ድረስ በሕዳሴ ግድብ ላይ በሚደረጉ ውይይቶች እንደማጣቀሻ እየቀረቡ ግብጾች በማደናገርያነት እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። አድሏዊና አፍትሃዊ የሆኑት የ1929ኙም ሆነ የ1959ኙ ስምምነቶች ከ86 በመቶ በላይ የናይል ውሃ ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያን ያገለሉ መሆናቸው እየታወቀ ግብጽ ዛሬም ድረስ ሙጥኝ ብላ ትገኛለች።
ግትር የሆነው የግብጽ አቋም ከፍተኛ ቁጭት እና ሀገራዊ የመልማት ፍላጎት እልህ ሲፈጥር ቆይቷል። ይህ ሀገራዊ ቁጭትና እልህም ጊዜው ፈቅዶ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ጉባ ላይ ተጥሏል። የኢትዮጵያውያንም የዘመናት ቁጭት መልስ ያገኘበት ታሪክ ተመዝግቧል። የኢትዮጵያም ተነሳሽነት በሌሎቹ ተፋሰሱ ሀገራት ዘንድ ከፍተኛ የመልማት ፍላጎት ተስፋ ፈንጥቋል።
በተፋሰሱ ዙርያ ያሉ ሕዝቦች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱና ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ጥቅም ላይ የማዋል ፍላጎታቸው እያደገ በመሄዱ ኢትዮጵያ ባሻገር የሌሎችም ፍላጎት መሆን ጀምሯል። በወንዙ የላይኛው ክፍል የሚገኙ ሀገራት ስለዓባይ ውሃ አጠቃቀም ከዚህ በፊት የተፈረሙትን የቅኝ ግዛት ስምምነቶች በመንቀፍ እንደማይቀበሉት በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ አሳውቀዋል።
ከ1999 እ.ኤ.አ ጀምሮም የናይል ተፋሰስ ትብብር (Nile Basin Initiative) የተሰኘ ጊዜያዊ የትብብር ማእቀፍ በማቋቋም አንድ ልዩ የናይል ቤዚን ኮሚሽን ለመመስረት ፍላጎት አሳዩ። በዓለም አቀፍ ሕግ ይዘት የተቃኘ ተፋሰስ- አቀፍ ውል ለማዘጋጀት በናይል የሚኒስትሮች ጥምረት (counselee) በኩል ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል።
እ.ኤ.አ ግብፅና ሱዳን የፈረሙት የ1959 ስምምነት የዓባይን ውኃ ሀብት ከአሥር የተፋሰሱ ተጋሪ ሀገሮች ለሁለቱ ብቻ የሚያከፋፍል በመሆኑ ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ ስምምነት ሆኖ ሌሎቹን ተጋሪ አገሮች ለማስገደድ እንደማይችል የዘርፉ ምሁራን ሲወተውቱ ቆይተዋል። ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ ጨምሮ በሁሉም ዘንድ የሚነሳ ገዥ ሀሳብ ነው።
ኢትዮጵያም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር ተከታታይነት ያላቸውን ድርድሮች በማድረግና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አካሄድን በመከተል ዛሬ ላይ አሁን ከምትገኝበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። እግረ መንገዷንም የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ወደ ፍጻሜው በማድረስ መጪውን ብሩህ ጊዜ እየተጠባበቀች ነው። ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ሀገራትም በጋራ መብታቸውን የማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት የናይል የትብብር ማዕቀፍ ዕውን የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርገዋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በዓለም ላይ ወደ 276 የሚጠጉ ድምበር ተሻጋሪ ወንዞች አሉ። እነዚህን ወንዞች 145 የሚሆኑ ሀገራት ይጋራሉ። አንዳንድ ሀገራት ወንዞቹን የሚመለከት ሕግ አላቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ የጋራ የውሃ አጠቃቀም ሕግ የላቸውም። ነገር ግን ሕጉ ያላቸው ሀገራት ውሃን ዘላቂና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ። አንዱ ሕጋዊ ማዕቀፍ ሆኖ በቀጣይ የናይልን የውሃ አጠቃቀም ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጠው የናይል የትብብር ማዕቀፍ ነው።
የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የዓባይን ውሃ በጋራ፣ በእኩልነትና ምክንያታዊ በሆነ ሁኔታ ውሃውን መጠቀምና አብሮ መንከባከብ የሚያካትትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የሚተዳደሩባቸውን መርሆችን ጭምር ያካተተ ማዕቀፍ ነው። ይህም በአሥራ አንድ ሀገራት መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው።
ጉዳዩን የኢትዮጵያ መንግስት የቅርብ ክትትል ያደረገበት በመሆኑ የተሳካ እየሆነ መጥቷል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችን በሚያገኙበት አጋጣሚ የውሃ ሀብትን በጋራ ማልማትና መጠቀም የሚቻልባቸውን መንገዶች ያነሳሉ። ይህም የኢትዮጵያ የውሃ ዲፕሎማሲ ሥራ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ ቀድማ ማዕቀፉን ያጸደቀች ሲሆን ከዛ በኋላ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋዳንዳ ገብተውበት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህ የመጣውም በጋራ ለመልማት ካለ ፍላጎት የመነጨ ነው። በቅርቡ ደግሞ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን በምክር ቤቶቻቸው አጽድቀውታል።
ይህ መሆኑ ደግሞ ለዘመናት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የላይኛው ተፋስስ ሀገሮች ከውሃው በፍትሃዊነት የመጠቀም መብታቸውን ከማረጋገጡም በሻገር ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር ስታደርገው የነበረውን የፍትሃዊነት ጥያቀቄና በጋራ የመልማት ሀሳብ ሌሎች ሀገራት እንዲቀላቀሉና ክርክሮችንም የሚያካሂዱት ሀገራት ሳይሆኑ ኮሚሽኑ እንዲሆን ያስችላል።
ይህ ማለት ጉዳዩ የኢትዮጵያ እና የግብጽ ብቻ ሳይሆን የ11ዱም ሀገራት ጉዳይ እንዲሆን አድርጎታል። ጠቅለል ሲደረግ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ወደ ኮሚሽን ማደጉ የሚከተሉትን ጥቅሞች ይዞ ይመጣል። የመጀመሪያው እና ዋናው ነገር የናይልን ውሃ በትብብር ለመጠቀምና ለማልማት ያስችላል። በቅኝ ግዛት ውሎች ውሃውን ከመጠቀም ተገለው ነበሩ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ውሃውን በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት ይጎናጸፋል።
ኢትዮጵያ ይህንኑ ሀሳብ መነሻ በማድረግ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር ተከታታይነት ያላቸውን ድርድሮች በማድረግና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ሀሳብን እያራመደች ዛሬ ላይ ደርሳለች። እግረ መንገዷንም የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ወደ ማገባደዱ በማድረስ መጪውን ብሩህ ተስፋ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች። በተለይም የናይል የትብብር ማዕቀፍ ወደ ኮሚሽን ደረጃ መሸጋገሩ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ መስሎ የቆየው ውዝግብ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በእኔነት ስሜት እንዲሟገቱበት እና እንዲከራከሩበት እድል የሰጠ ሆኗል።
በተፋሰሱ ሀገራት ዘንድ የሚታየውን አለመግባባት እና ውዝግብ የሚያረግብ ይሆናል። የአባይ ግድብ ጉዳይ ከሶስቱ ሀገራት እና አህጉር አልፎ ዓለም አቀፍ መወያያ አጀንዳ እስከመሆን ደርሷል። ለመጀመሪያ ጊዜም በጸጥታው ምክር ቤት የታየ አነጋጋሪ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል።
ይህ ጉዳይ ከባህሪው በላይ ተለጥጦ ዓለም አቀፋዊ የጸጥታ ችግር ጭምር ተደርጎ ከመወሰዱም በላይ የአንዳንድ ሀገራት መሪዎች ጭምር በቦንብ እንዲመታ ምክር እስከመስጠት ደርሰዋል። ይህ ውዝግቡ የደረሰበትን ጡዘት የሚያሳይ ነው። የተፋሰሱ ሀገራት አሁን በደረሱበት ደረጃ ችግራቸውን ሁሉ በኮሚሽኑ በኩል የሚፈቱ በመሆኑ ወደ ሰላምና ትብብር የሚመጡበት አጋጣሚን ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል።
ከዚህም በዘለለ የሚቋቋመው ኮሚሽን የናይልን ውሃ ከብክነት በጻዳ መልኩ በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችል ስትራቴጂ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል። የናይል ወንዝ የአፍሪካን 1/10 የቦታ ስፋት የሚሸፍን ነው። አስራ አንዱ ሀገራትም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተፋሰሱ ሀገራት ተብለው ይጠራሉ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በናይል የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ እስከ 300 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ይኖራል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን የዚህ ወንዝ ልማት በቀጥታ ከነዋሪዎች ሕይወት መሻሻል ጋር የሚያያዝ ነው።
የናይል የትብብር ማዕቀፍ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ኢትዮጵያ በፍትሃዊነት መርህ የዓባይን ውሃ መጠቀም ብቻ ሳይሆን የማልማትም ሥራ እያከናወነች ነው። ከዚህም ባሻገር የወንዙን ጤናማ የፍሰት ሂደት ለመጠበቅና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለሁሉም ሀገራት በቂ ውሃ እንዲኖር በማሰብ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ላይ ትገኛለች።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለውሃ መጠን መጨመር ጉልህ ሚና አለው። ችግኞች በተተከሉ ቁጥር አካባቢ ላይ የሚደርሰውን የመሬት መራቆት ይቀንሳል። የደን ሽፋንን ያሻሽላል። የግድቦችንም እድሜ ያራዝማል። የተፋሰሱ ሀገራትም በቂ ውሃ በዘላቂነት ማግኘት እንዲችሉ ይረዳል።
ባለፉት አምሥት ዓመታት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ በተከለቻቸው ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ውስጥ ወደ ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን የሚሆነው የተተከለው በዓባይ ተፋሰስ ነው። የዓባይን ውሃ በማልማት የሚመጣው ጠቀሜታ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለታችኛው ተፋሰስ ሀገሮችም ጭምር ጠቀሜታው የጎላ ነው። ይህ የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ የናይልን ውሃ በፍትሃዊነት የመጠቀም ፍላጎቷ አንዱ ማሳያ ነው።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም