የከበሩ ማእድናትን የሚያስጌጡት የጥበበኛው እጆች

አዲስ አበባ ተክለሃይማኖት አካባቢ ተወልዶ ያደገው የዛሬው የስኬት ገጽ እንግዳችን የበርካታ ባለሙያዎች ባለቤት ነው። ለእጅ ሥራና ለጥበብ ልዩ ፍቅር አለው። ከልጅነት እስከ ዕውቀት የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን በመስራት ነው ያደገው። ከዚህ ጎን ለጎንም ለማዕድን ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ በተለይ በማዕድን ዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ በርካታ ዜጎችን መድረስ ችሏል። ስልጠና ከመስጠት በተጨማሪም የከበሩ ድንጋዮችን እያሽሞነሞነ፤ በከበሩ ድንጋዮች ላይ እሴት እየጨመረ ለገበያ ማቅረብ ከጀመረ ሰንብቷል።

የስኬት እንግዳችን አቶ የዝና ማሞ ይባላል። የዝና ጌጣጌጥ እና ተዛማጅ ሥራዎች ማምረቻ ድርጅት መስራችና ባለቤት ነው። የማዕድን ዘርፉን ከተቀላቀለ ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ከማዕድን ሥራው አስቀድሞ በርካታ የጥበብ ሥራዎች ይሰራ እንደነበርና በተለይም በስዕል ሥራዎች እንደሚታወቅ አጫውቶናል። ለዚህም በመስሪያ ቦታው የሚታዩ ስዕሎች ምስክር ናቸው። ከስዕል ሥራው ባሻገር የሸክላ ሥራ፣ የእንጨት ሥራ፣ ሽመና፣ ቅርፃ-ቅርፅና ሌሎችንም ይጠበብባቸዋል። ለሁሉም የእጅ ሥራ ጥበቦች ተሰጥኦና ልዩ ፍቅር ያለው በመሆኑ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስን በሙሉ ራሱ ያመርታል።

የጥበብ ሥራ የተሰጠው አቶ የዝና፤ ውስጣዊ ፍላጎቱን በትምህርትና በልምምድ አሳድጓል። የከፍተኛ ትምህርቱን በስዕልና ቅርጻቅርጽ በመከታተልም ዲፕሎማ አግኝቷል። በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ በሚሰራበት ወቅት ያጋጠመው የትምህርት ዕድል ማዕድን ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ በር የከፈተለት እንደሆነም ይናገራል። መንግሥት ባመቻቸለት ዕድል በቻይና የጌጣጌጥ ሙያን ተምሯል። ይሁንና የጌጣጌጥ ሙያን መማር ብቻውን ምንም ዋጋ እንደሌለው በመረዳት በከበሩ ማዕድናት ዙሪያም የተለያዩ ስልጠናዎችን በግሉ እዚያው ቻይና ተመላልሶ ከከበሩ ማዕድናት ጌጣጌጦች እንዴት እንደሚሰሩ ስልጠና ወስዷል። በዚህም የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችንም አግኝቷል።

በጌጣጌጥ ሥራ መሰረታዊ ከሚባሉት ማቅለጥ፣ መበየድ፣ መቁረጥ መሳብ፣ ወደ ሽቦ መቀየር፣ ወደ ጠፍጣፋ መቀየርና ሌሎችንም ጨምሮ እስከ መጨረሻ ያለውንና ዛሬ ላይ የደረሰውን ቴክኖሎጂ በስልጠና ማግኘቱን ይገልፃል። ዛሬ ላይ የደረሰው የመጨረሻው ቴክኖሎጂ ካስቲንግ ወይም ሞልዶችንና ጌጦችን በኮምፒዩተር እየታገዙ ዲዛይን ማድረግና መስራት እንደሆነ ጠቅሶ፤ እነዚህን ስልጠናዎችም በግሉ ቻይና ተመላልሶ እንዳገኛቸው ያመለክታል።

በተለያዩ የስዕል ሥራዎቹ እንዲሁም በቅርጻ ቅርጽ ሥራው የሚታወቀው አቶ የዝና፤ የማዕድን ዘርፉን በዕውቀትና በከፍተኛ አቅም ለመስራት እንዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ትልቅ ደረጃ ላይ የማድረስ ራዕይ ሰንቋል። በተለይም የዝና ጌጣጌጥ እና ተዛማጅ ሥራዎች ማምረቻ ድርጅት ሲመሰረት ከውጭ የሚገቡ ጌጣጌጦችን በሀገር ውስጥ መተካትን ዋና ዓላማው አድርጎ መነሳቱን ይናገራል። ይህንንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳካት እንደሚቻልም ሙሉ ዕምነት አለው።

አቶ የዝና እንደሚለው፤ በአገር ውስጥ በቂና ገና ያልተነካ ሰፊ የማዕድን ሃብት አለ። ይህን ሃብት አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል። በርካታ ጌጣጌጦች ከውጭ አገር እየገቡ ሲሆን፤ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ጌጣጌጦች ቢኖሩም ሥራውን የሚሰሩት አብዛኞቹ የውጭ ዜጎች ናቸው። ይህን ለመቀየር ደግሞ በማዕድን ዘርፍ ስልጠና መስጠት የግድ በመሆኑ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። አሁን ላይ ደግሞ ስልጠናውን በመግታት የተለያዩ የጌጣጌጥ ሥራዎችንና የከበሩ ማዕድናትን በማቀላቀል እያመረተ ይገኛል። ምርቶቹን በተለይም ጌጣጌጦቹን ከአገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያም ያቀርባል።

ከሚያመርታቸው ጌጣጌጦች መካከል የጆሮ፣ የአንገት፣ የጣት ቀለበቶች፣ የእግር አልቦና የመሳሰሉት ይገኙበታል። እነዚህን መዋቢያ ጌጣጌጦች ከከበሩ ድንጋዮች እያመረተ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ሲሆን ለአብነትም ካናዳ፣ አሜሪካና ቻይና ምርቶቹን ልኳል። ለበቅርቡም ምርቶቹን ወደ ቻይና ለመላክ የውል ስምምነት በማድረግ በርካታ የጌጣጌጥ ምርቶችን ለመላክ በዝግጅት ላይ ነው። ለሀገር ውስጥ የወርቅ፣ ብርና ጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆችም እንዲሁ ምርቶቹን እያቀረበ መሆኑን የጠቀሰው አቶ የዝና፤ ለብርና ጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆች በስፋት በማቅረብ ከውጭ የሚገባውን ማስቀረት እንደሚችል ተናግሯል።

አብዛኞቹ ወርቅ፣ ብርና ጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆች የሚይዟቸው መዋቢያ ጌጣጌጦች ከጣልያን፣ ከህንድ፣ ከቻይና ከዱባይ እንደሚመጡ የጠቀሰው አቶ የዝና፤ ከእነዚህ ሀገራት የሚገቡትን ምርቶች በከፍተኛ ጥራት በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ትልቅ አቅም እንዳለና ይህም መቶ በመቶ እንደሚሳካ ሙሉ ዕምነቱ ነው። ለዚህም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የከበሩ ድንጋዮች መኖራቸው አንዱና ዋነኛው አስቻይ ሁኔታ ጠቅሶ፤ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍረት መቻሉም ሌላው ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳል። ከማምረት ባለፈም በዘርፉ ያካበተውን ዕውቅት ለሌሎች በማስተላለፍ በርካቶችን አሰልጥኖ በማዕድን ሥራ ባለሙያዎችን መፍጠር ችሏል።

‹‹በጌጣጌጥ ሥራ በርካታ ሰዎችን አሰልጥኛለሁ፤ ይህም ለእኔ ትልቅ ዕድል ነው›› ያለው አቶ የዝና፤ አዲስ አበባን ጨምሮ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከትግራይና ከደቡብ ክልል የተወጣጡ 230 የሚደርሱ ባለሙያዎችን ማብቃቱንም ይናገራል። ስልጠናውን ያገኙ ሰዎች በሙሉ ማዕድን በሚገኝበት አካባቢ ነዋሪ የሆኑና ማዕድን ቆፋሪዎች መሆናቸውን ጠቅሶ፤ እነዚህ ሰዎች ባገኙት ስልጠና ማዕድኑን ከማውጣት ባለፈ እሴት ጨምረው መጠቀም የሚችሉበት ሰፊ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ይጠቁማል። ባለሙያዎቹ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን በተጨማሪም ማዕድኑ እንዳይባክንና በአግብቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ያመለክታል።

ማዕድን ከመሬት እንደወጣ ሲሸጥና እሴት ተጨምሮበት ሲሸጥ የሚኖረው የዋጋ ልዩነት ሰፊ በመሆኑ በዘርፉ የሚሰጠው ስልጠና የጎላ ጠቀሜታ አለው። በተለይም ማዕድን ቆፍረው የሚያወጡ ሰዎች ስልጠናውን ካገኙ ለዘርፉ የላቀ አበርክቶ አለው። ስልጠናው በዋናነት ማዕድኑ በጥሬው እንዳይሸጥ ያደርጋል። ምክንያቱም፤ አብዛኞቹ የውጭ ዜጎች የከበሩ ድጋዮችን ገና ከአፈር ውስጥ እንደወጡ በጣም በርካሽ ዋጋ ይገዛሉ። ስልጠናው ይህን ማስቀረት ይቻላል። ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትንም ያረጋግጣል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ገበያው አብዝቶ የሚፈልጋቸው ውድ የሚባሉ የከበሩ ድንጋዮች ተመርጠዋል። ከእነዚህም መካከል ኤምራልድ፣ ሳፋየር፣ ሩፒ፣ ቶርማሌ ኦፓልና ሌሎችም ይገኙበታል። እነዚህ የከበሩ ድንጋዮች ዋጋቸው በጣም ውድና ተፈላጊ ናቸው። ስለሆነም ሁሉም ሰው እነሱ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው። በማለት ያመለከተው አቶ የዝና፤ እነዚህ የከበሩ ድንጋዮች ትልቅ ዋጋ የሚያወጡና ተፈላጊ እንደሆኑ ይናገራል። ጌጣጌጥ እና ተዛማጅ ሥራዎች ድርጅትም በዋናነት እነዚህ የከበሩ ድንጋዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው። በተለይም በማዕድን ዘርፍ የተሰማራ ማንኛውም ሰው ስልጠናውን እየወሰደ እሴት ጨምሮ መጠቀም እንዲችል ብርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ያስረዳል።

አቶ የዝና እንደሚናገረው፤ የከበሩ ድንጋዮች ብዙ አይነት ባህሪያትና የዋጋ ልዩነት አላቸው። ድንጋዮቹን አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ ባህሪም አላቸው። ወደ ስልጠና የገባበት ዋናው ምክንያትም ይህ ሲሆን ባለሙያዎች ስለድንጋዮቹ ባህሪያት ማወቅና በጥንቃቄ መጠቀም አለባቸው። ለአብነትም ሳፋየር እጅግ በውድነቱ የሚጠቀስ ሲሆን አንድ ግራም ሳፋየር ከሁለት ሺ እስከ ሶስት ሺ ዶላር ይሸጣል። እሴት ለመጨመር ዕውቀት ይፈልጋል። ስለዚህ በጥንቀቄ መሰንጠቅና መዘጋጀትን ይጠይቃል። ይህ ካልሆነ ግን ይባክናል፤ በዚህ ምክንያት አብዛኞቹ ማዕድናት ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ በጥሬው ይሸጣሉ።

‹‹የማዕድን ሃብት አንድ ጊዜ ብቻ የምናገኘውና መልሰን የማናገኘው ውድ ሃብት እንደመሆኑ በአግባቡና በጥንቃቄ አልምተን ልንጠቀምበት ይገባል›› የሚለው አቶ የዝና፤ መንግሥት ለዘርፉ አሁን ከሰጠው ትኩረት በላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያመለክታል። ምክንያቱም አሁን ላይ ማዕድኑ እየወጣ ያለውም ሆነ እየተሰራ ያለው ባህላዊ በሆነ መንገድ በመሆኑ ውጤታማ መሆን አልተቻለም። ስለዚህ ይህን አሰራር በመቀየር ዘርፉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በስልጠና ተደግፎ በባለሙያ ሊመራ ይገባል ባይ ነው።

የማዕድን ሃብትን ከብክነት ለመከላከል ቴክኖሎጂን መጠቀም አንዱ አማራጭ እንደሆነ የጠቀሰው አቶ የዝና፤ በማምረቻ ድርጅቱ የተለያዩ ማሽኖችን እንደሚጠቀም አጫውቶናል። የሚጠቀማቸው ማሽነሪዎችም በእሱ እጅ የተሰሩ ስለመሆናቸው ይናገራል። ከውጭ የመጣውን አንድ ማሽን በመመልከት መለዋወጫውን ብቻ በመግዛት የውጭ አካሉን በሙሉ በሀገር ውስጥ ጥበበኛ የሆኑ እጆቹ መሰራታቸውን ይገልፃል። ከሰራቸው መሳሪያዎች መካከልም መቁረጫ፣ መሰንጠቂያ ዋናዋናዎቹ ሲሆኑ ሁሉንም የጌጣጌጥ ሥራዎቹንም በእነዚሁ መሳሪያዎች እያመረተ ይገኛል።

‹‹የከበሩ ድንጋዮች ከመሬት ውስጥ ወጥተው ሲሸጡና አፈራቸውን ብቻ አራግፈው ሲሸጡ ያለው ልዩነት ሰፊ በመሆኑ ስልጠና ወሳኝ ነው›› የሚለው አቶ የዝና፤ በአሁኑ ወቅት ስልጠና ላገኙ 36 ባለሙያዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። በአሁን ወቅትም ከ36 ባለሙያዎቹ ጋር የሚያመርታቸውን የጌጣጌጥ ምርቶችም በስፋት ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ከውጭ የሚገባውን ምርት በማስቀረት እንዲሁም ወደ ውጭ በመላክ ጭምር የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ማሳደግ ዋነኛ ዓላማው እንደሆነና ድርብ ጥቅም ያለው መሆኑን ያስረዳል።

ስልጠና በመስጠት በዘርፉ በርካታ ባለሙያዎችን ማፍራት በመቻሉ ደስተኛ እንደሆነ የሚናገረው አቶ የዝና፤ በማምረት ሥራ ውስጥም ስልጠና ስለመኖሩ ይናገራል። አሁን ላይ በዋናነት የሚያመርታቸው ጌጣጌጦች የጆሮ ጌጦች፣ የአንገት፣ የጣት ቀለበት፣ የእግር አልቦና ሌሎችም ይገኙበታል። በቀጣይም የኢትዮጵያውያን ብቻ የሆኑ እንደ መስቀል፣ አሸንክታብ፣ አልቦና ሌሎች ባህላዊ ቁሳቁሶች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ያመለክታል። ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ነገር ያለን ህዝቦች ብንሆንም፤ ያሉንን የተሻሉ ነገሮች አውጥተን መጠቀም አልቻልንም›› በማለት ያክላል።

በተለይም የኢትዮጵያ ብቻ የሆኑና ኢትዮጵያዊ ቀለም ያላቸውን ባህላዊ ቁሳቁሶች ኢትዮጵያዊ በሆኑ የከበሩ ድንጋዮች በማምረት ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ መግባት እንደሚቻል አመልክቷል። በቀጣይም ጉዞው ወዳዛው እንደሆነ የጠቀሰው አቶ የዝና፤ ለዚህም ሰዓሊና ቀራጺ መሆኑ በብዙ እንደጠቀመው አጫውቶናል። የአቶ የዝና ድርጅት ማንኛቸውም በእጅ የሚሰሩ የጥበብ ሥራዎችን ከስዕል ጀምሮ እየሰራ አሁን ላይ ትልቁን ትኩረት ለማዕድኑ በመስጠት በቀን በትንሹ ሁለት ኪሎ ግራም እንደ መስቀል፣ የጆሮ ጌጥ፣ የአንገት ጌጥና ሌሎችንም ያለቀላቸው ምርቶችን እያመረተ ይገኛል።

በልደታ ክፍለ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ በግል ኢንተርፕራይዝ ተደራጅቶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የዝና ጌጣጌጥ እና ተዛማጅ ሥራዎች ማምረቻ ድርጅት፣ በቀጣይ ማስፋፊያ እንደሚያስፈልገውም ያመለክታል። ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ የጌጣጌጥ ማምረቻ መሆኑን ጠቅሶ፣ በቀጣይም ሥራውን በማስፋት ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መሸጋገርና ተመሳሳይ ድርጅቶችን ማስፋፋት ፍላጎቱ እንዳለው ይናገራል። ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ከማስፋፋት ባለፈ የመስሪያ ማሽኖችን ችግር መፍታት እንዲሁም ከውጭ የሚገቡትን ጥሬ ዕቃዎች ማለትም ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት መሆን የሚችሉ ጥሬ ዕቃዎችንና ሌሎች ጌጣጌጥ ለሚያመርቱ አምራች ድርጅቶች ድንጋዩን በቴምፕሌት አዘጋጅቶ የማቅረብ ዕቅድ እንዳለው ያስረዳል።

ለማዕድን ዘርፍ ሙሉ ጊዜውን የሰጠው አቶ የዝና፤ በስራዎቹና በሚሰጣቸው ስልጠናዎች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች የምስክር ወረቀቶችን አግኝቷል። ‹‹የማዕድን ሥራ ከትልቅ ኢንቨስትመንት ይልቅ ትልቅ ልብ የሚፈልግና በፍቅር የሚሰራ ሥራ ነው›› በማለት ይገልፃል።

ለሙያው ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ሥራውን ሲጀምር አንስቶ ያጋጠሙትን በርካታ መሰናክሎች ቱታ ለብሶ አቧራ በማራገፍና በመሥራት ማለፍ እንደቻለ ይገልጻል። ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የተለያዩ ስልጠናዎችን ለሙያው ፍላጎት ላለቸው በመስጠት እንዲሁም መንግሥታዊ ለሆኑ ጥሪዎች ምላሽ በመስጠትና በመኖሪያ አካባቢውም እንዲሁ አቅሙ በፈቀደው ልክ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ነው ያስገነዘበው።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም

Recommended For You