ኃያላን ሀገራት የተፈጥሮ ሀብቷን ለመጠቀም የሚያደርጉት ፍትጊያ ለአሕጉሪቱ ትልቅ ፈተና ሆኗል

አዲስ አበባ፡– ኃያላን ሀገራት የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም የሚያደርጉት ፍትጊያ ለአሕጉሪቱ ትልቅ ፈተና መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ረታ ዓለሙ ገለጹ።

የአፍሪካ የተጋላጭነት ፈተናዎች እና በዓለም አቀፍ ውድድር ውስጥ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ የጥናት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

አምባሳደር ረታ ዓለሙ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ አፍሪካ ልዩ ልዩ ባሕሎች፣ ታሪኮችና በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት ናት።

የዓለም ኃያላን ሀገራት የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም የሚያደርጉት ፍትጊያ ትልቅ ፈተና ሆኗል። በዚህም በአሕጉሪቱ ከሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች ጀርባ እነዚህ እጆች አሉ።

ስለሆነም የአፍሪካ ሀገራት ያለባቸውን ፈተና ለመቋቋም እና የዜጎቻቸውን ሕይወት ለመለወጥ ያላቸውን አቅም እና ሀብት በማስተባበር መሥራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

አባል ሀገራቱና በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትስስር ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና በዚህ በኩል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል። የአፍሪካ ኅብረትም በአሕጉሪቱ ጉዳዮች ላይ ያለውን የመሪነት ሚና ማጠናከር እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ መግቢያ በር ናት ያሉት አምባሳደር ረታ፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ቁልፍ ሚና እንደምትጫወትም ጠቁመዋል።

ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ በበኩላቸው፤ በዓለም ላይ ያለው የጂኦ-ፖለቲካ ፋክክር የፈጠራቸው ፈተናዎች የአፍሪካን የተጋላጭነት ፈተና እንዳባባሰው ገልጸዋል።

በዓለም ላይ ያሉ ጦርነቶች እና ግጭቶች በአፍሪካ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ የወጪ ንግድ እና አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ማሳደራቸውን ተናግረዋል።

ድህነት፣ ግጭቶች፣ የሕዝብ እድገት፣ ተፈጥሯዊ አደጋዎች፣ ጽንፈኝነት እና ሌሎች ፈተናዎች የአፍሪካን ተቋማዊ አቅም ደካማ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኃይል ፋክክሩ የፈጠረውን ፈተና እና ውስጣዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት አበክረው መሥራትና ሚዛን ጠብቀው መሄድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አሕጉሪቱ ዓለም ባለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እሽቅድድም ምክንያት እየፈተነች ነው። ይህም አሕጉሪቱ በሁሉም መስክ ወደፊት እንዳትራመድ እንቅፋት ፈጥሯል። ይህን ችግር ለመሻገር አፍሪካውያን አንድነታቸውንና ትብብራቸውን ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።

የጥናት ጉባኤው የአፍሪካን የተጋላጭነት ፈተናዎች ላይ መፍትሔ ለማበጀት እና በዓለም አቀፍ ውድድር ውስጥ ካሉ ዕድሎች ተጠቃሚ ለመሆን በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦች እንደሚቀርቡበት አመላክተዋል።

የአልጄዚራ የጥናት ማዕከል የጥናት ዘርፍ ኃላፊ ኢዘዲን አብደልሙላ (ዶ/ር)፤ የዓለም ኃያላን ሀገራት በአፍሪካ ውስጥ ፋክክር የሚያደርጉት አሕጉሪቱ ያላትን የተፈጥሮ እና የሰው ኃይል ሀብቶችን ለመጠቀም ነው ብለዋል።

ይህ ፍላጎት ከቅኝ አገዛዝ እና ከቅኝ ግዛት እሳቤዎች የተወረሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ፈተና ዓለም አቀፋዊ ይዘት አለው።

ስለሆነም አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሚነቷ ለማረጋገጥ መሥራት እንዳለባት አመላክተዋል።

ጉባኤው የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እና የአልጄዚራ የጥናት ማዕከል በትብብር ያዘጋጁት ሲሆን፤ “አፍሪካ የተጋላጭነት ፈተናዎች፤ በዓለም አቀፍ ውድድር ካሉ ዕድሎች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ላይ ያተኮረ ነው።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You