-የ2017 ዓ.ም መደበኛ የዳኝነት ሥራ ተጀመረ
አዲስ አበባ:- የፍርድ ቤት አሠራርን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የተጀመሩ ሥራዎችን ወደሙሉ ትግበራ ለማስገባት ትኩረት እንደሚደረግ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለጸ። የ2017 ዓ.ም መደበኛ የዳኝነት ሥራ ተጀምሯል።
መደበኛ የችሎት ሥራን ያስጀመሩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት፤ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎትን በማሳደግ የተጀመሩ ቅንጅታዊ ፕሮጀክቶችም ወደሙሉ ትግበራ ይሸጋገራሉ ብለዋል።
የዳኝነት አገልግሎቱን ለተገልጋይ ምቹ፣ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ የማድረግ ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚተገበር ተናግረዋል።
በዋናነት የዳኝነት ሥራውን ለማቀላጠፍና ተገማች ለማድረግ የሚያስችሉ የተጀመሩና በዚህ ዓመት የሚጠናቀቁ ሥራዎች አሉ ብለዋል።
በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ደረጃ ሦስት ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ስማርት ኮርት ሩም ትግበራ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። የማስቻያ ቦታዎች በቴክኖሎጂ የተደገፉ እንዲሆኑ መረጃዎች በዲጂታል መንገድ እንዲያዙ የሚያስችሉ ግልጽነትንም የሚያረጋግጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም አገልግሎት ማዳረስን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ከአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የሚሠራ ሲሆን በውስጡም በርካታ ነገሮች ማካተቱን ጠቁመው፣ ቻትቦት ያለው እንደሆነና ተገልጋዮች ከሌላ ቦታ ሆነው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዘ ቅሬታ የሚያቀርቡበት፣ ሌላው ደግሞ መረጃ የሚያገኙበት ነው ሲሉ በአብነት ጠቅሰዋል።
የመረጃ ማዕከሎች በሦስቱ ፍርድ ቤቶች ተደራጅተው ባለጉዳዮች በቦታው ተገኝተው መረጃ ያገኙበት የነበረውን አሠራር በዌብሳይትና በተሠራው የሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም መረጃ የሚያገኙበት አሠራር መጀመሩንም ጠቁመዋል።
በፍርድ ቤቱ ኔት ወርክ በመጠቀም አገልግሎት የሚሰጥበት የቪዲዮ ኮንፍረንስ አሠራርን የሚያካትት መሆኑን፣ የምስልና የድምፅ ቀረፃን እንዲሁም ከድምፅ ወደ ጽሑፍ የመቀየሪያ ሥርዓትንም እንደሚያካትትም አመልክተዋል። ትግበራው በሙከራ ደረጃ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲሠራ ቆይቶ ወደትግበራ መሸጋገሩንም አመልክተዋል።
ዘንድሮ ትግበራውን የማስፋፋት ሥራ እንደሚሠራ የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ፤ የማስፋፋት ሥራው በፌዴራል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በክልሎች፤ በሐረሪ ሕዝብ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በሲዳማ ክልሎችና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች የማስፋፋት ሥራ ይቀጥላል ብለዋል።
ሁለተኛው ዋይድ ኤሪያ ኔትወርክ በሚል የሚጠራ መሆኑን በመጠቆምም፤ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በሙሉ በኔትወርክ በማስተሳሰር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ፕሮጀክት ሲሆን ሥራው 78 በመቶ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በፍርድ ቤት የሚሠሩ ሥራዎች ዲጂታል በሆነ መልክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው ሦስተኛው ፕሮግራም መሆኑን የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፤ የተጀመረው ሥራ ዘንድሮ ይጠናቀቃል ተብሎ እንዲታሰብ አመልክተዋል።
በውስጥ አቅም እና ከሌሎች የውጭ አካላት ጋር የሚሠሩ ሥራዎች አሉ ብለዋል። ከአርካይቭ ጋር የተያያዘ በዚህ ዓመት የሚሠራ ሥራ ይኖራል፣ በዋናነት የዳኝነት ሥራውን ለማቀላጠፍ፣ ተገማች ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።
የዳኞችን ተነሳሽነት የሚያሳድጉ ምቹ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ቀልጣፋ የዳኝነት አሠራርን ለማጎልበት ትኩረት እንደሚደረግም ነው የተናገሩት። ዘንድሮ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ልዩ ችሎቶችን የማደራጀት ሥራ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
2016 ዓ.ም የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ በጠቅላይ ፍርድ ቤት 16 ሺህ 636 መዝገቦች ላይ፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት 24 ሺ 853 እንዲሁም የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 135 ሺ 233 መዝገቦች እልባት እንደተሰጠባቸው አመልክተዋል።
በተያያዘ ዜናም፤ በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከትናንት ጥቅምት 01 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ወደ መደበኛ አገልግሎታቸው ተመልሰዋል።
በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በአዋጅ 1234/13 በተደነገገው መሠረት ከነሐሴ 01 እስከ መስከረም 30 ዝግ ሆነው ይቆያሉ።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም