አዲስ አበባ፡- ከ300 ሺ በላይ ለሚሆኑ ግለሰቦች የቢዝነስና አመራር ክህሎት ሥልጠና መስጠቱን የኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ቦሩ ሸና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመ አስር ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በነዚህ ዓመታትም ክህሎትን መሠረት ያደረገ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ለመገንባት እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል።
አቶ ቦሩ፤ ተቋሙ ከሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ጋር እንዲሁም ከአነስተኛ ቢዝነስ ባለቤቶች ጋር የቢዝነስ እይታን ከፍ የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን በተለያዩ ጊዜዎች ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።
የተቋሙ ዋና ዓላማ ግለሰቦች እንዲሁም ተቋማት ችግር የመፍታት ባሕልን እንዲያዳብሩ ማገዝ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ተቋሙ ሥራ በጀመረባቸው ዓመታት ውስጥም ከ 300 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሥራ ፈጣሪዎች ቢዝነስና አመራር ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን መስጠቱን ገልጸዋል።
ያሠለጠናቸው በርካታ ሰዎችም የንግድ ድርጅት መክፈታቸውና በሥልጠናው ተነሳሽነት የንግድ ድርጅታቸውን አስፋፍተው የሥራ ዕድል የፈጠሩ ግለሰቦች በርካታ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ቦሩ ሥራ ፈጣሪዎች ይዘውት የሚመጡት ሀሳብ ወደ መሬት ወርዶ ውጤታማ እንዲሆን ከነሱ ጥረት በተጨማሪ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚዎች ድጋፍን የሚሻ ነው ያሉ ሲሆን ለዚህም ኢንስቲትዩቱ የኢንተርፕርነር ዘርፍ ላይ የሚሠሩ የመንግሥት አካላትንም ሲያሠለጥን መቆየቱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓትም ለ90 የመንግሥት ተቋማት አመራር ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና እየሰጠ ሲሆን ይህ ሥልጠናውም የተቋማት የሥራ ባሕል መቀየሩንና በተለይም በዩኒቨርስቲዎችና በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ ቆመው የነበሩ ወርክሾፖች ወደ ተግባር መግባታቸውን ገልጸዋል።
ተቋሙ ከሥልጠና በተጨማሪም የሀገሪቱ ሥነ ምኅዳር ለሥራ ፈጣሪዎች የተመቸ እንዲሆን የሚያግዙ ኢንሼቲቮችን ማዘጋጀቱና በዛም ኢንቨስተሮችና ስታርትአፖች ትስስር እንዲፈጥሩ በማስቻል ወጣቶች ሃሳባቸው ተግባራዊ ሆኖ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ሲፈጥሩ እየተስተዋለ ይገኛል ብለዋል።
አቶ ቦሩ የማኅበረሰቡን ችግሮች የማቃለልና ሀገርን ሊያሳድግ የሚያችል ትልልቅ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች እየተፈጠሩ መሆናቸውን በመግለጽ እነዚህን ወጣቶች መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም