ታዳጊ ሴቶች እየተጋፈጡት ያለውን ፈተና እንዲሻገሩ ለማስቻል በጋራ መረባረብ ይገባል

አዲስ አበባ፡- ታዳጊ ሴት ልጆች እየተጋፈጡት ያለውን ፈተና እንዲሻገሩ ለማስቻል በጋራ መረባረብና ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይገባል ሲል የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ የታዳጊ ሴቶች ቀን በዓለም ለ14ኛ፤ በሀገራችን ለ13ኛ ጊዜ “ታዳጊ ሴቶች ላይ መሥራት የነገን የተሻለች ሀገር መገንባት ነው” በሚል መሪ ሀሳብ በትናንትናው እለት ተከብሯል።

በበዓሉ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ ታዳጊ ሴት ልጆች እየተጋፈጡት ያለውን ፈተና እንዲሻገሩ ለማስቻል በጋራ መረባረብና ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይገባናል ብለዋል።

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ ፆታዊ ጥቃት፣ የአቻ ግፊት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ሴቶች መድረስ ያለባቸው ቦታ እንዳይደርሱ ምክንያት ናቸው።

የቀኑ መከበር የታዳጊ ሴቶች ድምፅ እንዲሰማ፣ መብታቸው እንዲከበር እንዲሁም ያሉባቸው ስጋቶች ላይ ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የፆታ እኩልነትን ለማስፈን እንዲሁም ሴቶችን ለማብቃት ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ወደፊትም በሴቶች መብት ዙሪያ እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አበክሮ ይሠራል ብለዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሴቶች ፊት ያሉ እንቅፋቶችን ለማንሳት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑንና አሁን ላይ በርካታ ችግሮች ስላሉ በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ታዳጊና ወጣት ሴት ልጆችም አቅማቸውን እንዲያጎለበቱ፣ ጠንካራ ሥነልቦና እንዲያዳብሩ፣ ታላቅ ሕልም ማለምና ትልልቅ ዓላማዎችን ለማሳካት እንዲተጉ መክረዋል።

ሕልማቸውን ከሚያደናቅፉ እና ከትምህርት ገበታቸው ወደ ኋላ እንዲቀሩ ከሚያደርጉ የአቻ ግፊቶችም እንዲጠበቁ አደራ ብለዋል።

የሀገራችን የወደፊት ተስፋ በመሆናቸው ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም ትልቅ ነገርን ማስመዝገብና ማሳካት እንዲችሉ መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሴቶችና ሕፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው፤ ቀኑ ታዳጊዎች ስጋትና ጥያቄያቸውን አንስተው የሚወያዩበት እንዲሁም ጠቃሚ ልምዶችን እርስ በእርስ መለዋወጥ የሚችሉበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።

በበዓሉ ላይ የታዳጊ ሴቶች ፍላጎትና ጥያቄ የተንጸባረቀበት የስዕል ዓውደ ርዕይ የተጎበኘ ሲሆን ሌሎች የኪነጥበብ ሥራዎችና በሀገር አቀፍ ደረጃ የላቀ አገልግሎት በመስጠት አርዓያ የሆኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዕውቅና እንዲያገኙ ተደርጓል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You