የሳይበር ደኅንነትን ቀዳሚ ሀገራዊ አጀንዳ በማድረግ የዲጂታል ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይገባል

አዲስ አበባ፡ የሳይበር ደኅንነትን ከሀገራዊ አጀንዳችን መካከል ግንባር ቀደም በማድረግ ዲጂታል ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አስታወቁ።

“የቁልፍ መሠረተ-ልማት ደኅንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ቃል ለአንድ ወር የሚካሄደው 5ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር በትናንትናው እለት ተጀምሯል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ እንደገለፁት፤ ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ለሳይበር ጥቃት ከተጋለጡ የየትኛውም ሀገር ሉዓላዊነት ለአደጋ ይዳረጋል። በመሆኑም የሳይበር ደኅንነትን ግንባር ቀደም ሀገራዊ አጀንዳ በማድረግ የዲጂታል ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይገባል።

ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ከጥቃት ለመጠበቅም ጠንካራ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችን፣ ሀገራዊ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን፣ በዘርፉ ብቁና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ማልማት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገሪቱን ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ከጥቃት መጠበቅ የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘመን ሉዓላዊ፣ ነፃ እና ጠንካራ ሆና እንድትቀጥል በማድረግ የሀገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መጠበቅ መሆኑንም አንስተዋል።

ቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደኅንነት ሥርዓት እንዲዘረጉና አስፈላጊውን የምላሽና የቅድመ መከላከል ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ፣ ደኅንነታቸው የተረጋገጡ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና በየጊዜው ፍተሻና ግምገማ በማድረግ የሳይበር ደኅንነትን ከጥቃት መጠበቅ ይገባል።

በተጨማሪም የመረጃ ልውውጥ ሥርዓትን በማጠናከር የቁልፍ መሠረተ ልማት ተቋማት የሚያጋጥሟቸውን የሳይበር ጥቃቶችም ሆነ ስጋቶች በቶሎ እንዲያሳውቁ ለማድረግ የሚያስችል የመረጃ መለዋወጫ ሥርዓት መገንባት የሚያስፈልግ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ማሞ እንደ ሀገር የዲጂታል መሠረተ ልማታችንን ስንገነባ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከወሳኝ ሥርዓታችን ጋር ስናዋሕድ፣ የግድ በንቃትና በጥንቃቄ ሊከወን እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያም የዲጂታል ሀብቶቿን የመከላከል እና የመጠበቅ፣ ነፃ የቴክኖሎጂ ውሳኔዎችን የመወሰን እና የዜጎቿን ደኅንነት እና ግላዊነት የማረጋገጥ አቅም ሊኖራት ይገባል። ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ለመጠበቅ እያንዳንዱ የመንግሥት ተቋምም ሆነ ግለሰብ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው፤ የሳይበር ወር መከበር ዋና ዓላማ የማኅበረሰቡን የሳይበር ደኅንነት ግንዛቤን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ መርሐ ግብሮችን ለማከናወን መሆኑን ገልፀዋል።

ዘንድሮም ለ5ኛ ጊዜ የምናከብረው የሳይበር ደኅንነት ወር ዋነኛ ትኩረት የሀገሪቱን ቁልፍ መሠረተ ልማቶች እና ተቋማት የሳይበር ደኅንነት በመጠበቅ የሳይበር ሉዓላዊነታችንን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ እና ፖለቲካዊ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ጥቃት በሚደርስባቸው ጊዜ በዜጎች እንዲሁም በሀገር ብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ጠንካራ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ገልፀዋል።

በሀገሪቱ በ2015 ዓ.ም 6959 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች የደረሱ ሲሆን በ2016 ዓ.ም ወደ 8854 ከፍ ብሏል። ይህም ከዓመት ወደ ዓመት የሳይበር ጥቃት ቁጥሩ እያሻቀበ መሄዱን የሚያመላክት መሆኑን አስታውቀዋል።

በየዓመቱ የሚካሄዱ የሳይበር ደኅንነት የንቅናቄ መርሐ ግብሮች የሳይበር ደኅንነት ተጋላጭነት እና ወቅታዊ የሳይበር ደኅንነት ትኩረት አኳያ ለዜጎች፣ ለተቋማት እንዲሁም ለሚመለከተው ለዘርፉ ማኅበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You