ኢትዮጵያ በያዝነው ወር አሕጉርና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ታስተናግዳለች

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በተያዘው የጥቅምት ወር ለኮንፈረንስ ቱሪዝም አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ የተለያዩ አሕጉርና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ። ከአንድ ሺህ 500 በላይ ዓለም አቀፍ እንግዶች የሚሳተፉበት ኮንፈረንስ እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሠላማዊት ካሣ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በቱሪዝም ዘርፉ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አስመልክተው ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በተያዘው የጥቅምት ወር ለኮንፈረንስ ቱሪዝም አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ አሕጉርና ዓለም አቀፍ ሁነቶች እንደሚጠበቁ ገልጸው፤ ”ከረሀብ ነፃ የሆነ ዓለም መፍጠር” በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሔደው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ አንዱ ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ፈተና የሆነውን ረሀብ በተደራጀ መልኩ መፍትሔ ለመስጠት የዓለም ሀገራት መንግሥታት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች በጋራ የሚመክሩበት እና ልምድ የሚለዋወጡበት መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በበጋ መስኖ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በኩታ ገጠም እርሻ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋትና በሌሎች ንቅናቄዎች በምግብ ራሷን ለመቻል የሠራቻቸውን ሥራዎች በተመለከተ ተሞክሮ ታካፍላለች ሲሉ አብራርተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም፣ በዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ረሀብን ለመዋጋት የተደረገ ዓለም አቀፍ ጥናት ይፋ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

በኮንፈረንሱ ከአንድ ሺህ 500 በላይ ዓለም አቀፍ እንግዶች፣ የሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ30 በላይ የሚሆኑ ተቋማት ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

የአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ኮንፈረንስም ከጥቅምት 9 ቀን እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ያሏትን እቅዶች፣ ከስፖርት ጋር ግንኙነት ያላቸውን የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ እና ሌሎች ሥራዎችን ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል።

ሦስተኛውን የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስንም ከጥቅምት 5 ቀን ጀምሮ እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

ኮንፈረንሱም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሠላምና መረጋጋት ያላትን ሚና የምታሳይበት እና ሀገራት ልምድ የሚለዋወጡበት እንደሚሆን አስታውቀዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፣ ኮንፈረንሱን ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶች በተሰጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች ከሚያደርጓቸው ምክክሮች ጎን ለጎን እንደሀገር የሠራናቸውን በርካታ የልማት ሥራዎች የሚጎበኙ ይሆናል። ይህም የሀገሪቱን የቱሪዝም ኮንፈረንስም ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው።

ኮንፈረንሶችን ለማካሄድ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቂ ዝግጅት መደረጉንና እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በኮንፈረንሱም አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ከማሳየት ባለፈም እ.ኤ.አ በ2023 ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ነጥብ ስምንት ትሪሊዮን ዶላር ከተንቀሳቀሰበት የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ እንድትሆን ዕድል የሚፈጥርላት መሆኑን አስታውቀዋል።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የለሙትን በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ለማስገብኘትም ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጨምረው ገልጸዋል።

መስከረምና ጥቅምት ወር ከፍተኛ የሆነ የቱሪስት ፍሰት የሚኖርበት እና በርካታ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩበት ወር መሆኑን ገልጸዋል።

ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ የአደባባይ በዓላት ለቱሪዝም ዕድገት፣ ለሀገሪቱ የገጽታ ግንባታ፣ የማኅበረሰቡን መስተጋብር እና የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር፣ የኢትዮጵያን ባሕል ለሌሎች የዓለም ሀገራት ለማስተዋወቅና ሌሎች በርካታ ጠቀሜታዎችን አስገኝቷል ብለዋል።

ቱሪዝም ለሀገሪቱ የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ ለማወቅ፣ ውሳኔ ለመስጠት፣ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ፓሊሲ ቀረጻና ስልታዊ እቅድን እውን ለማድረግ እና ሌሎች ጠቀሜታዎችን የሚያስገኝ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ወደ ተግባር መግባቱን አስታውሰዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You