“የአዲስ አበባ የምገባ ማዕከላት ዓለም አቀፍ ተሞክሮን የሚሰጡ ናቸው” -የተለያዩ ሀገራት ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፡– ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ በተለያዩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የምገባ ማዕከላት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሞክሮ የሚሰጡ መሆናቸው ተገለጸ።

የሚላን የከተማ የምግብ ፖሊሲ ስምምነት አባል ሀገራት በመዲናዋ ባሉ የምገባ ማዕከላት ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፤ በከተማዋ ተግባራዊ ከተደረጉ ምርጥ ተሞክሮዎች መካከል ሁሉንም ያማከለው የትምህርት ቤት ምገባ እንዲሁም የማኅበረሰብ ምገባ ፕሮግራም እንደ “ሞዴል” ተወስዶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ማስተማሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ኬኒያዊው ኤሪክ ኦጋሉ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገረው፤ ማዕከላቱ እየሰጡ ያሉት የምገባ አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሞክሮን የሚሰጡ በመሆናቸው አጋር አካላት ይህንን ተግባር ሊደግፉ ይገባል።

ተማሪዎችን በትምህርታቸው ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው ምገባን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን በማሟላት እንደሆነ በመጥቅስ፤ አዲስ አበባ በተለይ በትምህርት ቤት ምገባ የወሰዷቸው እርምጃ የሚደነቅና ለሌችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲል ተናግሯል።

ሴኔጋልን በመወከል በጉብኝቱ የተሳተፈው ጆሴፍ ሳምቡ በበኩሉ በተለያየ የምገባ ማዕከላት በመዘዋወር የተመለከታቸው ተግባራት ከተማዋ ምን ያህል ለማኅበረሰቡ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች እንደሆነ ማስተማሪያ ነው ብሏል። በትምህርት ቤት ውስጥ ያለው የተማሪዎች ምገባ በመማር ማስተማሩ ላይ ትልቅ አዎንታዊ ተፅዕኖ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲል መክሯል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምገባ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምነወር ኑረዲን እንደገለጹት፣ ትምህርት ቤቶችን ሳይጨምር የምገባ ማዕከላት እየሰጡ ባሉት አገልግሎት ከ36 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጐች ተጠቃሚ ሆነዋል።

በትምህርት ቤት ምገባ ከ801ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ አጠቃላይ የግብዓት አቅርቦቱና የትምህርት ቤት ምገባው በጀት ከዘጠኝ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ገልጸዋል። በዚህም ለ16ሺህ እናቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

በዚህ ሥራ አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ዕውቅናዎችን ማግኘቷን የተናገሩት ኃላፊው፤ የምገባ ማዕከላቱ የበርካታ ዜጐችን ሕይወት ከመደጎም አልፎ ለተለያዩ ሀገራት ተሞክሮን የሰጠ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

እኤአ በ2015 የተቋቋመውና 233 ከተሞችን በአባልነት ያቀፈው የሚላን የከተማ ምግብ ፖሊሲ ስምምነት በከተሞች ውስጥ ዘላቂ የምግብ ሥርዓት አተገባበርን ለማስተዋወቅ አልሞ እየሠራ ያለ ነው። ኢትዮጵያም የዚሁ አካል አባል በመሆን በምገባ ሥርዓት ዕውቅናን አትርፋለች።

የፖሊሲ ስምምነት አባል የሆኑና ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የከተማ ተወካዮች፤ አንዲሁም ከጣሊያኗ ሚላን ከተማ ፖሊሲውን የሚመሩ አካላት የአዲስ አበባን ተሞክሮ ለማየት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የምገባ ማዕከላትን በትላንትናው ዕለት የጎበኙ ሲሆን፤ በማዕከላቱ የተመለከቱት ሥራ ለወከሏቸው ሀገራት ትምህርት የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You