አዲስ አበባ፦ ባለፉት ሦስት ወራት በቅርቡ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር በካፒታል ደረጃ 12 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች በዱከም የሚገኘውን የኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ለውጡን ተከትሎ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር በተሠሩ የሕግ፣ የኢኮኖሚና ሌሎችም በርካታ ማሻሻያዎች በየጊዜው ወደኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ ባለሀብቶች ቁጥር ጨምሯል። በዚህም ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ግንባር ቀደም የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆናለች።
የኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ተኪ ምርቶችን እያመረተ ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ሲሆን በውስጡ 153 ድርጅቶች አሉት ከእነኝህ መካከል 95 በመቶ የሚሆነው በቻይና ባለሀብቶች የተያዘ መሆኑን የገለፁት ዘለቀ (ዶ/ር)፤ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ካሉት የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
እንደ ዘለቀ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ከ3ሺህ 300 በላይ የቻይና ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረጉ ሲሆን ይህም ከየትኛውም ሀገር ተቀዳሚ ቁጥር ነው። በዚህም ከ325ሺህ በላይ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
እንዲሁም የክህሎት፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተደረገ መሆኑን በመግለፅ፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከውጭ ለሚመጡ ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን የመፍጠር ሥራን እየሠራ መሆኑን ዘለቀ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩንቤ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደኢትዮጵያ በመምጣት መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ፣ በቂ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
በቅርቡ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ቁጥር ጨምሯል በዚህም ቁጥሩ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር 12 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ዝግ የነበሩ የወጪ፣ የገቢ፣ የችርቻሮና የጅምላ የንግድ የሥራ ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጋቸውን ተከትሎ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ብቻ 72 ጥያቄዎች መምጣታቸውን ያነሱት አቶ ዳጋቶ፤ በዚህም 41 በገቢ፣ 31 በወጭ ንግድ ዘርፍ ለመሳተፍ የቀረቡ ጥያቄዎች ሲሆኑ ከእነኝህ ውስጥ 12ቱ ይሁንታ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ በባለሀብቶች ዘንድ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታትና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለመደገፍ በተጨባጭ መሬት ላይ ወርዶ እየሠራ መሆኑን አቶ ዳጋቶ ገልጸዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም