ታማኞቹ የልማት አርበኞች

መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ ለክብሯ የሚተጉትን፣ ለልማት ቀና የሆኑ ድርጅቶችን ሸልማለች። በአንድነት ፓርክ ግቢ ውስጥ በሚገኘው ሰፊው የግብር አዳራሽ ከፍተኛ ግብር ከፋይ ድርጅቶች የስድስተኛው ዙር የታማኝ ግብር ከፍዮች የምስጋናና የዕውቅና ሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዷል። ታማኝነታቸውን በተግባር ላረጋገጡት ታታሪዎች ምስጋና አቅርባለች።

በዚህ መድረክ በተለያዩ መስፈርቶች 66 ድርጅቶች በፕላትኒየም፣ 165 ኩባንያዎች በወርቅ፣ 319 ኩባንያዎች የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። 20 ድርጅቶች ደግሞ ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት በታማኝነት ከፍተኛ ግብር በመክፈላቸው ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ከእነዚህ በታማኝነት ግብር በመክፈልና በሕግ ተገዥነት ዕውቅናና ሽልማት ከተበረከተላቸው ድርጅቶች መካከል ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አንዱ ነው።

ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ በስሩ ስምንት እህት ኩባንያዎች አሉት። ከእነዚህ እህት ኩባንያዎች መካከል ናሽናል ሲሚንቶ የፕላትኒየምና ልዩ ተሸላሚ ሆኗል። አራት ድርጅቶቻቸው የወርቅ ተሸላሚ ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ የብር ተሸላሚ መሆናቸውን የሚገልጹት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብሩ ወልዴ ናቸው።

“ለዚህ ሽልማት የበቃነው በታማኝነትና በሕግ ተገዥነት ከፍተኛ ግብር በመክፈላችን ነው። በ2016 በጀት ዓመት ብቻ ናሽናል ሲሚንቶ ብቻ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ግብር ከፍሏል የሚሉት አቶ ብሩ፤ ሀገር የምትገነባው በዕርዳታ ሳይሆን ከምታገኘው የውስጥ ገቢ ነው። ይህ ሁሉ የሚታየው መንገድ፣ ባቡር፣ ኤሌክትሪክ፣ የውሃና ሌሎች መሠረተ ልማቶች የተገነቡት በሀገር ውስጥ ገቢ ነው” ብለዋል።

ግብር ከልማት ባሻገርም በኅብረተሰቡ መካከል ፍትሐዊነት የማረጋገጫ መንገድም መሆኑን የሚገልጹት አቶ ብሩ፤ ከዚህ ሁለንተናዊ ጥቅሙ አኳያም ሁሉም ነጋዴም ሆነ ዜጋ በታማኝነት ግብር መክፈል ይኖርበታል ይላሉ።

የእሳቸው ኩባንያም ግብር በመክፈል ታማኝነቱን በአግባቡ በመወጣቱ ለዚህ ሽልማት መብቃቱን ገልጸው፤ ሀገርን ለማልማትና ከድህነት ለመውጣት ተግቶ መሥራትና ከሚገኘው ገቢ በታማኝነት ግብር መክፈል ለከፋዩም፤ ለሀገርም ክብር መሆኑን ነው የገለጹት።

አቶ መልካም አሰፋ የማራቶን ሞተር ኢንጅነሪንግ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው። ድርጅታቸው የ2016 በጀት ዓመት ጨምሮ በተከታታይ አምስት ዓመታት በታማኝነት ግብር በመክፈል የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት አግኝቷል።

“ግብር መክፈል ግዴታ ነው። ይህን ግዴታችንን በታማኝነት ግብር በመክፈል ለሀገራችን ዕድገት የበኩላችንን እየተወጣን እንገኛለን” የሚሉት አቶ መልካም፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ግብር መክፈላቸውን አውስተዋል። ሽልማቱ ትልቅ ክብር እንዳገኘን ተሰምቶናል። ይህን ክብር ለማስጠበቅ አሁንም ብዙ ሥራ መሥራት ይኖርብናል። ወደፊትም በሀገር ልማት ላይ የምናበረክተውን አስተዋፅዖ ለማላቅ ተግተን እንሠራለን ብለዋል።

የሚያገኙትን ትርፍ የሚያውሉት የማስፋፊያ ሥራዎችን በማከናወን መሆኑን አመልክተው፤ ኩባንያቸው በአሁኑ ጊዜም 14 አይነት የሚሆኑ ሞዴል መኪናዎችን ይገጣጥማል። ይህም ከግብር ጎን ለጎን የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሪን በማዳን ረገድ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ነው የነገሩን።

ግብርን በታማኝነት በመክፈልም ሆነ ጥራትና ብዛት ያላቸውን የመኪና ምርቶች በማምረት ለሀገራችን ልማት ትልቅ አስተዋፅዖ ለማበርከት እንሠራለን የሚሉት አቶ መልካም፤ ሁሉም ነጋዴ በወቅቱና በታማኝነት ግብር በመክፈል ለሀገሩ ልማት የበኩሉን ድርሻ ማበርከት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

በ2016 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ግብር ከፍለናል። ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት በታማኝነት ከፍተኛ ግብር በመክፈላችን የፕላቲኒየም ተሸላሚ ስለሆንን ልዩ ተሸላሚ ሆነናል የሚሉት የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክን በመወክል ሽልማቱን ያገኙት አቶ ፍሌራ ድንቁ፤ አንድ ድርጅት በሀገሩ ሠርቶ ትርፍ ካተረፈ ለመንግሥት ግብር መክፈል ግዴታ አለበት ነው ያሉት።

ለሀገር ልማት ግብር በመክፈል የበኩሉን ድርሻ መወጣት ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ መሆኑን አመልክተው፤ ምክንያቱም ከግብር የተሰበሰበው ገንዘብ ለሀገር ልማትና ደኅንነትን ለማስጠበቅ የሚውል ነው። ከዚህ አኳያ የእኛን አርዓያነት ተከትሎ ሁሉም ግብር ከፋይ በታማኝነት ግብሩን መክፈል ይኖርበታል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በ2015 በጀት ዓመት በተካሄደው የአምስተኛው ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች የምስጋናና የዕውቅና መርሐ ግብር ላይ 500 ታማኝ ግብር ከፋዮች ምሥጋና እና ዕውቅና እንደተሰጣቸው ይታወሳል። በ2016 በጀት ዓመት በ6ኛ ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች የምስጋናና ዕውቅና መርሐ ግብር ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 550 ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ዕውቅናና ምስጋና ተበርክቶላቸዋል።

ጌትነት ምሕረቴ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You