አዲስ አበባ፡- ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት እንደሚከበር የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ለኢፕድ በላከው መግለጫ፤ የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ እየተከበረ አስራ ስድስት ዓመታትን አስቆጥሯል። በያዝነው ዓመትም “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ ለ17ኛ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
ስለሆነም የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም በፌዴራል፣ በክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳደር ከተሞች ከሰንደቅ ዓላማ መርሆዎች ጋር ተገናዝቦ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በመላው ሀገሪቱ እንደሚከበር ተገልጿል።
ሰንደቅ ዓላማ የመስዋዕትነት፣ የነፃነት፣ የሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ዓርማ ምልክት ነው ያለው በመግለጫው፤ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሰንደቅ ዓላማ ትልቅ ስፍራና ትርጉም ያለው ነው ሲል አትቷል።
ሰንደቅ ዓላማ በልባችን የታተመ የአንድነታችን፣ የሉዓላዊነታችንና የነፃነታችንን መገለጫ ታላቅ ሀገራዊ ዕሴት በማለት፤ የአብሮነታችን ዓርማ ምልክት ነው ብሏል።
የሀገር ዳር ድንበርን ጥሶ ነፃነታችንንና ሉዓላዊነታችንን ለመውሰድ በየዘመናቱ በተደጋጋሚ የመጣን የውጭ ወራሪ የጠላት ኃይልን እናት አባቶቻችን በተባበረ ክንድ በአንድነት ቆመው መክተውና አሳፍረው የመለሱት ለሀገርና ለሰንደቅ ዓላማ ከሚሰጡት ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት በመነሳት ነው ሲልም አክሏል።
ስለሆነም ሰንደቅ ዓላማችን ተገቢውን ክብርና ገናና ከፍታውን ይዞ ከትውልድ ትውልድ ተላልፎ እነሆ ከአሁኑ ትውልድ ደርሷል ብሎም፤ በማንኛውም ቦታና ጊዜ ለሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብር መስጠትና ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነትና ታሪካዊ አደራም ጭምር ነው ሲል ገልጿል።
የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በየዓመቱ መከበሩ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ ቀጣይነት ብሔራዊ መነቃቃትን ለመፍጠር ትልቅ ትርጉም የሚኖረው መሆኑን በመጠቆም፤ ለሀገርና ለሰንደቅ ዓላማ ያለንን እውነተኛ ክብርና ፍቅር ሁላችንም እንደዜጋ የምንገልፅበትና ለዚህም በሰንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ዕለት ይሆናል ብሏል መግለጫው።
በዕለቱ በፌደራል የመንግሥት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሠራዊት ካምፖች እንዲሁም በየኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ላይ ሰንደቅ ዓላማ በመስቀልና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ይሆናል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም