በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር እያስተዋልን ነው። እነዚህ ምልክቶች ከፍተኛ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትርጉም ባለው በዚህ ቀጣና የአገሪቱን ጥቅሞች ሊጎዱ የሚችሉ በከፍተኛ ጥንቃቄ (በአይነ ቁራኛ) መከታተል እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ በቀይ ባሕርና በኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚታየው ዓለም አቀፍ ውጥረት፣ በሱዳን ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት፣ በአካባቢው ግብፅ እጆቿን ለማስረዘም የምታደርገው ጥረት፣ ሱማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማበላሸት እየሄደች ያለችበት እርቀት ተጠቃሽ ናቸው።
ከዚህ መነሻ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና የተጋረጠውን ስጋት መለየት፤ እንዲሁም ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሁናዊ ሁኔታ መገምገምና በማያወላዳ መልኩ የማሻሻያና የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። እዚህ ጋር አገራችን ከጎረቤት አገራትና በቀጣናው ልዩ ፍላጎት ካላቸው መንግስታት ጋር ከብሔራዊ ጥቅም አኳያ ያላትን ልዩነትና አንድነት በተገቢው መልኩ መለየትም ያስፈልጋል።
የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ እንደሚያምነው አገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ‹‹ልማትና እድገቴን ያረጋግጡልኛል›› ባለቻቸው ሶስት ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጋለች። የመጀመሪያው አጀንዳ ከ14 ዓመት በፊት ተጀምሮ መጠናቀቁ ሊበሰር ጫፍ ላይ የደረሰው የአባይ ግድብ የኃይል ማመንጫ ሙሉ ለሙሉ በማስጀመር ለዜጎቿ ከዚያም አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቷን የምታሳካበት የባሕር በር ይገባኛል ጥያቄዋን በአጭር ግዜ ውስጥ ማሳካት ነው። ሌላኛውና ሶስተኛው ጉዳይ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ቀጣና ሰላምና ፀጥታ በማረጋገጥ ለእድገቷ መሰረት የሆነ አዎንታዊ ከባቢ መፍጠር ነው።
ከእነዚህ ሶስት የአገራችን ቁልፍ ፍላጎቶች አንፃር አሁን በቀጣናው ያለው እንቅስቃሴ ስንገመግም ከፍላጎታችን በተፃራሪ የቆሙ ኃይሎችን እናገኛለን። ከዚህ ውስጥ ቀዳሚዎቹ ግብፅ፣ ሱማሌያ፣ የሱዳን የእርስ በርስ ግጭት እና የተጋጋለው የቀይ ባሕር አለመረጋጋት ላይ እሳት የሚያነዱ ቡድኖች ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ቀደም ካሉት ዘመናት አንስቶ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የመሪነት ሚናዋን ስትወጣ እንደቆየች ይታወቃል። ይህንን ሚናዋን ደካማ የመንግስት መዋቅር ባለባቸው እንደ ሱማሌያ ባሉ አገራት፣ የእርስ በእርስ ግጭት በነገሰባቸው ሀገራት ጭምር (ሱዳን አብዬ ግዛት) ሰላም አስከባሪ ወታደር በመላክ ተወጥታለች እየተወጣችም ነው። ይህንን ድርሻ እየወሰደች የምትገኘው ከምንም በላይ በአካባቢው መረጋጋት ተፈጥሮ ሁሉም አገራት ወደ ልማትና እድገት እንዲገቡና ከኋላ ቀርነት መላቀቅ እንዲችሉ ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ዋንኛ ምንጭም ልማት እና ሰላም ለመሆኑም ይህ ያልተቆጠበ በቀጣናው የምታበረክተው አስተዋፆ በግልፅ ያሳያል። ይሁን እንጂ አጀንዳው ሱማሊያን፣ ጅቡቲን ጨምሮ ከርቀት እጆቿን ለማስረዘም በምትጣጣረው ግብፅ አይን የተወደደ አይደለም።
በዚህ ምክንያት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ለግጭት፣ ለድርቅ፤ ለረሀብ ለጦርነት የተፈጠረ አካባቢ እንዲሆን ተደጋጋሚ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። የግብፅ እጆች በጎረቤት አገራት በውስጥ ፖለቲካ ጭምር እየገባ ይገኛል። የኢትዮጵያን ታላላቅ የልማት አጀንዳዎች በማሰናከል ላይ የተመሰረተው ይህ እንቅስቃሴም ረዘም ላሉ ዘመናት በወዳጅነት ላይ የተመሰረተውን የጎረቤት አገራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማበላሸት ዳር ዳር እያለ ነው። ሱማሊያ ለዚህ ጥረት በጎ ምላሽ እየሰጠች ይመስላል።
ያልተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት የነገሰባት ሶማሊያ በመጠቀም ግብፅ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ በበርካቶች ዘንድ ትችት እንዲሰነዘርባት አድርጓል። ግብፅ ሶማሊያን ተጠቅማ የውክልና ጦርነት ለማድረግ ግልፅ ትንኮሳዎችን እያደረገች ለመሆኑ ምልክቶች አይተናል። ለዚህ ማሳያው መርህ አልባው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ነው። የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳዎች ቀልብሶ ቀጣናው በተለመደው አለመረጋጋት እና ኋላቀርነት አንዲቀጥል ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተቀጥያም ነው።
ኢትዮጵያ ለዚህ ጠብ አጫሪ ድርጊት ብስለት የተሞላበት ምላሽ እያቀረበች ቢሆንም ከድርጊቱ ላይ አይን ሳይነቀል መከታተል ያስፈልጋል። ለእያንዳንዱ የአገራቱ ትንኮሳዎች የሚመጥን ምላሽ ማዘጋጀትም ይገባል። ከሁሉ በላይ ከኢትዮጵያ አልፈው ለቀጣናው ልማትና ሰላም መረጋገጥ የሚበጁ የልማት ስራዎች (እንደ አባይ ግድብና የባሕር በር ፍላጎትን የመሰሉ) ተፈጥሯዊና ሕጋዊ መብቶች በትንኮሳ የማይቀለበሱ መሆናቸውን ማሳየት ይገባል።
የኢትዮጵያ መንግስት ቀጣናው ከልማትና ከሰላም ውጪ የጠብ አጫሪዎች አጀንዳ ማስፈፀሚያ እንዳይሆን ከሚያደርገው ሁለንተናዊ ዝግጅት ውስጥ ቅድሚያ ሊይዝ የሚገባው ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን እስከመጨረሻው አሟጦ መጠቀም ነው። ለዚህም የኢጋድና የአፍሪካ ሀገራት ሁኔታውን በልኩ እንዲያጤኑትና ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ማድረግ ነው። በተለይ ግብፅ ወደዚህ ቀጠና የምትመጣበትን ምክንያት የአካባቢው ሀገራት በአግባቡ ተረድተውት የኢትዮጵያን እውነታ እንዲቀበሉ ማድረግ ያስፈልጋል።
የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ከላይ በዝርዝር ያስቀመጣቸውን ስልታዊ አካሄዶች የኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ እንዲያደርግ የውስጥ አንድነትን ማጠናከር አንደሚያስፈልግ ያምናል።
የባሕር በር ጥያቄም ይሁን ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ዲፕሎማሲ ቁልፍ ጉዳይ ቢሆንም ቀዳሚው ግን ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከርና ሉአላዊ ጉዳዮች ላይ ዘብ ለመቆም መዘጋጀት ነው። በሕዳሴው ግድብ ላይ የታየው ፅናትም ለዚህ በቂ ማሳያ መሆን ይችላል። ቁርጠኛ የሆነ የምሁራንና የፖለቲከኞ የፀና አቋም ግድቡ በድል ለመጠናቀቁ መሰረት ነበር። ይህንን ውስጣዊ አንድነትና የጋራ መግባባት በሌሎች ብሔራዊ አጀንዳዎቻችን ላይ መድገም ይገባናል። የውስጥ ሰላም ማስፈን ተቀዳሚ ተግባር ሆኖ በተጓዳኝ ደግሞ ለቀጠናው ሰላም መሆን ኢትዮጵያ ያላትን ሚና ማሳየት ይጠበቅባታል። የኢትዮጵያ መንግስትም ለዚህ ስልት ስኬታማነት ውጤታማ የሆኑ የውጪ ግንኙነት ማእቀፎች ላይ አበክሮ መስራት አለበት።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ይገባኛል ፍላጎቷን ለማሳካት የምታደርገው ሕጋዊና ስልታዊ አካሄድ ያልተዋጠላቸው፤ የአባይ ግድብ አይናቸው እየተመለከተ መጠናቀቁና የእድገት ምንጭ መሆኑ እንደ ውስጥ እግር እሳት የሆነባቸው፤ በቀጣናው ግዙፍ ኃይል ለመሆን እየተንደረደረች መሆኑ የሚያንገበግባቸው ግብፅን የመሰሉ አገራት ምስራቅ አፍሪካ እንዳይረጋጋ ቀን ከሌት እየሰሩ ነው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን እጆቻችንን ለልማት ስናነሳ፣ ይህንን መሰል እክል አንደሚገጥም ጠፍቶን አለመሆኑን መሰናክሉን አልፈን በምናስመዘግበው ስኬት ማሳየት ይገባናል።
ከሁሉም በላይ በአፍሪካ ቀንድ የኢትዮጵያን የማይናዋጥ አቋም የማስገንዘብ ስራ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ መቀጠል አለበት። በተለይ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላት ቁርኝትም አሁን ካለው ከፍ ማድረግ የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማከናወን ተገቢ ነው። የዲፕሎማሲ ስራው ከንግግርና ከወረቀት የተሻገረ በድል የሚገለፅ ሊሆን ይገባል።
ኢትዮጵያውያን የአባይ ግድብ ግንባታን በፍፁም ፍላጎትና አንድነት ስንጀምር እጃችንን የሚጎትቱ ትርክቶችን በማንሳት የስልጣኔ ጭራ ሊያደርጉን ተረባርበዋል። የመጀመሪያ ያረጀውና ያፈጀውን ‹‹ነባሩን የግብፅ የብቸኛ ተጠቃሚነት ትርክት ‹ሁሉንም ጠቅልሎ የመውሰድ እሳቤ› መጣስ አትችሉም›› የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‹‹በራሳችሁ አቅም የግድቡን ግንባታ እውን አታደርጉትም›› የሚል ነበር። ሁለቱም ትርክቶች መሰረታቸው ውሸት ቢሆንም ለዘመናት በመደጋገማቸው እንደ እውነት ተቆጥረው ነበር።
ይሁን እንጂ በአባይ ግድብ ዙሪያ እጃችንን አሳስረው ለማስቀመጥ ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ ሊሳካ አልቻለም። ኢትዮጵያውያን አይቻልምን በማፍረስ እውን አድርገው ለዓለም አሳይተዋል። ይህ ተግባር ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ከማስደንበሩም በላይ አሁን በቀጣናው ለመቅበዝበዛቸው ምክንያት ሆኗል። በየትኛውም ስሌት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ታላቅ ኃይል ሆና እንዳትወጣ፤ በቀይ ባሕር ላይ ተፅዕኖዋ ጎልቶ እንዳትታይ የሚፈልጉት እነዚህ አካላት የተለያዩ ስልቶችን እየተከተሉ ይገኛሉ። ከዚህ ውስጥ በሱማሊያ በኩል የጀመሩት ረብ የለሽ ሙከራ ተጠቃሽ ነው።
ይህንን ሕልማቸውን በአባይ ገድብ ግንባታ ላይ እንዳደረግነው ሁሉ ዳግም ልናከሽፈው ይገባል። ፈተናዎችን ተቋቁመን ከእቅዳችን ዳር የደረስነው በሕብረታችንና በአንድነታችን መሆኑን መገንዘብ አለብን። በአባይ ግድብ ዙሪያ የማይበጠስ ጠንካራ አንድነት አሳይተን ‹‹ግድቡ የኔም ነው›› ብለን ባንነሳ ለዛሬ ድል ባልበቃን ነበር። ለዚህ ነው ዛሬም በምስራቅ አፍሪካ ሊኖረን ለምንሻው ጠንካራ ክንድ ዳግም ሕብረት የሚያስፈልገን። የጠላቶቻችንን የሴራ ጉንጉን ለመሻገር ቀጣናውን የተረጋጋና ለሁለንተናዊ እድገት ምቹ እንዲሆን ውስጣዊ አንድነታችንን ማጠንከር ይገባናል።
ዛሬም ሌላ የሕዳሴ ፕሮጀክት አለን፤ ይህ አጀንዳ የባሕር በር ባለቤት መሆን ነው። በቀደመው የኢትዮጵያ ታሪክ የባሕር በር የነበርንና በሴራ የተነጠቅን ሕዝቦች መሆናችን ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው። አሁን ህጋዊ፣ ተፈጥሯዊ መብታችንን ተገን አድርገን እውን ልናደርገው ይገባል። ይሁን እንጂ ቀላል ፈተና እየገጠመን አይደለም፤ በቀጣናው ልዩ ፍላጎት ባላቸው አካላት ጉሽሚያ እየደረሰብን ነው። ለዚህ ነው ሕብረታችን የሚያስፈልገው።
የአባይ ግድብ ሲጀመር የነበረ ውክቢያና ማስፈራሪያ ዛሬም በተመሳሳይ ቀጥሏል። ለዚህ ውክቢያ እና ማስፈራሪያ ጆሮ ሰጥተን ቢሆን ግድቡን ከዳር ባላደረስነው ነበር። በተመሳሳይ እየተደረገ ላለው ትንኮሳና ዛቻ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ አይሆንም። ትኩረት አለመስጠት ግን በንቃትና በጥንቃቄ በቀጣናው የሚታየውን ትንኮሳ አለመከታተል እንዳልሆነ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት።
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናች። የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ምሳሌ እና ተፅእኖ ፈጣሪ ሀገር። በአፍሪካና በምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናው ያላት ተፅእኖ ፈጣሪነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ደግሞ የባሕር በር ጥያቄዋ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል። ለስኬቱም ‹‹የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለድርድር የማይቀርብ ብሔራዊ ጥቅማችን›› መሆኑን ግልፅ በማድረግ በጋራ ልንቆም ይገባል። ሕብረታችን ሲፀና፣ አንድነታችን ሲጎለብት ደግሞ ማንኛውም ብሔራዊ ጥቅማችንን መሰረት ያደረገ ጥያቄ ሁሉ መልስ ያገኛል!
ታሪኩ ዘለቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም