ዲላ፦ በጌዴኦ ዞን እያንዳንዱ ዜጋ የሥራ ዕድል እንዲያገኝ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በትኩረት እየሠሩ መሆኑን የዞኑ ቴክኒክና ሙያ መምሪያ አስታወቀ።
የጌዴኦ ዞን ቴክኒክና ሙያ መምሪያ ኃላፊ አቶ አካሉ ሐልቻዬ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በጌዴኦ ዞን አራት ቴክኒክና ሙያ ተቋማት አሉ። እነዚህም በሁለት ዘርፍ ተማሪዎችን ተቀብለው ሙያዊ ሥልጠናና የቴክኒክ እውቀት እየሰጡ ይገኛል። ተቋማቱ የመደበኛ የቴክኒክና የሙያ ሥልጠና እና አጫጭር ሥልጠናዎች ይሰጣሉ።
የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎችን ቢያንስ የአንድ ሙያ ባለቤት በማድረግ እያንዳንዱ ዜጋ የሥራ ዕድል እንዲያገኝ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት በትኩረት እየሠሩ ነው ያሉት አቶ አካሉ ሐልቻዬ፤ ለዚህም በዞኑ 12ተኛ ክፍል የጨረሱ ተማሪዎችን በፍላጎታቸው መሠረት ጥራት ያለው የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና እንዲያገኙ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2016 ዓመተ ምሕረት ማኅበረሰቡ ለቴክኒክና ሙያ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን፣ የመሠረተ ልማት መጓደል እንደነበር አንስተው፤ በተጨማሪም የመብራት፣ የውሃና ሌሎች መሰል ጉዳዮች፣ የማሠልጠኛ ማሽኖች እጥረት፣ ዘመኑን የዋጁ ማሽኖች በኮሌጆቹ አለመኖር ተጠቃሽ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ተናግረዋል።
መንግሥት በክህሎት መር ሥልጠና ላይ ትኩረት እያደረገ ነው። ይህን ተከትሎ በዞኑ ቴክኒክና ሙያ ላይ የሚስተዋለውን ተግዳሮቶችን ለመሙላት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸው፤ በ2017 ዓ.ም ተግዳሮቶቹን ወደ ውጤት ለመቀየር በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ተቋማቱ በአልሙኒየም፣ በእንጨት፣ በብረት እንዲሁም በሌሎች ሥራዎች ላይ የቴክኒክ እና የሙያ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጡ የገለጹት አቶ አካሉ ሐልቻዬ፤ እነዚህ ሙያዎች ገበያው በስፋት የሚፈልጋቸው ዘርፎች ናቸው። በነዚህም የዞኑ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በዘርፉ ያለውን የሰው ኃይል እጥረት ለማሟላት ይረዳል ብለዋል። የሥራ አጥ ቁጥርን በመቀነስም እያንዳንዱ ዜጋ የሥራ ዕድል እንዲያገኝ ያደርጋል ያሉት አቶ አካሉ፤ ይህም የሥራ ፍቅር ያለው ትውልድ እንዲፈጠር ከማድረግ ባለፈ እንደሀገር ያለብንን ድህነትን ለመቅረፍ ይረዳል ነው ያሉት።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2017 ዓ.ም