የኤሌክትሮኒክስ ፊርማን ጨምሮ ሌሎች ረቂቅ አዋጆች ለዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮሚቴዎች ተመሩ

አዲስ አበባ፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኤሌክትሮኒክስ ፊርማን ጨምሮ ሌሎች አምስት ረቂቅ አዋጆችን ለዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

ምክር ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ ስድስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

ምክር ቤቱ የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ፣ የኢትዮጵያ የሕንፃ፣ የእንስሳት ጤና እና ደኅንነት፣ የመድኃኒት ፈንድና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ማቋቋሚያ፣ ጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር፣ የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ነው ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የመራው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሠረት ኃይሌ የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ ማሻሻያ አዋጅ ሕጋዊ ዕውቅና ለመስጠት እና በዲጂታል የፊርማ ሥርዓት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ሚና መብት እና ግዴታ ለመደንገግ የረቂቅ አዋጁ መሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚው ያላትን ዝግጁነት ለማረጋገጥ እና በዘርፉ መልካም ዕድሎችን ለመጠቀም ረቂቅ አዋጁ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ የረቂቅ አዋጁን መሻሻል ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅምና ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት በጥልቀት ሊያየው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የሕንፃ ረቂቅ አዋጅ የአገልግሎት ለውጥ ሥራ የሕዝብን ጤንነትና ደኅንነት ለመጠበቅ እና የሕንጻ ተደራሽነትን ለአካል ጉዳተኞችና ለማኅበረሰቡ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ሚኒስትር ዴኤታዋ አመልክተዋል።

እያጋጠሙ ላሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፤ የግንባታ ጥራት እና የሃብት ብክነት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ግልፅና ምቹ የሆነ የአሠራር ሥርዓትን ለመዘርጋት ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ በከተሞች የሚገነቡ ሕንፃዎች የመሬት የመሸከም አቅም፤ የአካል ጉዳተኞችን ደኅንነት እና የአካባቢን ተፅዕኖ ታሳቢ ያደረጉ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የእንስሳት ጤና እና ደኅንነት ረቂቅ አዋጅ በእንስሳት ሃብት ልማት የሕዝቡን ተጠቃሚነትና በዘርፉ ዓለም አቀፍ የገበያ ተወዳዳሪነትን ለመፍጠር እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የእንስሳት ተዋፅዖ ምርትን ለማሳደግ እና ለማሻሻል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሠረት ገልጸዋል።

ዜጎች በእንስሳት ሃብት ልማት ተጠቃሚ እና ጤናማ የኑሮ ዘይቤ ለመፍጠር ያስችል ዘንድ በሕግ ማዕቀፍ ማካተቱ ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል።

ምክር ቤቱም የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ለግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ መርቷል።

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ፤ የመድኃኒት ፈንድና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እና የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ ለጤና፤ ማኅበራዊ ልማት፤ ባሕልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ መርቷል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 6/2017 አድርጎ ለዝርዝር እይታ ለከተማ፣ መሠረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ መርቷል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ ባደረገው ስብሰባ የምክር ቤቱን 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ቃለ ጉባኤ መርምሮ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You