ጦላይ፦ ውትድርና ለሀገር ሉዓላዊነት፤ ለሕዝቦች ሁለንተናዊ ዕድገት መስዋዕትነት የሚከፈልበት እንዲሁም በጀግንነት ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ የሚጻፍበት የሙያ ዘርፍ ነው ሲሉ በመከላከያ ሚኒስቴር የሎጅስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱራሃማን እስማኤል ገለጹ።
የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በመሠረታዊ ውትድርና ሥልጠና ያሠለጠናቸውን መሠረታዊ ወታደሮች ትናንት አስመርቋል።
ውትድርና ከሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ጉዞ ጋር እያደገ የመጣ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ሠላም ሲባል እራስን አሳልፎ የሚሰጥበትና ለትውልድ የሚተላለፍ የጀግንነት ታሪክ የሚጻፍበትም መሆኑን ሌተናል ጄኔራል አብዱራሃማን በዕለቱ ገልጸዋል።
ሌተናል ጄኔራል አብዱራሃማን አክለውም፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በፅናትና በጀግንነት ግዳጁን በብቃት እየፈጸመ ይገኛል ያሉ ሲሆን፤ ሠራዊቱ በየጊዜው ለሚፈጠሩ ችግሮች ሳይንበረከክ ሕዝቡንና ሀገሩን በፍትሐዊነት እያገለገለ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጀግኖች ልጆቿ አይበገሬነት ለረጅም ዓመታት ሀገርን ከጠላት ተከላክሎና ጠብቆ የማቆየት ታሪክ በዛሬው ትውልድም እየተደገመ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሌተናል ጄኔራል አብዱራሃማን ገለጻ፤ ሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብቃቱን ያረጋገጠ መከላከያ ሠራዊት እየገነባች ትገኛለች። ተመራቂዎች ወደ ተመደቡበት ቦታ በመሄድ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር ግዳጅ ሲቀበሉ በእያንዳንዱ ተልዕኮ ጀርባ የኢትዮጵያ ፍቅርና ክብር እንዲሁም ሉዓላዊነቷ ማስቀደም አለባቸው።
ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶቿ በመከላከል የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ሉዓላዊነቷ ሳይደፈር አቆይቷል ያሉት ሌተናል ጄኔራል አብዱራሃማን፤ ተመራቂዎች በገቡት ቃል መሠረት በትጋትና በፍትሐዊነት ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል ጡምሲዶ ፊታሞ ዱባለ በበኩላቸው፤ ሀገርን ከተለያዩ ጥቃቶች ለመከላከል የወታደራዊ ሳይንስ ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ነው።
ተመራቂዎቹ ለዘጠነኛ ዙር የመሠረታዊ ውትድርና ሥልጠና ሲከታተሉ የነበሩ ሠልጣኞች መሆናቸውን ተናግረዋል። ትምህርት ቤቱ ከአመለካከት ጀምሮ ሁለገብ የሆነ ሥልጠና በመስጠት ለሀገር ሉዓላዊነት የሚተጉ የሠራዊት አባላት እያፈራ ይገኛልም ነው ያሉት።
ወታደር እውቅ፣ ብቁና የታጠቀ ነው ያሉት ብርጋዴል ጄኔራል ጡምሲዶ ፊታሞ ዱባለ፤ በውስጥና በውጭ የኢትዮጵያን ጠላቶች ለመመከትና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የሚዋደቅ ነውም ብለዋል።
ሠልጣኞቹ በመሠረታዊ ውትድርና ማግኘት ያለባቸውን የተግባር እና የንድፈ ሃሳብ ሥልጠናዎችን በተገቢው መንገድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም