በቴክኖሎጂ መታገዝ የሚያስፈልገው የአየር ንብረት ለውጥ

የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን በእኩል ሁኔታ የሚጎዳ እና ለመቆጣጠር የሚያዳግት ክስተት ነው። በተለይ ለአፍሪካ እና ለሀገራችን እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል። ይህንን ጉዳት ለመከላከል እና ለመቅረፍ በየጊዜው ጥናቶች እየተጠኑ በፖሊሲ እና በአሠራር በመንግሥት ተግባራዊ ይደረጋሉ።

በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ታደሰ ኩማ (ዶ/ር) በኢንስቲትዩቱ የሚጠኑ ጥናቶች ዓላማቸው መንግሥት የሚሠራውን የአየር ንብረት ለውጥ ሥራ መረጃ ላይ በመመሥረት ፖሊሲዎች እና አሠራሮች እንዲዘረጉ ማድረግ መሆኑን ይጠቅሳሉ። የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ደግሞ ነባር አሠራሮችን መተካት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በተደረገው ጥናት መሠረት የማይደርቁ ተክሎች ተብለው የተቀመጡ አዝርዕቶች በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት አፈር እና ውሃ መቋጠር ባለመቻል እየደረቁ መሆናቸውን ይጠቁማሉ ብለው፤ ለአብነትም የቡና ተክልን ያነሳሉ። በመሆኑም አምራቾች የቡና ምርትን ትተው ወደ ሌላ ምርት እንዲዛወሩ የሚያደርግ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ይገልፃሉ።

የመንግሥት ፕሮጀክቶች ተብለው ከተቀመጡት ውስጥ የግብርና ዕድገት ፕሮግራም፣ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም፣ የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክቶች እና ሌሎች ኢንቨስትመንቶች ይጠቀሳሉ። እነዚህን ለማሳካት ደግሞ በአየር ንብረት ዙሪያ በነባርነት የቆዩትን አሠራሮች በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ መቀየር እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

አርሶ አደሩ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ድርቅ ሲያጋጥመው ያለው አማራጭ ንብረቱን ሸጦ እራሱን ማዳን መሆኑን በመጥቀስ፤ ነገር ግን የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ሴፍቲኔት በመኖሩ ቢያንስ ሀብታቸውን አቆይተው እንዲያገግሙ እንደሚያደርጋቸው ያብራራሉ።

በመሆኑም በተለይ የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል ያሉት ታደሰ (ዶ/ር)፤ ኢንቨስትመንቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የተፋሰስ ልማት፣ በቂ የግብርና መሠረተ ልማት መዘርጋት እንዲሁም ገበያ ትስስር ላይ ማተኮር እንዳለበት ያመለክታሉ።

በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ጫሊ ይተፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ከእርሻ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቅረፍ ማኅበረሰብን ያማከለ ግብርና እንዲኖር ማድረግ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አረንጓዴ ዐሻራ ለመተግበር የፖሊሲ ጥናቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ይናገራሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ እንዲከሰት ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል የተፈጥሮ መዛባት እና የሕዝብ ቁጥር መጨመር ተጠቃሽ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ይህም የእርሻ መሬት ለመፈለግ ሲባል የደን መጨፍጨፍ የአየር ንብረት እንዲዛባ እንደሚያደርግ ይገልፃሉ።

በመሆኑም የተሻለ ግንዛቤ እንዲፈጠር እና የአየር ንብረት ተፅዕኖ ለመቀነስ ግብርናው ላይ በተለይ ለምግብነት የሚውሉ ማንኛውም ዓይነት ምርቶች ሲመረቱ አካባቢን በማይጎዳ መልኩ መሆን እንዳለበት ያመለክታሉ። በተጨማሪም ከተማ ለማስፋፋት ቤቶች ሲገነቡ የአካባቢ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከተፈጥሮ ጋር በማጣጣም መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ።

አካባቢን መጉዳት ምን ያህል ችግር እንደሚያስከትል ለማኅበረሰቡ በማስተማር ግንዛቤ እንዲያገኙ መሠራት እንዳለበት ጠቁመው፤ በተጨማሪም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በሰፊው አርሶ አደሩ እንዲጠቀም የሚያስችል አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ያብራራሉ። የተፈጥሮ ሥርዓት እንዳይጎዳ ለማድረግ የሚያስችሉ ጥናቶች መሬት ላይ ወርደው ተግባራዊ እንዲሆኑ ተቋማዊ አሠራር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚስፈልግ ያሳስባሉ።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You