ከሊባኖስ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን የመመለስ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፡- በሊባኖስ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን የመመለስ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው እንደገለጹት፣ በሊባኖስ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ የዜጐች ደኅንነት ችግር ላይ እንዳይወድቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ሀገራት በዜጎች ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ተከትሎ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎችን ልዩ ትኩረት በመስጠት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በዚህም በሊባኖስ በተከሰተው ችግር ዙሪያ በዜጎች ላይ የደረሰውን ችግር ለመታደግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

ቀደም ሲል የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ መኖሩን በመጥቀስ፤ የሊባኖስ ችግር ሲከሰት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የቅርብ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ 51 ኢትዮጵያውያንን በዮርዳኖስና በካይሮ በኩል በተደረጉ ሁለት በረራዎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፤ ወደፊትም አጠናክሮ ለማስቀጠል ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በቦታው በመገኘት ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት እየተሞከረ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በሊባኖስ የሚገኘው የኢትዮጵያ የቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤት የምዝገባ ሥርዓት ዘርግቶ በአካልና በዲጂታል ምዝገባ እያከናወነ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ በዚህም መሠረት ከሦስት ሺህ በላይ ዜጎች ተመዝግበዋል። እንዲሁም በሊባኖስ ውስጥ አንጻራዊ ሠላም ወደ አለባቸው አካባቢዎች እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሴቶችና ሕጻናት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ሁሉንም አማራጮች ለመጠቀም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክርና ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ችግሩ የመጣው በኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ አይደለም ያሉት አምባሳደር ነቢያት፤ የበርካታ ሀገራት ዜጎች በሊባኖስ እንደሚኖሩ በመጠቆም በኢትዮጵያ በኩል ከመንግሥት ጥረት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በሊባኖስ ርስ በርስ እየተረዳዳ መሆኑን ተናግረዋል። ተፈናቃዮች የሚጠለሉባቸውን ተጨማሪ ቤቶችን ተከራይተው ዜጎችን ከችግር የመታደግ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት።

በተያያዘ ዜና አምባሳደር ነቢያት እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና ተመርጣለች። በዚህ መሠረት ከ2025 አንስቶ እስከ 2027 ለሦስት ዓመት የምክር ቤት አባል ሆና ትቆያለች ብለዋል።

ይህ በኒውዮርክ በተካሄደ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በተደረገ ድምፅ አሰጣጥ ላይ የተገኘ ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፤ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ 193 ሀገራት የተገኙ ሲሆን 171 ሀገራት ድጋፋቸውን በመስጠት ኢትዮጵያ አባል እንድትሆን መርጠዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አባል በሆነችበት ምክር ቤት ውስጥ የፖለቲካና የሲቪል መብቶች በዓለም ላይ እንዲከበሩና ለታዳጊ ሀገራት የሚሰጡ የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ሥራዎች እንዲያድጉ ትኩረት ሰጥታ ትሠራለች ሲሉ ጠቅሰዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 79ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ሠርታለች ያሉት አምባሳደር ነቢያት፤ በቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በአሁኑ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ብሔራዊ ጥቅሞችን በሚያስከብሩ በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርጓል። በዚህም የኢትዮጵያ ሚና ጎልቶ እንዲወጣ ማድረግ ያስቻለ ሥራ ተሠርቷል ሲሉ ገልጸዋል።

ሞገስ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You