መንግስት ኃላፊነቱን እየተወጣ  ግዴታዎችን ይጠይቅ

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ የመኖሪያ ቤት እጥረት አንዱና ዋነኛው ነው። የከተማዋ ሕዝብ ቁጥር በውልደት መጨመር እና ከተለያዩ አካባቢዎች በሚደረግ ፍልሰት የአዲስ አበባ ነዋሪ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ላይ ይገኛል። ይህ ደግሞ የመኖሪያ ቤት እና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን በማስከተል ላይ ይገኛል።

ከእነዚህ ጫናዎች ዋነኛው ደግሞ የቤት አቅርቦት ነው። ይህንኑ እጥረት ለመቅረፍ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የቤት ልማት ፕሮግራሞችን ነድፎ ወደ ተግባር ገብቷል። በዚህም 130 ሺ የሚጠጉ ቤቶችን ገንብቶ በ14 ዙር ለተጠቃሚዎች አስተላፏል። እስካሁንም በዚህ ፕሮግራም ከ500 ሺ የሚበልጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚዎች ሆነዋል።

ሆኖም የተሰሩት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሰፊውን ሕዝብ የመጥቀማቸውን ያህል ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ አንጻር በርካታ ውስንኖቶች የሚታይባቸው ናቸው። በተለይም በ13ኛ እና 14ኛ ዙር የተላለፉት ቤቶች በርካታ የመሰረተ ልማት ችግር የሚታይባቸው ናቸው። የዚህ ጽሁፍ ባለቤት ነዋሪነቴ ቦሌ አራብሳ ነው። በዚህ ሳይት በ14ኛው ዙር የተላፉት ቤቶች በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው አውቃለሁ።

አብዛኞቹ ቤቶች በአግባቡ የማጠናቀቂያ ስራ ያልተሰራላቸው ከመሆኑም በላይ የውሃ፤ የኤሌትሪክ፤ የፍሳሽ እና የመጸዳጃ ቤት መሰረተ ልማት ጭራሽ ያልተዘረጋላቸው ናቸው። ስለዚህም ቤቶቹ በአሸዋ እና በሲሚንቶ ከመሰራታቸውም ውጭ እንደቤት በርካታ መሰረተ ልማቶች የሌላቸው ናቸው። ይህ ሁሉ ባልተሟላበት ሁኔታ የቤት ባለቤቶች እስከ ጥቅምት 30 ቤታችሁን አድሳችሁ ካልገባችሁ ቤታችሁን ትነጠቃላችሁ መባሉ በብዙዎች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል።

እንደ እኔ መሰረተ ልማት አለመሟላት ቤታችን እንዳንገባ ማነቆ መሆኑ እየታወቀ ‹‹ካልገባችሁ ቤታችሁ ይነጠቃል›› መባሉ ስህተት ነው ብዬ አስባለሁ። መንግስት እወስደዋለሁ ብሎ ያሳወቀው ርምጃ ተገቢ አለመሆኑን ስንናገርም ብዙ አዳማጭም አላገኘንም። አንዳንድ ባላስልጣናት በሚዲያ ቀርበው ሲናገሩ እንደሰማሁትም መንግስት ወደዚህ እርምጃ ለመግባት የተገደደው በሕጋዊ መንገድ ውል የተገባባቸው ቤቶች ሕገወጥነት እየተበራከተባቸው በመምጣቱ ነው። ይህ ትክክል ሊሆን ይችላል። እንደ አዲስ አበባ ነዋሪነታችንም በተለያዩ አካባቢዎች በተዘጉ ኮንዶሚኒየሞች ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉ ሕገወጥ ተግባራትን እንሰማለን።

በተዘጉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የተለያዩ ወንጀሎች እንደሚሰሩም ከጸጥታ አካላት በየጊዜው ከሚተላለፉ መረጃዎች እንረዳለን። የጫት መቃወሚያዎች፤ የሀሽሽ ማጨሻዎች እና አልፎ ተርፎም ከባህል ውጭ ያፈነገጡ ድጊቶች የሚፈጸምባቸው እንደሆኑ እኛም እንረዳለን።

ውል ተገብቶባቸው ባልተገባባቸው ቤቶች ሴቶች ይደፈራሉ፣ ዝርፊያ ይፈጸማል፤ እነዚህና መሰል ነገሮች አሉ። አንዳንድ ቤቶች በጥበቃ የተከራዩም አሉ። ይህንን ለማጣራት እንዲያመችም መንግስት ይህንን ስልት መንደፉ በአንድ በኩል የሚያስኬድ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ይህንን ርምጃ መውሰድ መጀመር የነበረበት የራሱን የቤት ስራ ከተወጣ በኋላ መሆን ነበረበት። እንደ መንግስት ከሁሉም በፊት ሰዎች ወደ ቤታቸው ያልገቡበትን ምክንያት ቆም ብሎ ማሰቡ መቅደም ነበረበት። ዋናው ችግር የመሰረተ ልማት አለመሟላት ነው።

መንግስት መጀመሪያ የቤት ባለቤቶቹን ችግር ሊረዳ ይገባ ነበር። አቤቱታቸውንም ሊያዳምጥ በተገባ ነበር። ነዋሪዎች ወደቤታቸው የገቡት በመሰረተ ልማት አለመሟላት እየተሰቃዩ ያሉበትን ተጨባጭ ችግሮች የተቋሙ አመራሮች በአካል ተገኝተው ማጤን ነበረባቸው።

ትምህርት ቤቶች ሳይገነቡ፣ ጤና ተቋማትም በአካባቢው ሳይኖሩ ልጆችን አፈናቅሎ መሄድ ማህበራዊ ቀውስንና ምስቅልቅልንም ሊፈጥር እንደሚችል መታሰብ ነበረበት። በርካታ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው መግባት እየፈለጉ ያልገቡት ምንም አይነት መሰረተ ልማት ስለሌለ ነው። ስለዚህም መሰረተ ልማት እስኪሟላ በሚል ልጆቻቸውን በተከራዩበት ቤት አካባቢ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች አስመዝግበዋል። አሁን ደግሞ በድንገት እስከ ጥቅምት 30 ካልገባችሁ የሚለው ዜና ሲሰማ ልጆቹ ላይ የሚደርሰው እንግልት እና የትምህርት መቆራረጥ እንደ ሀገር ሊያሳስበን ይገባ ነበር።

ችግር ካልገጠመው በስተቀር ማንም ሰው ቤቱን ትቶ በተከራየው ቤት ተጨማሪ ወጪ እያወጣ መቀጠል አይፈልግም፣ ካልቸገረው በስተቀር አንድ ሰው ቤት እያለው በኪራይ የሚበዘበዝበት ምክንያት አይኖርም። አማራጭ አተው የገቡትም ቢሆኑ በጨለማው ውስጥ እየኖሩ ነው። ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈሉ ውሃ በአህያ እያስጫኑ ለመጠጣት ተገደዋል። በተለይም በመጸዳጃ ቤት ችግር ለከፍተኛ ስቃይ እና የስነ ልቦና ችግር ተጋልጠዋል።

የቤት ችግሩ የባሰባቸው አንዳንድ ነዋሪዎች ቤታቸው የገቡት ሽንት ቤት ቆፍረው መጠቀም ቢጀምሩም በዝናብ ምክንያት ተደፍኖባቸው መጸዳጃ ቤት መጠቀም እንዳልቻሉ ተመልክቻለሁ። አንዳንዶቹም ሌሊት ልጆቻችውን ሲያምባቸው ወደ ተቆፈሩት መጸዳጃ ቤቶች ለመሄድ በጨለማው ድንግዝግዝ እየተቸገሩ መሆኑን ሰምቻለሁ። ብቻ ችግሩ ድርብርብ ቢሆንም መነግስት ግን በዚህ ልክ የተረዳው አይመስለኝም። ትራንስፖርትም ቢሆን ያልተመደበባቸው አካባቢዎች ስላሉ እነዚህ አካባቢዎች መግባት በእጅጉ አዳጋች መሆኑን መረዳት ይገባል።

በተለይም በ14ኛው ዙር በዕጣ የወጡ ቤቶች መሰረተ ልማት አልተሟላላቸውም፣ ውሃም አልገባላቸውም፣ መብራትም የሌላቸው አሉ፣ ግራና ቀኝ የደረጃ መወጣጫ ብረት ያልተሰራላቸውና ጣሪያቸው የሚያፈሱ በርካታ ሕንጻዎች መኖራቸውንም ሄዶ መመልከቱ ብቻ በቂ ነው። በተለይም በክረምቱ በነበረው ዝናብ ምክንያት በርካታ የመኖሪያ ቤቶች በፍሳሽ ተበላሽተዋል።

ስለዚህም መንግስት የቤት ስራውን ሳይወጣ እስከ ጥቅምት 30 ግቡ ብሎ ማስገደዱ ተገቢ አይደለም። በርካታ የቤት እደለኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውል ከፈጸሙ በኋላ ቤቶቹ መሰረተ ልማት ያልተሟሉላቸው በመሆኑ ከቤት ኪራይ አለውጡም። በዚህም ለግለሰብ ቤት ኪራይና በየወሩም ለጋራ መኖሪያ ቤት ኪራይ ዕዳ ለመገፍገፍ ተገደዋል። ይህ ደግሞ አሁን ካለው ኑሮ ውድነት አንጻር በነዋሪው ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።

በእርግጥ መንግስት እስከ ጥቅምት 30 አድሳችሁ ካልገባችሁ ቤታችሁን እነጥቃለሁ ያለው ለየትኞቹ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንደሆነ ግልጽ ባያደርገውም በተለይም በ14ኛው ዙር እጣ የወጣላቸውን የሚመለከት ከሆነ በእርግጥም ውሳኔው በግብታዊነት የተወሰነ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። በዚህ ጉዳይ ላይ በተለያዩ ሳይቶች በተደረጉ ውይይቶችም እስካሁን መሰረተ ልማት የተሟላላቸው ሳይቶች የሉም። በዚህም ምክንያት ወደቤታቸው የገቡ ባለዕድለኞች ቁጥር ከ1 በመቶ አይበልጥም። ስለዚህም መንግስት የሰጠሁትን ማስጠንቀቂያ ማጠፍ አልችልም የሚል እንኳን ቢሆን በተባለው ቀን ውስጥ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ግዴታ አለበት።

ከዚሁ ጎን ለጎን መንግስት ከባለዕድለኞች ጋር ውል ሲገባ ግዴታውን ያስተላፈው ከንግድ ባንክ ጋር ባለው የክፍያ ሁኔታ እንጂ ባለዕድለኞች ቤታቸው ካልገቡ ይነጠቃሉ የሚል ስምምነትም የለም። ይህ ስምምነት በሌለበት ቤታችሁን እነጥቃለሁ ብሎ ማስፈራራት ከሕግ አንጻርም የሚያስኬድ አይደለም።

በውሉ መሰረት ስለቤቱ የሚመለከታቸው ተዋዋዩቹ እንጂ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አይደለም። ኮርፖሬሽኑ የባንኩን ስልጣን መንጠቅም አይችልም። ባንኩ የሚገባው እዳ ሳይከፈለው ከቀረ የሚጠይቅበት ሕጋዊ አግባብ አለው። ሌላው አካል ‹‹ቤታችሁ ስላልገባችሁ ይወሰድባችኋል›› ብሎ መመሪያ ማውጣቱ ሕጋዊ አካሄድንም የተከተለ አይደለም።

እጣ የወጣለት ሰው ወደቤቱ ሊገባ የሚችለው መሰረተ ልማት መሟላቱን አይቶ፣ ቤቱን አድሶ ለመኖር ምቹ ነው ብሎ ሲያምን ነው። የውሃ፣ የመብራት፣ የመንገድ መሰረተ ልማት ሳይሟላ እና ትራንስፖርት ሳይመደብ የገቡ ነዋሪዎች ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን እየተመለከትን ነው። ሌሎችንም በዚህ መልኩ ደፍራችሁ ግቡ ማለቱ የሰውን ችግር አለመረዳት ነው ብዬ አስባለሁ።

በ14ኛው ዙር የወጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ተዘዋውሮ የተመለከተ ሰው በቀላሉ የሚረዳው ነገር የቤቶቹን መሰረተ ልማት ለማሟላት በርካታ ግዜ የሚወስድ መሆኑን ነው። የመንገድ መሰረተ ልማቱ ገና በጅምር ላይ የሚገኝ ነው። የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ገና አልተጀመሩም። የፍሳሽ ማጣሪያ ገና አልተዘረጋም፤ የመብራት ማስተላለፊያ ምሶሶዎች የቆሙ ቢሆንም ገና ኃይል አልተዘረጋላቸውም። ስለዚህም በእያንዳንዱ ቤት እስኪዳረስ በርካታ ግዜያትን ይወስዳል። የውሃ መስመር ገና አልተዘረጋም።

በዚህም ላይ የፍሳሽ ማስወገጃ ትቦዎች ባለመዘርጋታቸው መጸዳጃ ቤቶች በየቦታው ተቆፍረውና በቆርቆሮ ተከበው ይታያሉ። እነዚህ መጸዳጃ ቤቶች መጠናቸው አነስተኛ በመሆኑ የተባለው ሕዝብ ቁጥር ወደየቤቶቹ ቢገባ ሞልተው ለመፍሰስ ቀናት አይወስዱም። ስለዚህም መንግስት ወደቤታችሁ ግቡ ሲል አብረው ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችንም ማጤን አለበት።

በእርግጥ መንግስት ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ አራብሳ ሳይት ላይ የመሰረተ ልማት እንዲሟላ መንገድ እንዲሰራ ወስኗል። ውሃ በሙሉ ኃይል እየገባ ይገኛል። መብራት በብዛት ዝርጋታው ተጠናቅቋል፤ ኃይል መልቀቅ ብቻ ነው የሚቀረው። እነዚህ አራብሳ ላይ ያሉ ነገሮች ናቸው። ሆኖም የተባለው ነገር በተግባር ምን ያህል ይተረጎማል የሚለው የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው።

መንግስት ቃሉ ጠብቆ እስከ ጥቅምት 30 የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎቹን የሚያጠናቅቅ ከሆነ ለነዋሪው መልካም እድል እንጂ መርዶ አይደለም። ሆኖም ለበርካታ ግዜያት መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው ሳይቶች እስከ እዚህ ግዜ ድረስ ይሟላል እየተባለ ቃልና ተግባር ተራርቀው ቆይተዋል። መግለጫ ከመስጠት ውጪ የተባለው ቃል መሬት ላይ ወርዶ መንገዱም ሲሰራ፤ ውሃውም ሲገባ፤ መብራቱም ሲቀጠል ለማየት በርካታ ግዜያትን ሲወስድ ነው የታዘብነው።

ስለዚህም በቤት ኪራይ እየተሰቃዩ ያሉ የቤት ባለዕድለኞች እስከ ጥቅምት 30 ቤታቸውን አድሰው መኖር ይፈልጋሉ። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን መንግስት የተባሉትን መሰረተ ልማቶች ማሟላት ሲችል ብቻ ነው። ቢያንስ ቢያንስ መጸዳጃ ቤት፤ ውሃ እና መብራት መሰረታዊ ስለሆኑ ቅድሚያ ሰጥቶ እነዚህን ሊያሟላ ይገባል። ይህንን ካደረገ በኋላ እስከ ጥቅምት 30 ቤታቸውን አድሰው ባልገቡት ላይ እርምጃ ቢወስድ እንኳን የሞራል መብት አለው ሊባል ይችላል። ያ ባልሆነበት ሁኔታ ‹‹እስከ ጥቅምት 30 ቤታችሁን አድሳችሁ ካልገባችሁ ቤታችሁን እነጥቃለሁ›› ማለት ሰውን ከማስፈራራት ውጪ የሚኖረው ፋይዳ የለም።

አፈወርቅ ከቦሌ አራብሳ

 አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You