ተስፋ ሰጭ ውጤቶች የታዩበት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አፈፃፀም

ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ ወዲህ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት፣ መንግሥት ለሀገሪቱ መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ ያስችላሉ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል። ከእነዚህ መርሃ ግብሮች አንዱ፣ ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Economic Reform Program) ነው።

የመርሃ ግብሩ ዓላማ አምራች የሆነውን የሠው ኃይል የሚሸከም የሥራ እድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ በመፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብ ነው። የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ስራ አመቺነት ማሻሻያ መርሃ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብይት ስርዓት ጋር ዘመናዊ ትስስር ለመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን የተላለፈውን ውሳኔ ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል ናቸው።

በ2011 የበጀት ዓመት ወደ ትግበራ የገባው የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም፣ ብዙ የፖሊሲ ሐሳቦችን በውስጡ ያካተተ እና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ዓላማዎችንና ግቦችን ማሳካት አስችሏል። ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማረም፣ የዕዳ ጫናን ለማቃለል፣ የሀገር ውስጥ የማምረት ዐቅምን ለማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮችን ለማስፋፋት፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለማረም በተደረገው ጥረት ውጤቶች መገኘታቸውን መንግሥትም ገልጿል። በቅርቡ የጸደቀው ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ቀሪ የማክሮ ኢኖኮሚ ማሻሻያ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ግብዓት እንደሚሆን ታምኖበታል።

እነዚህ የፖሊሲና የሕግጋት ማሻሻያዎች እና ሕጋዊ ማዕቀፎቹን መሰረት በማድረግም የተወሰዱ ተግባራዊ እርምጃዎች ኢኮኖሚው ወደተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሸጋገር አዲስ ተስፋ ፈንጥቀዋል። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ ገብታለች።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ በአራት ምሦሦዎች ላይ የተገነባ ነው። እነዚህም ምሦሦዎች የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን እና ዘላቂነትን የሚደግፍ ዘመናዊ እና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ መመሥረት፤ ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢ እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ዐቅምን ማጠናከር እና ጥራት ያለው አገልግሎትን በብቃት ለማቅረብ የመንግሥትን ዐቅም ማሳደግ የሚሉት ናቸው።

በመንግሥት ይፋ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ማብራሪያ እንደሚያሳየው፣ የፕሮግራሙ ዋና ዋና ቁልፍ ዓላማዎችና ግቦች የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከል እና የረጅም ጊዜ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጉድለት ችግሮችን መፍታት፤ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን በማዘመን የዋጋ ንረትን መቀነስ፤ የዕዳ ተጋላጭነትን በመፍታት እና የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶቻችንን በሀገር ውስጥ ዐቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል መፍጠር፤ የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነት፣ ተወዳዳሪነትና ጤናማነት ማጠናከር እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ጠንካራ፣ አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባት ናቸው።

ማሻሻያው ለጠንካራ፣ በግሉ ዘርፍ ለሚመራ፣ ሁሉን አቀፍ ለሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት እንዲሆን ታቅዷል። ፕሮግራሙ በሚተገበርበት ወቅት ከፍተኛ እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ባለ ነጠላ አሐዝ የዋጋ ግሽበት ይኖራል ተብሎ ግብ ተጥሏል። ከዚህ በተጨማሪም የማሻሻያው ትግበራ የውጭ ምንዛሪ መዛባትን በማስተካከል፣ የፋይናንስ ዘርፉን ይበልጥ በማጠናከር፣ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የታክስ ገቢን በማሳደግ፣ የመንግሥትን ኢንቨስትመንት ውጤታማነት በማሻሻል፣ የባንክ ዘርፍን ተወዳዳሪነትና ጤናማነት በማጎልበት እና የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓት የመገንባትን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት እንደሚያስችል ተገልጿል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋና ዋና የፖሊሲ እርምጃዎች በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት፣ የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ፣ በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት፣ የልማት ፋይናንስ ዕድሎች እና የመንግሥት ዕዳ አስተዳደር ማሻሻያ ናቸው። የማሻሻያ መርሃ ግብሩ በእነዚህ የፖሊሲ እርምጃዎች አማካኝነት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ታምኖበታል።

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣ የታመነበት ይህም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የሁለት ወራት አፈፃፀም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ሰሞኑን ተገምግሟል። በግምገማው ላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያው የታለሙለትን ግቦች ማሳካት በሚያስችለው ቁመና ላይ እንደሚገኝና ተስፋ ሰጭ የሆኑ ውጤቶች እየተመዘገቡበት እንደሚገኝም ተገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንደተናገሩት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው በተረጋጋ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል። መሰል የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያን ከተገበሩ ከብዙ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር፣ በተረጋጋና ስኬታማ በሆነ መልኩ እየተፈፀመ ነው። የተረጋጋና ጫና የማይፈጥር የገበያ ዋጋ እና ማኅበራዊ ሁኔታ አለ።

የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ሲተገበሩ ብዙ ጫናዎች መከሰታቸው የሚጠበቅ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አህመድ፣ ኢትዮጵያ የተገበረችው ማሻሻያ ግን ከብዙ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር የተረጋጋ አፈፃፀም ያሳየ እንደሆነ ይገልፃሉ። ለአብነትም ባለፉት ሁለት ወራት የነበረው የዋጋ ንረት ሁኔታ የተፈራውን ያህል እንዳልሆነና በአንዳንድ እቃዎች ላይ ጭማሪ ቢታይም የአብዛኞቹ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ዋጋ የተረጋጋ ሆኖ መቀጠሉን ያስረዳሉ።

‹‹የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አንዱ ትኩረት ገቢን ማሳደግ ነው። ገቢን ለማሳደግ አዲስ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። የገቢ አሰባሰብ ተሻሽሏል። ገቢን የማሳደግ ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል። ከታክስ ከፋዮች ጋር ውይይቶች ተደርገዋል፤ ከልማት አጋሮች ጋር ውይይቶች ተደርገዋል፤ ሁሉም የማሻሻያው ትግበራ ስኬታማ እንዲሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል›› ሲሉ አስታውቀዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ‹‹ከእነዚህ አጋሮች የበጀት ድጋፎች ይጠበቃሉ። በቀጣይ ወራት የውጭ እዳ እፎይታ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፤ ይህ እፎይታው ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል። የዓለም የገንዘብ ድርጅት የባለሙያዎች ቡድንም ባካሄደው ግምገማ ማሻሻያው በተሳካ ሁኔታ እየተተገበረ እንደሆነ አረጋግጧል›› ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ የሀገር ውስጥ እዳ ሽግሽግን በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተለያዩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አበድሮት የነበረውንና እስካሁን ሳይከፈል የቆየውን ብድር እና የካፒታል እድገት ጭማሪ እስከ 900 ቢሊዮን ብር ቦንድ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ለንግድ ባንክ ተሰጥቷል። ይህ እርምጃ በንግድ ባንክ ላይ ይመጣ የነበረውን ጫና በመቀነስ የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፤ የባንኩን የካፒታል አቅም ያሳድጋል። ከዚህ ቀደም ተከማችተው የነበሩ ብድሮች ወደ ረጅም ጊዜ ቦንድ እንዲቀየሩ ተደርጓል። ይህም የሀገር ውስጥ የብድር ሽግሽግን ጤናማ ያደርጋል።

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ባለው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ጫና እንዳይፈጥር ይህን የኅብረተሰብ ክፍል የመደገፉ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትኩረት ይደረጋል፤ ዝቅተኛ ገቢ ባለው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ያተኮረ፣ ከመስከረም ወር ጀምሮ ታሳቢ የሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ (ለኑሮ ድጎማ የሚሆን) በካቢኔው ጸድቋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ስራዎችን ከማጠናከር ጎን ለጎን በሴክተር የልማት ስራዎች ላይም ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል። ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትን የመቆጣጠር ተግባር በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ነው። ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ ምርትን በማሳደግ እንዲሁም የምርት ስብጥርን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ስራ መሰራት እንዳለበት በግምገማው ተመላክቷል።

ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ዋና ዋና የፖሊሲ ርምጃዎች መካከል አንዱ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን (Floating Exchange Rate) ስርዓት ትግበራ ነው። ይህ የፖሊሲ እርምጃ የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ እና የሀገሪቱን የንግድ ሥርዓት ከአጎራባችና ከአቻ ሀገራት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በዚህ ረገድ ማሻሻያው የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝትና ክምችት እያሳደገው እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገልጿል።

የባንኩ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ እንዳስረዱት፣ ማሻሻያው ከተተገበረ በኋላ የተገኙ ውጤቶች ማሻሻያው በሌሎች ሀገራት ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ ውጤታማ የሆነና ምሳሌ መሆን እንደሚችል አመላካች ናቸው። ከማሻሻያው ትግበራ በፊት በባንኮችና በትይዩ (ጥቁር) ገበያው መካከል ያለው የምንዛሬ ዋጋ ልዩነት 100 በመቶ ነበር፤ አሁን ልዩነቱ ከሦስት በመቶ በታች ወርዷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁለቱ ገበያዎች መካከል ያለው ልዩነት ከ10 በመቶ በታች ከሆነ ማሻሻያው የተሳካ እንደሆነ ይቆጠራል።

በወጭ ንግድ ረገድ፣ በተያዘው የበጀት ዓመት መስከረም ወር የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ባለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ከተመዘገበው የውጭ ምንዛሪ የ53 በመቶ ብልጫ አለው። ባለፈው የበጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከውጭ የተላከው ገንዘብ (Re­mittance) ከዘንድሮው የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ጋር ሲወዳደርም እንዲሁ በ145 በመቶ ጨምሯል። ይህም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ ግኝት በየጊዜው እየጨመረ እንደሆነ ያሳያል።

በወርቅ ምርት ላይ የታየው መሻሻልም የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ማሻሻያው ውጤት ነው። ባለፈው የበጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከወርቅ የወጭ ንግድ የተገኘው ገቢ 58 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር፤ በዘንድሮው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የተገኘው ገቢ 488 ሚሊዮን ዶላር ነው። የዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ገቢ ካለፈው የበጀት ዓመት ገቢ (255 ሚሊዮን ዶላር) የበለጠ ነው። በሁለት ወራት ውስጥ በባንክ ስርዓት ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት በ80 በመቶ (በብሔራዊ ባንክ በ153 በመቶ እና በግል ባንኮች በ29 በመቶ) አድጓል።

‹‹በማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያው አዲስና ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ እየተተገበረ ይገኛል። ይህ ፖሊሲ በመተግበሩ የዋጋ ንረት እየቀነሰ ነው። የዋጋ ንረቱ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 29 በመቶ ዘንድሮ ወደ 17 በመቶ ቀንሷል። ይህ ስኬት የተገመዘገበው መንግሥት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚሰራቸው ስራዎች በተጨማሪ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረጉ ነው።›› ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ስራ የፋይናንስ ስርዓቱ በተገቢው መንገድ እንዲመራ ማስቻል ነው። በውጭ ምንዛሬ፣ በብድር አሳጣጥ ረገድ የሚታዩ ተገቢ ያልሆኑ አሰራሮችን ለማስተካከል ባንኩ በቀጣይ ጊዜያት ጠንካራ የቁጥጥር ስራዎችን ይሰራል፤ በነዚህ ሕገወጥ ተግባራት ላይ በተሳተፉ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃም ይወስዳል። ብሔራዊ ባንክ የጀመረውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አጠናክሮ ይቀጥላል።

የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ፖሊሲን መሰረታዊ በሆነ መልኩ ያሻሻለ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የነበረውን ስር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚፈታ ወሳኝና ታሪካዊ እርምጃ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ማሞ፣ ማሻሻያው በታሰበውና በተረጋጋ መልኩ ስኬታማ ሆኖ እየተተገበረ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው፣ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያው ቀደም ብሎ ዝግጅት ሲደረግበት እንደቆየ ጠቁመው፣ ማሻሻያው ከሚያስገኘው ጥቅም ባሻገር ሊያስከትለው ስለሚችለው ጫናም ቀደም ብሎ ስለታሰበበት እስካሁን የተፈራውን ያህል ጫና እንዳልፈጠረ ይገልፃሉ። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሁኔታና የመንግሥት ወጭ አስተዳደርና አመዳደብ ከሌሎቹ ሀገራት የተለየ በመሆኑ መሰል ሪፎርሞች በሌሎች ሀገራት ያስከተሏቸው ጫናዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ጎልተው እንዳልታዩ ያስረዳሉ።

‹‹ሪፎርሙ ለዘርፎች ትልቅ ማነቆ የሆኑትን የግብዓት ችግሮች ይፈታል። በባለሃብቶች ተደጋጋሚ ጥያቄ ከሚነሱባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የወጭ ምንዛሪ እጥረት ነው። ሪፎርሙ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ነው። በግሉ ዘርፍ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት ለዘርፎች እድገት ወሳኝ ናቸው። ኢንቨስትመንት ሲጨምር ምርትና ምርታማነት ያድጋል። የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ውጤታማነትና ጥራት ከሚለካባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የዜጎች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ነው። ማሻሻያው ኢንቨስትመንትን ያስፋፋል፤ ኢንቨስትመንት ሲስፋፋ የስራ እድል ይፈጠራል። የስራ እድል ሲፈጠር ዜጎች በኢኮኖሚው ውስጥ ተሳታፊ ይሆናሉ። ይህም ኢኮኖሚው ውጤታማና ጥራት ያለው እንዲሆን ያደርገዋል›› በማለት የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢኮኖሚው ላይ ጉልህ አዎንታዊ ለውጥ እንዲኖር እንደሚያደርግ ዶክተር ፍጹም ያብራራሉ።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You