ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የአንዳንድ ታላላቅ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች አባልም መስራችም ናት። የድርጅቶቹ አባል መሆኗም ዓለም አቀፋዊ ትስስሯን አጠናክሮላታል። ሕግጋቶችን በመቅረጽ አወንታዊ አስተዋጽኦ አበርክቶላታል።
ይህ ማዕቀፍ ሰላምን፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እና በሀገሮች መካከል ትብብርን በማጎልበት ተኪ የሌለው ሚና ይጫወታል። እናም ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም በተሻለ ሁኔታ ለማስከበር በምታደርገው ጥረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚያካሂደው ጉባኤን ጨምሮ የዓለም አቀፍ ድርጅት መድረኮችን መጠቀሟን መቀጠል ይገባታል።
ሰሞኑን ተ.መ.ድ. ባካሄደው 79ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ኢትዮጵያን የወከለው ልዑካን ቡድንም ይህን ማድረጉ ይበል ያሰኛል። አሁን የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ቀደም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጉባኤው ባደረገው ተሳትፎ ከጉባኤው ጎን ለጎን በተካሄዱ ውይይቶች የኢትዮጵያን ጥቅሞች በሚያስጠብቁ፣ በናይል ተፋሰስ ፍትሃዊ እና እኩል ተጠቃሚነት ዙሪያ፣ ሁለትዮሽን በሚያጠናክሩና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኀንነት ላይ ያተኮሩ እና መሰል ውይይቶች አካሂዷል።
ከውይይቶቹ መካከል ኢትዮጵያ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን ጥረት የሚመለከተውን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል። ሶማሊያን በተመለከተም ኢትዮጵያ ሽብርተኞችን በመዋጋት ረገድ በምታደርገው የተጠናከረ ጥረት ዙሪያ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፤ በሶማሊያ የሚደረገው የአዲሱ የህብረቱ ሽግግር ተልእኮ (አትሚስ) የሚኖረው የኃይል ሥምሪት ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ የስምሪቱ ማዕቀፍ በጥንቃቄ መሠራት እንዳለበት በማሳሰብ ያነሱት ነጥብ ወሳኝ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት በሰላምና በመረዳዳት የሚገለጽ፤ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ጎረቤቶቿ ሰላም ካልሆኑ ኢትዮጵያ ሰላም ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት ከባድ ፈተና ይዞ መምጣቱ አይቀርም።በመሆኑም በአፍሪካ ቀንድም ሆነ ከዚያ ባለፈ የምታደርገው የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሰከነና መርህን መሠረት ያደረገ ነው። ችግሮች ሲከሰቱ የጋራ መፍትሔ ላይ ያተኮረ መሆኑም የሚበረታታ ነው።
በሶማሊያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አስተማማኝ ሰላም እና ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዳይኖር ምክንያት ሆኗል። ለዓመታት በጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን አልሸባብ የምትታመሰው ሶማሊያ ደህንነቷን በጎረቤት ሀገራት ወታደራዊ ድጋፍ ለማረጋገጥ አስገድዷት መቆየቷ ይታወቃል። ለዚህም የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ባለፉት ዓመታት በሶማሊያ ውስጥ ተሰማርቶ የሰላም ማስከበር ተልእኮ ሲያካሂድ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ወታደሮቿን ያሰማራችበት ይህ ተልእኮ ተልእኮውን አጠናቆ ሲወጣ፣ አዲስ በተቀየረው ስሙ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)የፀጥታ ሁኔታውን የሶማሊያ መንግሥት እንዲረከብ እንደሚያደርግ መገለጹ ይታወሳል።
የሶማሊያ መንግሥት አዲሱን ተልእኮ አስመልክቶ የሚያወጣቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ አዲሱ የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀጣና ስጋት ይዞ ብቅ ብሏል። በመሆኑም በሶማሊያ በቀጣይነት የሚሰማሩትን የሰላም አስከባሪዎች በተመለከተ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባግባቡ ሊያጤኑት እንደሚገባ እሙን ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ወታደሮቻቸውን ያሰማሩ ሀገራት ተደጋጋሚ ጥሪዎችና አስተያየቶች እያቀረቡ ይገኛሉ።
ቀጣናው ሊተነበይ ወደማይችል ውጥረት ውስጥ እንዳይገባ መደረግ ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ አስቀድሞ
መዘጋጀት እንደ ሀገርም እንደ አህጉርም የሚጠበቅ ተግባር ነው። በተለይም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለቀጣናው ሰላም መስፈን ሲሉ ልዩ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ ዛሬ ላይ የሚሰጠው ማሳሰቢያና የምናየው አስጊ ሁኔታ የቀጣናው ደህንነት ዘላቂነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት በመሆኑ ነው።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮቿን እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ልዑክ አሰማርታ ኃላፊነቷን በመወጣት ላይ ትገኛለች። ለሶማሊያና ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ መስፈን፣ ለጋራ ዕድገት እና በሕዝቦች መካከል ያለውን የጠበቀ የእርስ በርስ ትስስር ይበልጥ እንዲጎለብት ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግም ቆይታለች። ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
ስለሆነም የሶማሊያን ሰላምና ደህንነትንም ሆነ የቀጣናውን ደህንነት ለማስጠበቅ በጥልቀት የታሰበበት እና በቂ ዝግጅት የተደረገበት ስምሪት መስጠት ተገቢ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። ይህ ሳይሆን ቢቀር የአካባቢው ሰላም ወደማይቀለበስ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ አካባቢውን የትርምስ ማእከል እንዳያደርገው ያሰጋል፤ ለዚህም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይሻል። በጊዜው ደርሷል ሩጫ ሶማሊያም ስራውን ለመረከብ እየተዘጋጀችበት ይመስላል፤ ይህ ግን ተገቢ ዝግጅት ይሻል።
አካባቢው የተረጋጋ ካልሆነ ለአክራሪዎች እና ሽብርተኞች መመላለሻ በመሆን የቀጣናው ሰላም ሌላ ገጽታ እንዲላበስ እድል ይፈጥራል። ይህ ደግሞ እየታየ የነበረውን የሰላም ጭላንጭል ተስፋ ውጦ አካባቢውን የትርምስ ቀጣና ሊያደርገው ይችላል። በመሆኑም ሁኔታው ውሳኔውን ለመተግበር ከመቸኮል ይልቅ ተረጋግቶ ማሰብን ይጠይቃል።
ለዚህም ይመስላል ኢትዮጵያ እና ሌሎች ወታደሮቻቸውን በአፍሪካ ህብረት ተልእኮ ስር በሶማሊያ ያሰማሩ ሀገራት በተደጋጋሚ ሲያሳስቡት የቆዩት። በሶማሊያ የሚገኘው የህብረቱ ተልዕኮ ተልእኮውን አጠናቆ የፀጥታ ስራውን ለሶማሊያ መንግሥት ከማስረከቡ በፊት ያሉ ነበራዊ ሁኔታዎችን መቃኘት ያስፈልጋል። ማሳሰቢያው በዚህ ጊዜም ችላ መባል የለበትም፤ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋልና ጊዜ መሰጠት አለበት።
ቀደም ሲል በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ቡድኖች አማካይነት በአሸባሪ ቡድኖች ላይ የተመዘገበው ድል ለቀጣናው እፎይታ የሰጠ፣ መተማመን እንዲነግስ ያደረገ ነው። ይህንን ማስጠበቅ ተገቢም ትክክልም ይሆናል። የተገኘውን አበረታች ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉ እና የሚቀለብሱ ድርጊቶች ሊፈጠሩ አይገባም።
ኢትዮጵያ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ከሶማሊያ ሕዝብ እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል ስታደርግ የቆየችውን ተግባር መቀጠል ይኖርባቸዋል። የቀጣናው ሁኔታ የኢትዮጵያም ጉዳይ እንደመሆኑ የሚያሰጋ ነገር ከተፈጠረ ኢትዮጵያውያን እጃቸውን አጣጥፈው ይመለከታሉ ተብሎ አይታሰብም።
ኢትዮጵያ ሁኔታውን በዝምታ እንድታልፍ የመፈለግ የአንዳንድ ወገኖች አዝማሚያ ከአጉል ብልጠት የሚመነጭ ነው። ከሶማሊያ ጋር ያለው ጉርብትና ለልማቱ የተሻለ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችለው በሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት ሲኖር እንደመሆኑ ለሶማሊያም ሆነ ለአካባቢው ሰላም መስፈን ወሳኝ በመሆኑ ለተግባሩም መተባበር ይገባል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ብሄራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ በንቃት መከታተል ይኖርባታል። ይህንን የሚመለከተው የደህንነት አካል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆን አለበት። ለቀጣናው ሰላም ከውሳኔው በፊት ደግሞ፣ ደጋግሞ ማጤን ይጠይቃል። ከሁሉም በላይ ግን ከአትሚስ በኋላ ያለው ሁኔታ እና ዝግጅት መቃረቡን ተከትሎ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተገቢ ምላሽ እና ወሳኝ ርምጃ እንደሚወስዱ ይጠበቃል እላለሁ።
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም