አዲስ አበባ:- ክህሎትና ፈጠራን መሠረት ያደረገው፣ ወደ ሥራ ፈጠራ እና ተወዳዳሪነት ባህል የሚያሸጋግረው የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ መርሃ ግብር ዘንድሮ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ታዬ እንደገለጹት፤ ቀጣሪ መንግሥት ነው የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በመቀየር የሪፎርም ማእከሉ ክህሎትና ፈጠራን መሠረት ወደ አደረገ ትግበራ ሽግግር ይደረጋል፡፡
የሪፎርሙ ዓላማ የሥራ ፈጠራ እና የተወዳዳሪነት ባህልን እውን ማድረግ ነው፤ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም ጥናቱ በመጠናቀቁ በ2017 ዓ.ም ወደ ትግበራ ይገባል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው የምትገኘውን ፈጣን እና ተከታታይነት ያለው እድገት ለማስቀጠል የተለያዩ የለውጥ መሳሪያዎችን ተግባራዊ በማደረግ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ከለውጥ መሳሪያዎች ውስጥ ዋነኛው የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ መርሃ ግብር ነው፡፡ ከመርሃ ግብሩ አምስት ንዑሳን ዘርፎች መካከል የሰው ኃይል ማሻሻያ ንዑስ ዘርፍ ውስጥ አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በአዲስ መንፈስ የተነቃቁ እና የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሱ የመንግሥት ሠራተኞችን በመመደብ አጠቃላይ የሲቪል ሰርቪስ አሠራርን ለማዘመን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
የሪፎርም ማእከሉ ቀጣሪ መንግሥት ነው የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በማስቀረት ክህሎትና ፈጠራን መሰረት ወደ አደረገ ተወዳዳሪነት መለወጥ ነው፡፡ ከእንግዲህ የመንግሥት ተቋማት ሃሳብን፣ ፈጠራን እና ምርታማነት ትኩረት አድርገው ለውጥ እንዲያመጡ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚገጥመውን የመልካም አስተዳደር ችግር ወደ ቀልጣፋ እና ውጤታማ አገልግሎት ለመቀየር ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የአስተዳደር ሥርዓት እንዲሰፋና እንዲጠናከር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚደረግም ፕሬዚዳንት ታዬ አመልክተዋል፡፡
ትግበራው እውን እንዲሆን የሁሉም ርብርብና ሚና ወሳኝ በመሆኑ በአንድ መንፈስ መንቀሳቀስ እንደሚገባም ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት፡፡
በተያያዘ ዜና ኢትዮጵያ ፈጣን፣ ለውድድር ክፍት እና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ ካላቸው የአፍሪካ ኢኮኖሚዎች አንዷ ለመሆን ጉዞ መጀመሯን፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ማሻሻያዎችን እያከናወነች እንደምትገኝም ጠቁመዋል፡፡
በእነዚህ አማካኝነት ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ስብራቶችን ለመጠገን እንዲሁም ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ግስጋሴ በማድረግ ላይ ትገኛለችም በማለት አብራርተዋል፡፡
ሕዝቡ፣ የመንግሥት አመራር እና ሠራተኞች፣ የሲቪል ማህበረሰብ እንዲሁም የልማት አጋሮች የተጠናከረ ድጋፍ እና ተሳትፎ እንዲጠናከርም አሳስበዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም