ሰመራ፦ በአፋር ክልል ለስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ የተሳካ ሥራ መሥራቱን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
የአፋር ክልል ሕብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት ለስድስት ቀናት ሲያካሂዱ በቆዩት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ያደራጁትን አጀንዳ በተወካዮቻቸው ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል።በሀገር ደረጃ በሚደረገው ምክክር ክልሉን የሚወክሉ ተሳታፊዎችንም መርጠዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ እንዳሉት፤ ከአፋር ክልል የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ቀርበው ከተመረመሩ በኋላ ከሌሎች ክልሎች ከተሰበሰቡ አጀንዳዎች ጋር በሀገር ደረጃ በሚካሄደው ጉባኤ ቀርበው ምክክር ይደረግባቸዋል ብለዋል።
አምባሳደር አይሮሪት መሀመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ የተሳኩ ሥራዎች የተከናወኑበት እንደሆነ ጠቁመው፤ ሂደቱ እንዲሳካ አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።
ስድስት ቀናት በወሰደው አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በክልሉ ከሚገኙ 49 ወረዳዎች የተመረጡ ከ800 በላይ የሕብረተሰብ ክፍል ወኪሎች እና በክልሉ የሚገኙ ከ700 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሦስቱ የመንግሥት አካላት፣ የተለያዩ ተቋማት እና ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች ተሳትፈዋል፡፡
ከመስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት ሰፊ ውይይት ያካሄዱት ከ49 ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች አጀንዳቸውን አጠናክረው ለመረጧቸው 54 ተወካዮች አስረክበዋል።
ከመስከረም 25 ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት ሦስት ቀናት ደግም፣ 54ቱ ተወካዮች የክልል ባለድርሻዎች አካላት ከሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሦስቱ የመንግሥት አካላት፣ የተለያዩ ተቋማት
እና ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች ጋር በመሆን ሰፊ ውይይት አድርገው አጀንዳቸውን የሚያደራጁላቸው 25 ሰዎችን መርጠው አጀንዳቸውን ሲያደራጁ ቆይተዋል።
በመጨረሻም የተመረጡት 25 ተወካዮች የክልሉን አጀንዳ በማደራጀት ለጉባዔው አቅርበው ከተነበበና ከተሰማ በኋላ በተወካዮቻቸው ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል።
የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱን ሲያስተባብሩ የቆዩት ኮሚሽነር አምባሳደር አይሮሪት መሐመድ (ዶ/ር) እና ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን የክልሉን አጀንዳዎች ከህብረተሰብ ክፍል እና ከባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተረክበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኮችን በተከታታይ እያካሄደ ይገኛል።
እስካሁንም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በሲዳማ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር መድረኮችን ማካሄዱ ይታወቃል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም