አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ የፍልሰተኞችን ጉዳይ በልማት ፖሊሲዎችና ዕቅዶች ውስጥ አካታ እየሠራች መሆኑን የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ሁለተኛው አህጉራዊ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
ሚኒስትሩ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2018 የጸደቀውን ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነትን በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡በስምምነቱ ከተካተቱ 20 አጀንዳዎች ውስጥ አስሩን በተለያዩ የልማት ፖሊሲዎችና ዕቅዶች ውስጥ ተካተው እንዲፈጸሙ አድርጋለች፡፡
በዚህም መደበኛ ያልሆነውን ፍልሰት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም መደበኛ ፍልሰትን በማስፋት ከፍልሰት የሚገኘውን ጥቅም በማሳደግ በኩል ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መቻሏንም ጠቁመዋል፡፡
የስምምነቱን ሀገር አቀፍ የአፈጻጸም ሪፖርት እኤአ በ2020 ለተመድ ማቅረቧን አስታውሰው፤ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ የአፈጻጸም ግምገማ መድረኮች ላይም የነቃ ተሳትፎ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ኢትዮጵያ የፍልሰት መነሻ፣ መተላለፊያ እና መዳረሻ ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሀገር አቀፍ የትብብር ጥምረት ካውንስል በማቋቋም እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የስደተኞች አስተዳደር ላይ ውጤት ለማስመዝገብ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚጠይቅ አመልክተው፤ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ሥራዎችን በመደገፍ በኩል እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ኤሚ ፖፕ በበኩላቸው፤ የስደተኞችን ጉዳይ በብሔራዊ የልማት እቅዶችና ስትራቴጂዎች ውስጥ አካቶ መሥራት እድገትን በማፋጠን በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
ዜጎች በነጻ ተዘዋውረው መሥራትና መኖር የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ሳንፈጥር ዘላቂ ልማት ማሰብ ከባድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስደተኞችን በሚመለከት በየዕለቱ የምንሰማቸውን አሰቃቂ ታሪኮች ለማስቀረት ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡
ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነት ተግባራዊነት ላይ መንግሥታት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሌሎችም ባለድርሻዎች በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ አመልክተው፤ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅትም ይህን ሥራ በቅርበት ይደግፋል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የጤና፣ የሰብዓዊ ጉዳዮችና ማህበራዊ ልማት ኮሚሽር አምባሳደር ሚናታ ሳማቴ ሴሉማ፤ የስደተኞች ጉዳይ የአፍሪካ ኅብረትን፣ የአባል ሀገራትንና የሌሎችንም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ይፈልጋል፡፡
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ስምምነት የስደተኞችን ጉዳይ በአግባቡ ለማስተዳደርና አጀንዳ 2060ን ለማሳካት፣ የሥራ እድል ለማስፋፋትና በሁሉም መስክ አፍሪካውያን የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
ስደት ለመነሻ፣ መተላለፊያ ተቀባይ ሀገሮች ትልቅ እድል ይዞ ይመጣል ያሉት አምባሳደሯ፤ አህጉራዊ አቅሞችን አስተባብሮ መጠቀምና የስደተኞችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሁሉም ባለድርሻዎች በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጉባኤው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ትብብር የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም