አዲስ አበባ፡– ‹‹የቻይና ዜሮ ታሪፍ ፖሊሲ ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልከውን የምርት መጠን እንድታሳድግ እና አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴን ለመቀየር ያግዛታል›› ሲሉ በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዳዊት ሀይሶ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
መምህር ዳዊት ሀይሶ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲው ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልከውን የምርት መጠን አቅርቦት ለማሳደግና እንዲሁም ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
እንደ መምህር ዳዊት(ዶ/ር) ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልካቸው ምርቶች ከቀረጥ ነጻ መሆናቸው የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ እና ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።
በተጨማሪም ኢንቨስተሮችን ለመሳብ እና በቻይና ገበያ ውስጥ እንዲገባ እንደሚያግዝ አውስተው፤ ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና እንዲላኩ የተፈቀዱት ምርቶች በርካታ እንደመሆናቸው
ይህን ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አውስተዋል። ፖሊሲው በኢትዮጵያ ያሉ ላኪዎች ምርታቸውን ወደ ትልቁ ዓለም ገበያ እንዲያስገቡ ትልቅ እድል ይሰጣል ብለዋል።
በዓለም አቀፍ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ መሰረት ይህ ታሪካዊ ውሳኔ መሆኑን አውስተው፤ ምርታማነትንና የኤክስፖርት መጠንን ለማሳደግ የተቀላጠፈ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።
ፖሊሲው የሥራ እድል ለመፍጠር እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማነቃቃት ያስችላል ያሉት መምህር ዳዊት(ዶ/ር)፤ ይህም ሀገሪቷ በተወሰኑ የወጪ ገበያዎች ላይ ያላትን ጥገኝነት ይቀንሳል ብለዋል።
በዚህም ባለሀብቱ በደንብ መበረታታት አለበት፤ አምራቹ መጠንከር አለበት፤ መንግሥትም ከፖሊሲ አንጻር እንዴት አድርገን መጠቀም እንችላለን የሚለውን ሊያስብበት ይገባል ሲሉ አስረድተዋል።
በሀገር ውስጥ የሚገኙ አምራቾች፣ ባለሀብቶች እና መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ዕድሎች ሲገኙ ተጠቃሚነቱ ከፍ እንዲል የሚያመርታቸውን የምርት ዓይነቶች በስብጥር አብዝቶ ማምረት እና መጠንከር እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል፡፡
ማምረት ብቻውን በቂ ወይም ስኬት አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት መምህር ዳዊት(ዶ/ር)፤ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ጥራትን ያስቀደመ አሠራር መከተል ይገባል ብለዋል።
ምርቶቹ ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና እንዲገቡ ዕድል መገኘቱ በቻይና ገበያ ውስጥ ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ ረገድ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡
ቻይና በቅርቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ33 የአፍሪካ ሀገራት የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲ በ2024 የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ላይ ከቀረጥ ነጻ እንዲገበያዩ መፍቀዷ የሚታወስ ነው።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም