አዲስ አበባ:- በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን በሚመጥን ደረጃ ልክ ላይ ለማድረስ አሰባሳቢ እና ገዢ ትርክት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በሚመጥናት ደረጃ ልክ በዓለም አቀፍ መድረኮች መታየት ይኖርባታል፡፡ ይህንን እውን ለማድረግም ከነጠላ ትርክት ወደ ሕብረ ብሄራዊ ትርክት መሻገር ይጠበቃል፡፡
አሰባሳቢ እና ገዢ ትርክትን ያጸኑ ሀገራት ስፍራቸው ታላቅነት እና ብልጽግና ሆኗል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ኢትዮጵያውያንም በአንድ ሃሳብ የጋራ መግባባትን እውን በማድረግ የታቀደው የእድገት ደረጃ መድረስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ሕብረብሄራዊ አንድነትን ማጽናት፣ እኩልነት እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ብልሹ አሠራር፣ ሕገወጥነትና ሙስና የሂደቱ እንቅፋት እንዳይሆኑ የተጀመረው የጸረ ሙስና ትግል፣ ሕግ የማስከበርና የመንግሥት አሠራሮችን ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የማድረግ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
ሀገራዊ እድገትን ለማስቀጠል፣ ብልጽግናንም እውን ለማድረግ ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆም ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለትግበራው ደግሞ ሰላም ማስፈንና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቁልፍ ሥራዎች ይሆናሉ ብለዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለጻ፤ ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብት የመንግሥት እና የመንግሥት ጸጥታ ተቋማት ብቻና ብቻ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመጠበቅ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነትን አፈጻጸም ይሻሻላል፡፡ ለሚገነባው ዘላቂ ሰላም ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይገባዋል፡፡
ዛሬም በድጋሚ መቀራረብ፣ መነጋገር፣ መከራከር፣ መግባባት የመጨረሻ ግብ ሊሆን ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ ሁሉ ሂደትም መተማመን ዋጋው የላቀ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
አምና የተመዘገበው እድገትና ሀገራዊ ስኬት በአንድ በኩል አመርቂ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ቁጭትን የሚፈጥር እና የበለጠ ኃላፊነትን የሚጥል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሰላምን ለማስፈን እየተደረጉ ካሉ ጥረቶች መካከል በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኩል የሚከናወነውን አንስተዋል፡፡ ኮሚሽኑ የቅድመ የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራትን በማጠናቀቅ ወደ ምክክር ምዕራፍ መሸጋገሩን አንስተዋል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልልች ለምክክር ግብአት የሚሆኑትን ጥያቄዎችና ሃሳቦችን ለመሰብሰብ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡ ጥረቶቹ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ምክክር በማካሄድ የተሻለ መግባባት እንዲፈጠር እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የተሸረሸሩ ማህበራዊ እሴቶችን ለማደስ እና ሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ለማሳለጥ የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችልም አመልክተዋል፡፡ ኮሚሽኑ የያዘውን ዓላማ እንዲያሳካና የተጣለበትን ተስፋ እውን እንዲያደርግ የሁሉንም ድጋፍ ይፈልጋል ብለዋል፡፡
በመንግሥት በኩል ዛሬም የሰላም በሮች ክፍት ናቸው፤ በተናጠል ቢሆን በጋራ በሰላማዊ መንገድ ከማናቸውም ወገን ጋር ለመነጋገር መንግሥት ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑንም ፕሬዚዳንት ታዬ አረጋግጠዋል፡፡
የኃይል አማራጭን በመጠቀም ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚደረጉ ማናቸውም እኩይ ተግባራትን መንግሥት በሆደ ሰፊነት የሚያልፍበት ዕድል እጅግ የጠበበ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በሆደ ሰፊነት በቂ ጊዜ መሰጠቱንም ነው የገለጹት፡፡
የህብረተሰቡን አብሮ የመኖር እሴትን የሚሸረሽር ተግባር በሚፈጽሙ አካላት በጥላቻ ንግግርም፣ የሕዝብን አብሮነትና ማህበራዊ ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ሕዝብን ከሕዝብ በሚያጋጩ አካላት ላይ መንግሥታዊና ሕጋዊ ርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡
የተመዘገበው እድገት ኢትዮጵያ በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆና የተመዘገበ በመሆኑ የውጤቱን ፋይዳ ከፍ ያደርገዋል፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች ባይኖሩ ኖሮ ከዚህ በላይ እድገት ሊመዘገብ እንደሚችል ሲታሰብ እንደሚያስቆጭም ተናግረዋል፡፡
በተለይ የጸጥታ ስጋትን፣ ሌብነትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ ብልሹ አሠራርን፣ ኮንትሮባንድንና ሕገወጥነት ካላቸው ስር የሰደደ ሁኔታ እና ዘርፈ ብዙ መገለጫዎች አንጻር በአጭር ጊዜ ነቅለን የምንጥላቸው ነው ያሉት፡፡
ሆኖም ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመቀነስና የእድገቱ እንቅፋት እንዳይሆኑ ትኩረት በመስጠት በሂደትም ከሙስናና ሌብነት የተላቀቀች ሀገር እንድትሆን በብርታት እንደሚሠራም አመልክተዋል፡፡
የፍትህ ሥርዓቱ ውጤታማነትና የሰብአዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል የሚያስችሉ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ በማስታወስም፤ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙ የፍትህ መዛባትና የመብት ጥሰቶችን በአግባቡ ለመቋጨት የሽግግር ፍትህ ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ጥረቶች መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡
የጸደቀውን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ለመተግበር የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ መጠናቀቁን፣ ለፖሊሲ ትግበራው የሕግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውን፣ አስፈጻሚ ተቋማትን የማደራጀት ሥራም በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም