ዜና ትንታኔ
አፍሪካ ከዓለም በቆዳ ስፋትና በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዋ አህጉር ናት። የተፈጥሮ ሀብት የተትረፈረፈባት ይች አህጉር መገኘት ከነበረባት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተጽእኖ ፈጣሪነት ደረጃ ላይ አይደለችም። የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነፃነት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነትን፣ተጽእኖ ፈጣሪነትን፣ ሉአላዊነትንና ኃያልነትን የሚያስከብር መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
አፍሪካ በአላት የዳበረ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ መልካምድራዊ አቀማመጥና በሌሎችም ሀብቶች አኳያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷና ተጽእኖ ፈጣሪነቷ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ይላሉ፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ያሉበት የእድገት ደረጃ ከአደጉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ በመሆኑ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ማዕከል ተመራማሪና መምህር ደቻሳ አበበ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፤ የበፊቱ ትውልድ የአህጉሪቷን ሕዝብ ከቅኝ አገዛዝ ለማውጣትና የአፍሪካውያንን የቀደመ ነፃነታቸውንና ክብራቸውን ለማስመለስ መስዋዕትነት በመክፈል ነጻነቱን አስከብሯል። የአሁኑ ትውልድ ደግሞ አህጉሪቷን ከድህነት ማላቀቅ፣ ግጭትን ማስወገድ፣ ሁሉም ዜጎች መካከለኛ ገቢ
እንዲኖራቸው ማስቻል፣ ኃያልና ተሰሚነት ያላት አህጉር ለማድረግ መሥራት እንደሚኖርበት ይገልጻሉ፡፡
የአፍሪካ ህዳሴ የሚረጋገጠው በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚው ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ሲቻል ነው የሚሉት ምሁሩ፤ በውጭ ኃይሎች በቀጥታ በሚጫንብን ፖሊሲ ለማስወገድና ዘላቂ ልማት ለማምጣት አፍሪካውያን በህብረትና በትብብር መስራት እንደሚኖርባቸው ነው የጠቆሙት።
እንደ ደቻሳ (ዶ/ር) ገለጻ፤ አፍሪካውያን የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነትና ሌሎች ልዩነቶች ቢኖሯቸውም ያላቸውን አቅም አንድ ላይ አሰባስቦ የመጠቀም ፍላጎት አላቸው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው አፍሪካ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት መቀመጫ እንድታገኝ እየተደረገ ያለው ትግል አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ሃሳብ ከግላዊነት ይልቅ በጋራ መቅረቡ የተሻለ ቢሆንም የጋራ መዳረሻ እንደሚያስፈልገው ደቻሳ (ዶ/ር) ያመላክታሉ፡፡
ተደማጭነት የሚገኘውም በሁለንተናዊ አቅም ሲኖር ነው የሚሉት ተመራማሪው፤ በዚህም አፍሪካ እንድትሰማ ከተፈለገ ከፉክክሩ ይልቅ ትብብር ማስፋት፣ የጎንዮሽ የኢኮኖሚ ትስስሮችን በማጠናከርና ተመጋጋቢ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ይህን ማድረግ ሲቻልም የታሰበውን ተደማጭነትና ኃያልነት በቀላሉ ማሳካት እንደሚቻል ነው የጠቆሙት፡፡
አፍሪካን እንደ አንድ ሀገር በማሰብ የአፍሪካ-ሩሲያ፣ የአፍሪካ-ቻይና፣ የአፍሪካ-አሜሪካና ሌሎችም ፎረሞች በየጊዜው ይካሄዳሉ የሚሉት ደግሞ የሰላምና ደህንነት ባለሙያና የኢንተራክሽን ፎር ቼንጅ ኢን አፍሪካ ዳይሬክተር ወርቁ ያዕቆብ (ዶ/ር)፤ በእነኝህ ፎረሞች ላይ አንዳንድ ሀገራት የንግድ ስምምነቶችን የመፈራረም ሁኔታ ቢኖርም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ስምምነት መደረግ ካለበትም የሚደረገው እንደአህጉር እንጂ እንደ ሀገር ሊሆን እንደማይገባ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡
አፍሪካ እንደ አህጉር ከሌሎች ጋር በምትፈጥራቸው ወዳጅነቶችና ትብብሮች የተለያዩ እሳቤዎችን አመንጭታ ሌሎችም እንዲቀበሉ የማድረግ ሚናዋን ማጎልበት እንደሚኖርባት የሚገልጹት ወርቁ ያዕቆብ (ዶ/ር)፤ የአፍሪካ ህብረት እንኳን የ54 ሀገራትን ወክሎ የአህጉሪቱን ዜጎች መብት ሊያስከብሩ የሚችሉ እሳቤዎችን በሚያመነጭበት ወቅት እንደ አህጉር ተጽእኖ የመፍጠር አቅሙን ማጎልበት አለበት ይላሉ፡፡
እንደ ወርቁ ያዕቆብ (ዶ/ር) ገለጻ፤ በአፍሪካ እንደ አህጉር ከኢኮኖሚ ቅኝ ግዛት በመላቀቅ ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን ሀገራቱና ሕዝቦቻቸው እንዲሁም መሪዎች ተቀራርበው መሥራት ይገባቸዋል።
ያደጉት ሀገራት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በተናጠል የሚያደርጉት ውይይት የአፍሪካ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን
ለማጠናከርና የተናጠል ይሁን የጋራ ጥቅሞቻቸውን ካደጉት ሀገራት እንዲያገኙ ያግዛል የሚሉት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና ዓለም አቀፍ ትምህርት ክፍል የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ በቀለ ሀብታሙ ናቸው፡፡
አፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት የተፈላጊነት መጠንን በመጨመር የባለብዙ ወገን ወዳጅነት ዕድሎችን ይፈጥራል። በዚህም አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅሞችን የሚያስገኝ ይሆናል የሚሉት ተመራማሪው፤ አፍሪካ ካላት የተፈጥሮ እምቅ አቅምና ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ የተነሳ ሁሉም ያደጉ ሀገራት የወደፊት እጣ ፈንታቸውን ከአፍሪካ ጋር ለማስተሳሰር እንደሚፈልጉ ያስረዳሉ፡፡
ይህን ለማሳካት እያንዳንዱ ሀገር ጋር ከሚያደርጉት ግንኙነት ይልቅ በአንድ ማዕቀፍ በአፍሪካዊነት እሳቤ በመወያየት ፍላጎታቸውንና የሀገራቸውን የፖሊሲ ጉዳዮችን ለማስፈጸም አቅም ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ጊዜ አፍሪካ ትታወቅበት የነበረው ስደት፣ የከፋ ድህነት፣ ጦርነትና ጭቆና እየከሰመ በተቃራኒው አንጻራዊ ልማትና ፖለቲካዊ መረጋጋት እየታየ ነው። በመሰረተ ልማት፣በኢንዱስትሪ፣በግብርናና በማህበራዊ መስኮችም ተጨባጭ ልማቶች እየታዩ መሆናቸውን ምሁራኑ ያብራራሉ።
አሁንም የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም የአፍሪካ ሕዝቦችም በአንጻራዊነት የኑሮ ደረጃቸው እየተሻሻለ ይገኛል። እየተመዘገበ ያለውን የዕድገት ፍሬም እየቀመሱ ናቸው።የድህነት መጠኑም በመቀነስ ላይ ይገኛል። የእርስ በርስ ግጭቱም እየቀነሰ መጥቷል። ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማስፈን በኩልም እንዲሁ ለውጦች እየታዩ ነው። መንግሥታቱም በጋራ አጀንዳዎች ላይ አብሮ የመሥራትና ትብብራቸውን የማጠናከር ባህላቸውም እየጎለበተ መጥቷል። ሆኖም የሚፈለገውን ተጽእኖ ፈጣሪነት ለማምጣት አሁንም እንደ አህጉር ፈርጀ ብዙ ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡
በዘመነ ግሎባላይዜሽን አፍሪካዊ ይበልጡኑ በህብረት ካልሰሩ የህዳሴ ጉዞቸው የሚፈለገውን ያህል ሊፈጥን አይችልም። ለዚህ ነው አሁን አፍሪካዊያን ትልቁ ተግባራቸው መሆን ያለበት የአፍሪካን ኢኮኖሚ በእጅጉ ማሳደግ ነው።በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ የማዕድን ሀብት እየተገኘ ነው። እየወጣ ያሉባቸውም ሀገራት አሉ።የአፍሪካ ወጣቶች አብዛኛዎቹ በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው። እነዚህም በአፍሪካ ለውጥ ለማምጣት ምቹ ሁኔታ መሆናቸውን ምሁራን ጠቅሰዋል።
አፍሪካዊያን እንደ አህጉር ኢንቨስትመንትን በማፋጠን፣ ኢንዱስትሪን በማስፋፋት፣የመሠረተ ልማት አውታሮችን በማስፋትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በማጎልበት ከድህነት በመውጣት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖ መፍጠርና ተሰሚነታቸውን ማጎልበት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት ምሁራኑ፡፡
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም