ዜና ትንታኔ
ስድስተኛው ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና መርሀ ግብር በፌዴራል ደረጃ ዛሬ የሚካሄድ ሲሆን፤ በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ የታክስ ሕግ ተገዢነት ላስመዘገቡ 550 ግብር ከፋዮች እውቅና እንደሚሰጥ የገቢዎች ሚኒስቴርና ጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ለሀገሪቱ የገቢ እድገት የእነዚህ ግብር ከፋዮች ሚና ትልቅ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
ይህ የእውቅና መርሀ ግብር በዘርፉ ያጋጠሙ ማነቆዎችን ለማስወገድ እንደ ምሳሌነት ከሚነሱ ተግባራት አንዱ መሆኑ ይገለጻል፡፡ ለመሆኑ ተቋማቱ ለመንግሥት ገቢ አሰባሰብ ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን ለማስወገድ ምን ሠሩ?
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ እንደገለጹት፤ በተለይም በ2016 በጀት ዓመት በሁለቱም ተቋማት በተደረጉ ጥረቶች በዓመቱ ለመሰብሰብ በእቅድ ከተያዘው 529 ቢሊዮን ብር ውስጥ 512 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ይህ አፈጻጸም በ2015 በጀት ዓመት ከነበረው 442 ቢሊዮን ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እድገት ያለው ሆኗል፡፡
በዚህ ጥረት ውስጥ ተቋማቱ አገልግሎታቸውን በጥራት ለመስጠት የሚያደርጉት ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ግብር ከፋዮችም የራሳቸውን በጎ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በተለይ በመንግሥት የተዘረጉ የታክስ ሕጎችና አሠራሮችን ተከትለው የሚሠሩ ግብር ከፋዮች ለሀገራቸው ታምነው የራሳቸውን ድርሻ አስቀርተው የመንግሥትን ገቢ በሚፈለገው ጊዜና መጠን በመክፈላቸው ባለፉት አምስት ዓመታት እውቅናና ማበረታቻ ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንደሚሉት፤ የገቢ አቅምን ካሳደጉ ተግባራት መካከል ለታማኝ ግብር ከፋዮች የተሰጠው ትኩረት አንዱ ነው፡፡ በተለይ ለታማኝ ግብር ከፋዮች የሚሰጠው የእውቅና መርሀ ግብር ታክስ እንዳይጭበረበር የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረከት ነው፡፡ ተሸላሚዎች ታማኝነትን በሂደት እንዲያጸኑ ከማስቻሉም በላይ የበለጠ ሀገርን ማገልገል የሚማሩበት ነው፡፡
ከአገልግሎት አሰጣት አኳያ የመንግሥትም ሆነ የሕዝቡ ፍላጎት ጤናማ እውነተኛ ፍትሐዊ የሆነ ሥራን መሥራት ሲሆን፤ ሆኖም አገልግሎት ሰጪዎች እንደሚፈልጉት ብቻ የሚሰጥ አይደለም ይላሉ፡፡ የሚሰጠው ፍትሐዊ አገልግሎት የብዙ ጉዳዮች ድምር ውጤት መሆኑንም ያመላክታሉ፡፡ ጥቂት ችግሮች ሲከሰቱ ባልሆነ መንገድ ትርጉም በመስጠት ነገሩን የማባባስና የተቋም ችግር አድርገው የማየት አዝማሚያዎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡ ይህ ግን መታረም ያለበት ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡
ተቋማቱ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የመጀመሪያ ጉዳያቸው ያደረጉት ነገር ከ14ሺህ በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችን የሚያደራጁበት ተቋማዊ መዋቅር በተሟላ መልክ ማደራጀታቸውን እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም በዘርፉ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ የሰጠ ትልቅ የሥራ አካል እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡
ወይዘሮ ዓይናለም ለታክስ አሰባሰቡ ችግር የነበሩና እርምት የተወሰደባቸውን ጉዳዮች በአንጻሩ ሲገልጹ እንዳነሱት፤ ሁለቱ ተቋማት የሚያስተዳድሩት ከ14 ሺህ በላይ ሠራተኞች አሏቸው፡፡ በሀገር ውስጥ ገቢ ከአምስት ሺህ በላይ፣ በጉምሩክ በኩል ደግሞ ከዘጠኝ ሺህ በላይ ሠራተኞች ይተዳደራሉ፡፡
“ከ14ሺህ ሠራተኞች ውስጥ አምስትም አስርም ወይም ከዚያ በላይ የሚሆን እጃቸው ንጹህ ያልሆኑ፤ ስነ ምግባር የጎደላቸውና የሞራል ዝቅጠት ውስጥ ያሉ ሠራተኞች አይኖሩም ብለን አናምንም፡፡ ነገር ግን ላለፉት ጊዜያት ስኬት ያበቁን ጠንካራ ሠራተኞች ወደፊትም የዚህ ተቋም ጠንካራ መሠረትና መሪዎች እንዲሆኑ የምናጠናክራቸው፤ በታማኝነታቸውም የሚመሰከርላቸው ሠራተኞች እንዳሉ መረዳት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
በዚህም በጥፋት ውስጥ ያሉትን በማረምና የተሻሉትን በማበረታታት በታማኝነት ሀገርን እንዲያገለግሉ እየተደረገ ይገኛል” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ሀሰተኛ ደረሰኝ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጣልቃ ገብነት ሊፈታ የሚችል በተቋሙ መወሰድ አለበት የሚል ስምምነት ላይ ተደርሶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተግብቷል ይላሉ ሚኒስትሯ፤ የተሠሩ ተግባራትን ሲያብራሩ፤ ሥራውን በቴክኖሎጂ መደገፍ መፍትሔ ይሆናል በማለት፤ በዚህም በኤሌክትሮኒክስ የተደገፈ የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
ምንም እንኳን በቴክኖሎጂ የተደገፈ የክፍያ ሥርዓት መገንባት ቢያስፈልግም፤ በሲስተም ተደራሽነት፣ እንዲሁም ደግሞ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ የምትከተለው የግብር ሥርዓት ለክልል ግብር ከፋዮችም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ለተደራጁት ግብር ከፋዮች በሚጠቅም መንገድ የወረቀት ደረሰኝ እንዴት ይተዳደሩ የሚል አዲስ መመሪያ ወጥቶ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት ማለቁንም አስታውቀዋል፡፡
በዋናነት ከሲስተም ጋር የተገናኘ በግለሰብም ሆነ በኩባንያ ደረጃ ሲጠቀሙ ከገቢዎች ሚኒስቴር ሲስተም ጋር የተቀናጀ ደረሰኝ ለመተግበር መመሪያ ወጥቶ ውሳኔ በመስጠት ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
አሁን ላይ የሽግግር ጊዜ ላይ ነው ያለነው የሚሉት ሚኒስትሯ፤ “በ2017 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከዚህ ቀደም የታተሙ ደረሰኞችን የምንጠቀምበት፤ ከዚህ የተረፉትን ደግሞ ከአሠራር ውጪ የምናስወግድበትን ሥርዓት ዘርግተን እንሠራለን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከአገልግሎት አሳጣጥ ጋር ተያይዞ ያሉ የሥነ ምግባር ብልሹነት በተመለከተ እንደ ተቋም ገቢዎችና ጉምሩክ ከማንኛውም ሲቪል ሰርቪስ ተቋማት በተለየ መልኩ የራሱ የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ብልሹ አሰራር ላይ የተገኙ ሠራተኞች የሚስተካከሉበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ተጨባጭ ችግሮችን ፈጥረው በተገኙ ሠራተኞች ላይ ተጨባጭ ማስረጃ ላይ በተመሰረተ መንገድ ርምጃዎች ሲወሰዱ እንደነበር አብራርተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን በተቋማቱ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆናቸው፤ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በታማኝነት እንዲወጡ፤ በተለይ በመንግሥት ሥራ ያላቸውን ኃላፊነት ተጠቅመው ከመንግሥት ገቢ ላይ ለማስቀረት የሚሠሩ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ጋር ያልተገባ ግንኙነት ማድረግ ለችግር እንደሚዳርጋቸው እናስተምራለን፤ ይህንን ጥሰው ሲገኙም ርምጃ እንወስዳለን ነው ያሉት፡፡ ይህ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በትኩረት የሚሠራው በአንድ በኩል የውስጥ ችግርን መፍታት፤ የሠራተኞችን ሥነ ምግባር ሊያርም የሚችል ሥራ መሥራት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሰጪዎችም ቢሆኑ የሚከተሉት የሌብነትን መንገድ ስለሆነ እነሱም ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት፡፡
ሚኒስትሯ እንደሚሉት፤ በዚህ ጉዳይ በተለይ ከተቋሙ ተልዕኮ ጋር ተያይዞ ሰዎች በስፋት በሚያነሱት ጉዳይ ላይ የትኛው ትክክል ነው? በሚለው ከማህበረሰቡም ሆነ ከተጠቃሚው በተጨባጭ መረጃ አስደግፎ እስከመጨረሻ የመሄድ ጉድለት ይስተዋላል፡፡ ሆኖም በተቋሙ በኩል ተጨባጭ መረጃ እስከተገኘ ድረስ ማስተካከያ ርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኝነቱ አለ፡፡
በሌላ በኩል ለገቢ አሰባሰቡ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ዘርፈ ብዙ የሆኑ የተቋሙን ችግሮች የፈታ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ በተለይም የንግድ ማህበረሰቡ ሕጋዊ መንገዱን ትቶ ወደ ሕገ ወጥ መንገድ እንዲያተኩር ካደረጉት ጉዳዮች አንዱ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ ነበር ብለዋል፡፡
መንግሥት በኢኮኖሚ ማሻሻያው የወሰደው የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት አስተዳደር በገበያ እንዲወሰን የማድረጉ ርምጃ ለታክስ አስተዳደሩ ትልቅ እፎይታን የሰጠ መሆኑን በማብራሪያቸው አመላክተዋል፡፡ ይህም የሕገ ወጥ ደረሰኝ፤ የኮንትሮባንድና ሌሎች የማጭበርበሪያ ሂደቶች ቀድሞ ከነበሩት የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን፣ አዲሱ የፖሊሲ ማሻሻያ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ተቋምም በ2017 በጀት ዓመት በይፋ የሚታወጀው የገቢ እቅድ ይህንን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ይህንና መሰል የማጭበርበር፣ የስርቆት፣ እና ከታክስ መረብ ውጪ የመሆን ፍላጎቶችን በሰፊው የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይም በሀገር ውስጥ ገቢም ሆነ በጉምሩክ በሂደት ሊታዩ የሚችሉ ውጤቶችን የሚያመጣ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
አማራጮችን በመዘርጋት በሀገር ውስጥ ታክስም ሆነ የውጪ ቀረጥና ታክስ ለመሰብሰብ በሚደረገው ጥረት አጋዥ የሆኑ የቴክኖሎጂ አማራጮች ተዘርግተው ሲሠራባቸው እንደቆዩ በመግለጽ፤ በዚህም ምክንያት በሁለቱም ዘርፎች ግብር ከፋዮች በአካል ወደ ተቋማቱ ሳይመጡ ታክሳቸውን ማሳወቅ የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋቱን ይናገራሉ፡፡
የመጨረሻ የተቋማቱ ውጤት መለኪያ የሀገሪቷ ኢኮኖሚ ያመነጨውን ገቢ በመሰብሰብ የመንግሥት የልማት ፋይናንስ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረግ ነው በማለት፤ በዚህ ረገድ በየዓመቱ እየተሻሻለ የመጣ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ታሳቢ ያደረጋቸውን በተለይም ከገቢ አንጻር የሀገር ውስጥ የገቢ አቅምን ከማሻሻል አኳያ ዘርፈ ብዙ ርምጃዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡ ይህም የገቢ መሰብሰብ ተግዳሮቶችን በመሻገር የሚፈለገውን ግብ ማሳካት ያስችላል ነው ያሉት፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም