በሕይወት ውስጥ አግኝቶ ማጣት እንዲሁም አጥቶ ማግኘት በሆነ ቅጽበት ሊፈራረቁ እና ባልታሰበ ሁኔታ ተከስተው ድንገት ሙሉ ነገሮችን በመልካም አልያም በመጥፎ መልኩ ሊቀይሩት ይችላሉ። እንደው እንደዘበትም ዕድሜ ልክ ጥረው ግረው ያፈሩት ጥሪት በአንድ ጀንበር ተንኖ ታሪክ ብቻ ይሆናል። ይህን መሰል የቀን ጎዶሎ እንዳይመጣም ‹‹አግኝቶ ከማጣት ይሰውረን›› የሚለውን ንግግር ብዙዎች ሲሉት የሚሰማው ማጣትን ተከትለው የሚመጡት ሥነ-ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አጠቃላይ የአንድን ሰው ኑሮ ዝብርቅርቁን በማውጣት ከዜሮ እንዲጀምር ስለሚያደርጉ ነው። ምናልባት ተመልሶ የማንሰራራቱና ቀድሞ ወደነበረ አኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ የሚደረገው ሒደት እንደ ችግሩ ተጋላጭ ሥነ-ልቦናዊ ጥንካሬ የሚወሰን ቢሆንም እንኳን አንዳንዴ ግን ሒደቱ እንዳይሳካ ወደ ኋላ የሚጎትቱ ምክንያቶች ካሉ ለለውጡ አዳጋች ይሆናል። ይህን ያነሳሁላችሁ ያለምክንያትም አይደለም ይልቁንም ከሰሞኑ ከአንድ ፋብሪካ ግዢ ጋር ተያይዞ ያደመጥኩት ችግር ጆሮዬን እንድጥል ብቻ አይደለም ስለጉዳዩ እንዳውቅ ፍላጎት ስላሳደረብኝም ነው።
ተከሰተ የተባለውን ችግር እያውጠነጠንኩም በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን አስመልክቶ መረጃ ሊሰጡኝ ይችላሉ ወደተባሉት ክርክር የሚደረግበት ፋብሪካ እህት ኩባንያ በሆነዉ በላቦራ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ የማኔጂንግ ዳይሬክተሩና የምክትል ዳይሬክተሩ ዋና አማካሪ ዶክተር አሰፋ አዳነ ጋር ለመደወል የስልክ መነጋገሪያውን ከጆሮዬ አስጠጋሁ። ‹‹ሠላም›› ከወዲያ ጫፍ የደረሰኝ የንግግር መጀመሪያ ነበር። ከየት እንደደወልኩና የፈለግኩትን መረጃ መናገር ከመጀመሬ ነበር ተቋማችን ድረስ መጥተው ሊያናግሩኝ እንደሚፈልጉ የገለጹልኝ።
ከአንደበታቸው
የነገሩን መነሻ ከምን እንደሚጀምሩልኝ ግራ በመጋባት መንፈስ ውስጥ ሆነው ግዢ የተፈፀመበት ፋብሪካ ባለቤቶቹና ቤተሰቦቻቸው የእስር ቅጣት እስከደረሰባቸው ድረስ ዶክተር አሰፋ ሁነቱን አንድ በአንድ ያወጉኝ ጀመር። የተባለው ፋብሪካ በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኝ ሲሆን፤ ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር በመባል ይታወቃል። ይህንንም ገዝተው አዲሱ ባለቤት የሆኑት ዶክተር በዕውቀቱ ታደሰና ባለቤታቸው ወይዘሮ መሠረት በረደድ ሕዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም ከሻጮች ጋር በሕጋዊ ውል በመስማማት እንደተፈራረሙ ያስታውሳሉ። ሆኖም ድርጅቱ እንደታሰበው ምርት ማምረትና ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለሌሎችም ጥቅም ማስገኘት በሚጀምርበት የመጀመሪያው ወቅት ከሻጮች ጋር አለመግባባት ይፈጠራል።
ክርክሩም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይደርሳል። በችሎቱም ሁለቱ ተከራካሪ ወገኖችና የገዢዎች ማለትም ዶክተር በዕውቀቱ 60 ዓመት የተጠጋቸው አዛውንት እህታቸውን ጨምሮ የባለቤታቸው ወይዘሮ መሠረት ሦስት እህትና ወንድሞች እንደተገኙ ዶክተር አሰፋ ይናገራሉ። ከሦስቱ መካከልም ሁለቱ ከ37 ዓመታት በፊት በወቅቱ የነበረውን ፖለቲካዊ ሁኔታ በመሸሽ ባሕር ማዶ በስደት የቆዩ መሆናቸውን ይገልፃሉ። ከአሜሪካ ከመጡ በሦስተኛው ቀናቸው የሚደረገውን ችሎት ለማድመጥ ይሄዳሉ።
ውሳኔው ቅር ያሰኛቸው ገዢዎች የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና በፌዴሬሽ ምክር ቤት የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ ዘንድ ቅስማቸውን የሰበረውን ውሳኔ ለማሳወቅ ይገባሉ። ችሎቱን ለመከታተል የሄዱት የቤተሰብ አባላትም ምን እንደተባሉ ለማወቅ በመጓጓታቸው ዶክተር በዕውቀቱን በጥያቄ ያጣድፏቸዋል። እርሳቸውም ለፕሬዚዳንቷ ቀርበው እንደተናገሩና አቤቱታቸውን ለጉባዔው ማቅረብ እንደሚችሉ እንደተነገራቸው ያሳውቋቸዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ችሎቱ አልቆ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ አልፏል የሚሉት ዋና አማካሪው፤ በወቅቱ ዶክተር በዕውቀቱ ስለ ጉዳዩ ለቤተሰቦቻቸው ሲያብራሩ በምን መረጃ ውሳኔው እንደተወሰነባቸው እንደማያውቁና ምናልባትም ዳኞቹን ያጭበረበረ አካል ሊኖር እንደሚችል ይናገራሉ። ይኼኔ በአቅራቢያው ያልፉ የነበሩትና በሰበር ችሎቱ ላይ የነበሩት አንደኛው ዳኛ ሰምተው ‹‹ምን አልክ›› በሚል ይጠይቋቸዋል። ዶክተር በዕውቀቱም ድርጊቱ እጅጉን አሳዝኗቸው የነበረ በመሆኑና ውሳኔውን የወሰኑባቸው ዳኛ ይህን መሰል ጥያቄ ሲጠይቋቸው ‹‹ምን አገባክ›› የሚል ምላሽን ይሰጣሉ።
ዳኛውም ከመቅጽበት በፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ የሚገኙትን የፌዴራል ፖሊስ አባላት ጠርተው እንዲያዙ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ። በመቀጠልም አራቱም የቤተሰብ አባላት በሦስተኛው ቀን በድጋሚ ችሎት ይሰየምና ‹‹ችሎት በመድፈር ወንጀል›› ባልና ሚስት ወይንም የፋብሪካው ገዢዎች ለስድስት ወራት እስራት እንዲሁም ቀሪዎቹ አራት የቤተሰብ አባላት በአንድ ወር ጽኑ እስራት ቅጣት ይፈረድባቸዋል። ከአንድ ወር በኋላም ሁለቱ ወደመጡበት አሜሪካ ሳይውሉ ሳያድሩ እንደተመለሱ የሚናገሩት ዶክተር አሰፋ፤ ‹‹እኔም ይህን መረጃ ልሰጥሽ የመጣሁት በወቅቱ የግል ስልክ እያናገርኩ ሁኔታው ከተከሰተበት አካባቢ በጥቂት ርቀቶች ላይ ስለነበርኩ ነው›› በማለት ድርጊቱን አስረዱኝ።
ዶክተር አሰፋ፤ ጉዳዩን ከፋብሪካው ሽያጭ ጀምሮ በደንብ እንደሚያውቁት ነው የሚናገሩት። ፋብሪካው እንደሚሸጥ ሲሰሙ ከድርጅታቸው ጋር ይሠራ ለነበረው አብሽካር ለተባለ የሕንድ ድርጅት በቢሾፍቱ ከተማ ላይ የሚገኝ ፋብሪካ ለመግዛትና ሊሠሩበት ማሰባቸውን ያሳውቁታል። ድርጅቱም ሐሳቡን በመቀበል ከሰዎቹ ጋር በመገናኘት ስምምነት ያደርጋሉ። ለሻጮችም በባንክ ሒሳብ ቁጥራቸው 200 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ገብቶላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ነገር ግን ድርጅቱ ሐሳቡን ይቀይርና አብሮ ከመሥራት ይልቅ ዶክተር በዕውቀቱና ባለቤታቸው ወይዘሮ መሠረት በጠቅላላ እንዲገዙት ይነግራቸዋል። በዚህም 22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ይገዙታል።
በስምምነቱ 22ነጥብ5 ሚሊዮን ብር ይግዙት እንጂ ከዚህ ውስጥ ሰባት ሚሊዮን ብር ደግሞ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚከፈል የብድር ዕዳ እንደነበረበትም ዋና አማካሪው ይናገራሉ። ለሽያጭም ያበቃው ይኸንኑ ዕዳውን መክፈል አለመቻሉም ነው ይላሉ። በዚህም ውል ስምምነቱ ከታሰረ በኋላ ገዢዎች ወደ ባንኩ በመሄድ ዕዳውን ወደራሳቸው ያዞሩታል። ወዲያውም ዕዳውን እንዳዞሩ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ይከፍላሉ። ሁለት ሚሊዮን ብር ደግሞ በሽያጩ ወቅት ለቅድሚያ ክፍያ ይፈጽማሉ። ከዚህ ውጪም ድርጅቱ ከተቋቋመበት 1996 ዓ.ም ጀምሮ እስከተሸጠበት ዕለት ድረስ ያልተከፈለ ግብር 800 ሺህ ብር በላይ ስለነበር ይህንንም በተመሳሳይ ይከፍላሉ። በጠቅላላም 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በክፍያና በዕዳ ይፈፀማል።
ባንክ ላይ ያለ ንብረትን መሸጥ አይቻልም ተብሎ በአክሲዮን ሙሉ በሙሉ ድርሻቸውን ወደ ፋብሪካው ገዢዎች አሸጋግረው ሻጮች እንደተሰናበቱ የሚናገሩት ዶክተር አሰፋ፤ ለዚህም የሰነድ ማስረጃዎች መኖራቸውንና በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲም ውልና ማስረጃ ተፈራርመው ሕጋዊ እንደሆነ ያስረዳሉ። ግዢው ከተፈፀመ በኋላም ፋብሪካው ያረጀ በመሆኑ አስፈላጊው ዕድሳትና በሰው ኃይል የማሟላት ሥራዎች እንዲሁም ጥሬ ዕቃዎች በማስገባት የመጀመሪያውን ምርት ማምረት ሲጀመር ሻጭ ወደ ፋብሪካው በማምራት ሁከት ይፈጥራሉ። የሸጡትም ፋብሪካውን እንጂ ‹‹ይዞታው የእኔ ነው›› የሚል ጥያቄንም እንዳነሱ ያስታውሳሉ።
ሽያጩ ሲፈፀም 8 ሺህ 290 ሜትር ካሬ ጅምር ሕንፃ ያለበትና ሌላኛው ደግሞ ፋብሪካው ያረፈበት 3015 ሜትር ካሬ ይዞታ ሲሆን፤ ይኸኛው ይዞታ ግን ከባንክ ብድር የተወሰደበት በመሆኑ ካርታውም በልማት ባንክ ተይዞ ይገኛል። ገዢዎችም የከፈሉት ዕዳ በዚሁ ፋብሪካው ባረፈበት ይዞታ የተወሰደውን ብድር እንደሆነ ዶክተር አሰፋ ያስረዳሉ። ይሁን እንጂ እንደታሰበው ሳይሆን ይቀርና ሻጭ የተቀጠሩትን ሠራተኞች በማባረር ብሎም አዲስ ጥበቃዎችን በማስገባት ድርጅቱን ዳግም በቁጥጥራቸው ስር ያውላሉ። ስለዚህ ውሉ ላይ ችግር ቢፈጠር ቅድሚያ በመወያየት ይፈታል የሚል አንቀጽ በመኖሩ ቅድሚያ ለሠላማዊ የችግር መፍቻ ዘዴ በመስጠት ሙከራ ይደረጋል። ሆኖም ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ይቀራል።
ገና ከጅማሬው ያላማረው የፋብሪካው ሥራም ለቀጣይም አዳጋች እንደሚሆን በማጤን ገዢዎች፤ ሻጭ ፋብሪካውን መሸጣቸው ቁጭት አሳድሮባቸው ሊሆን ስለሚችል በሚል በቀና መንፈስ በማሰብ ፋሪካውን ለመመለስ ነገር ግን የባንኩን ዕዳ መልሰው እንዲያዞሩና ገዢዎች የፈፀሟቸው ክፍያዎች እንዲመልሱላቸው ይጠይቃሉ። ነገር ግን ሻጭ በዚህም ሃሳብ ሳይስማሙ ይቀራሉ። በሽምግልና ሊፈታ ያልቻለውን ጉዳያቸውን ይዘው ሥራቸውን እያስተጓጎሉ ገዢዎች ውሏቸውን ከፍርድ ቤት እንዳደረጉም ዋና አማካሪው ይናገራሉ። በምስራቅ ሸዋ ዞን የስር ፍርድ ቤቶችም ጉዳዩን ተቀብለው ሲከራክሯቸው ይቆያሉ።
ጉዳዩ ይቀጥልና ፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ይደርሳል። ሻጭም በቅሬታቸው ፋብሪካው የተሸጠበት ውል እንዲፈርስ፣ አይፈርስም ከተባለ ደግሞ ገንዘቡ በአንድ ጊዜ እንዲከፈላቸው ብሎም በግቢው ውስጥ የቆሙ ባሶች ሊሠሩ ይችሉ የነበሩ በመሆናቸው ያጡት ገንዘብ ተሰልቶ ክፍያ እንዲፈፀምላቸው ይጠይቃሉ። ፍርድ ቤቱም አጠቃላይ ድርጅቱ ከተገዛበት 22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ውስጥ ቅድሚያ ክፍያ የተከፈለው ሁለት ሚሊዮን እንዲሁም ለባንክ የተከፈለው ሶስት ሚሊዮን ብር በማስላት አምስት ሚሊዮን በመቀነስ 17 ሚሊዮን ብር በአንድ ጊዜ መክፈል አለባችሁ በሚል ይወሰናል።
በውሉ መሠረት 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚቀርና ይህንኑ መክፈል ሲገባ የባንክ ዕዳውን ታሳቢ ባላደረገ መልኩ ቀጥታ የተከፈለውን ክፍያ ብቻ ተቀናሽ በማድረግ ፍርድ ቤቶቹ 17 ሚሊዮን ብር እንዲከፈል ይወስናሉ። በተያያዘ ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ያረፈበት 3015 ሜትር ካሬ ስፋቱ የሆነው ይዞታ ተመላሽ እንዲሆን ይወሰናል። እነዚህ ውሳኔዎችም የባንክ ዕዳውን ገዢው እንዲችል ብሎም ፋብሪካውም ወደ ሻጭ እንዲመለስ የሚያደርጉ ናቸው።
በአንድ ጊዜ ክፈሉ የተባለውም ሳይከፈል ስለቆየ የሚል ቢሆንም በውሉ ላይ እንደሰፈረው ግን በየዓመቱ 3 ነጥብ 75 ሚሊዮን ብር ለመክፈል ነበር።ሆኖም ሻጮች ወዲያው ክርክር በመጀመራቸው ባልተሠራበት ሁኔታ ሊከፈል አይችልም። በተጨማሪም ሻጮች በውል ስምምነቱ ላይ በገቡት ስምምነት መሠረት ግዴታቸውንም አለመወጣታቸውንና የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ወይንም ካርታ ስም ዝውውር እንዳላደረጉ ዋና አማካሪው ያስረዳሉ። ውሳኔውም ቦታውን አስረክቡ ነገር ግን ደግሞ ውሉ የፀና ይሆናል የሚል በመሆኑ ውሉ የፀና የሚሆን ከሆነ ፋብሪካው ያረፈበትን ይዞታ እንዴት ማስረከብ ይቻላል? የሚል ጥያቄም ያጭርባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት የፋብሪካውን ብድር ከፍለው 200 ሺህ ብር ብቻ እንደሚቀር የሚገልጹት ዋና አማካሪው፤ ገዢዎች እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው ወለድ ሲሰላ 12 ሚሊዮን ብር ቅጣት ወለድ እንዲከፈል የሚያደርግ ሲሆን፤ባንክ ላይ የተከፈለው የባንክ ዕዳ እንዲሁም ሌሎቹ ክፍያዎች ሲሰሉ 39 ሚሊዮን ብር ገዢ እንዲከፍልና ፋብሪካውንም እንዲያስረክብ የሚያደርግ መሆኑን ዶክተር አሰፋ በሃዘን ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት የባንክ ዕግድ እንደደረሳቸውና የተለያዩ ድርጅቶችም ኪሳራ ውስጥ በመውደቃቸው ያበደሯቸውን ብድር እንዲመልሱ እያስጨነቋቸው እንደሆነ ይናገራሉ። የተሰጠውም ውሳኔ ፍትሐዊ ያልሆነና የተዛባ በመሆኑ ብዙ ኪሳራ ላይ መውደቃቸውን የሚመለከተው አካል እንዲያይላቸው በመማፀን የሰነድ ማስረጃዎች ያወጡ ጀመር።
የተለያዩ ሰነዶች
የግብር ከፋይነት ማረጋገጫ፣ የንግድ ፈቃድ እንዲሁም የተለያዩ ደብዳቤዎች ጉዳዩን አስመልክቶ ከሚያብራሩ የፍርድ ቤት መዝገቦች ባሻገር የተመለከትናቸው ሰነዶች ናቸው። ሕዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን ለመሸጥና ለመግዛት የተደረገ ውል ስምምነት ይገኛል።በውል ስምምነት ሰነዱ ላይም ለገዥ በሕግ አግባብ ባለቤትነቱን ሙሉ በሙሉ ለማስተላለፍ የተደረገ የሽያጭ እና የውል ስምምነት እንደሆነ ያረጋግጣል። በዚህም ገዢዎች የፋብሪካውን ዋጋ ብር 22 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ለመክፈል ግዴታ እንደገቡና ይህንንም በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በመክፈል ለማጠናቀቅ እንደተስማሙ ያመለክታል።
የመጀመሪያ ክፍያ ግን ሁለት ሚሊዮን ብር እንደሚሆን ያስቀምጣል።በተያያዘ ሻጭ በድርጅቱ ስም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በብድር የወሰዱትን አጠቃላይ ዕዳ ብር ሰባት ሚሊዮን በመረከብ በውሉ መሠረት ግዴታቸውን ለመፈፀም መስማማታቸው ከውሉ ስምምነት ሰነድ ላይ ይነበባል።ታኅሳስ 16 ቀን 2005 ዓ.ም በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ የተደረገ ስብስባ አስመልክቶ የተያዘ ቃለጉባዔ ሌላኛው ሰነድ ነው። ቃለጉባዔው የማህበሩ አባል የሆኑት ኢንጂነር ጌታቸውና ወይዘሮ ሐረግነሽ በማህበሩ ውስጥ ያላቸውን ጠቅላላ ብር ለዶክተር በዕውቀቱና ወይዘሮ መሠረት በማስተላለፍ ከማህበሩ እንደተሰናበቱ ሰነዱ ያስነብባል።
የቢሾፍቱ ከተማ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ አዳማ ዲስትሪክት በቀን 6/5/2011 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 2886/3625/2 ወጪ አድርጎ የሰጠው መረጃ ሌላኛው ሰነድ ነው። በሰነዱ በደብዳቤ ቁጥር አዲ/028/2019 በቀን 26/04/2011 ዓ.ም ፋብሪካው በካርታ ቁጥር 83/27 እና 83/6 በየትኛው ላይ እንዳረፈ መጠየቃቸውን ያስታውሳል። ይህንንም በመውሰድ ጽሕፈት ቤቱ የማጥራት ሥራ የሠራ ሲሆን፤ በድርጅቱ ስም ያለው የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ወይም ካርታ በቀን 17/06/1996 የተሠጠው የካርታ ቁጥሩ 83/27 ነው። ሆኖም ግን በተደረጉ ልኬቶችና ማጥራቶች በሻምበል ጌታቸው ስም በሚገኘው የካርታ ቁጥሩ 83/6 በሆነው 3015 ሜትር ካሬ መኖሩንና ፋብሪካውም ሙሉ በሙሉ በዚህ ይዞታ ላይ ያረፈ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ደብዳቤው ይገልፃል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቀን 10/05/2011 ዓ.ም በቁጥር አዲ/089/2019 ለድርጅቱ በላከው ደብዳቤ ደግሞ ከሕዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም ወይንም የፋብሪካው ግዢና ሽያጭ ውል ከታሰረበት ዕለት ጀምሮ ብድሩን ወደራሳቸው ያዞሩት ገዢ ለባንኩ 5 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር መክፈላቸውን ያስረዳል። በተጨማሪም የቢሾፍቱ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ለባንኩ ይዞታዎቹን አስመልቶ ደብዳቤ መላኩን ይገልፃል። በዚህም በድርጅቱ ስም የተመዘገበ በ8 ሺህ 290 ሜትር ካሬ ላይ የሚገኝ ይዞታ መኖሩንና በይዞታው ላይ ጅምር ሕንፃ ያረፈበት መሆኑን እንዲሁም በሻጭ ሻምበል ጌታቸው ስም የተመዘገበ ስፋቱ 3015 ሜትር ካሬ ላይ ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ያረፈ መሆኑን ያብራራል።
የፍርድ ሂደት
የፋይል ቁጥር 38398 የሆነ በቀን 04/03/2007 ዓ.ም ያለው ሰነድ ሌላኛው ማስረጃ ነው። የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሳሽ ጌት እሸት ዲተርጀንት ማኑፋክቸሪንግ እና ፓኬጂንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በተከሳሾች ኢንጂነር ጌታቸው እሸቱና ባለቤታቸው ወይዘሮ ሐረግነሽ መኮንን በቀረቡበት ችሎት ላይ መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ መስጠቱን ያመለክታል። የከሳሽ ባለንብረትም በስምምነቱ መሠረት የንግድ ፍቃድ ከቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የንግድ ጽህፈት ቤት እንዲሁም የንግድ ፈቃድ ማስረጃ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በማውጣት ፋብሪካው የማምረት ሥራ ላይ እንደሚገኝ ከሳሽ ጌት እሸት ዲተርጀንት ማኑፋክቸሪንግ እና ፓኬጂንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፋይል ቁጥር 38398 የሆነ በቀን 04/03/2007 ዓ.ም የወጣው ሰነድ ላይ ያብራራል። ይሁን እንጂ ተከሳሾች ድርጅቱ የሚገኝበትን ካርታና ፕላን ሳያስረክቡን ስለቀሩ ተከሳሾች ፋብሪካው ያረፈበትን ስፋቱ 3015 ካሬ ሜትር የሆነ የካርታ ቁጥሩ 83/6 የሆነ በአንደኛ ተከሳሽ ስም ተመዝግቦ የሚገኘውን ቦታ ባለቤትነት ስም ወደ ከሳሽ ስም እንዲያዘዋውሩ ሲጠየቁ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ይገልፃል።
በስምምነቱ መሠረት ፋብሪካውን በገዙት ዶክተር በዕውቀቱ ስም ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የወጣ የንግድ ፍቃድ እንዲሁም ከፌዴራል መንግስት የንግድ ሚኒስቴር በዶክተር በዕውቀቱ ስም ተመዝግቦ የሚገኝ የንግድ ምዝገባ የምስክር ወረቀት ከሳሾች ፋብሪካውን በሕጋዊ አግባብ የግዢ ውል ለመፈፀማቸው ያሳያል ሲል መዝገቡ ያትታል። በመሆኑም ተከሳሾች የጌት እሸት ዲተርጀንት እና ፓኬጂንግ ፋብሪካ እንዲሁም ፋብሪካው የሰፈረበትን ቦታ ስም ወደ ከሳሾች ዶክተር በዕውቀቱና ባለቤታቸው ወይዘሮ መሠረት ያዘዋውሩ በሚል ውሳኔ ማረፉን ከሰነዱ ይነበባል።
የመዝገብ ቁጥር 153204 በቀን 27/06/2010 ዓ.ም ከሳሾች የፋብሪካው ሻጮች ማለትም እነ ኢንጂነር ጌታቸው ሆነው ተከሳሾች ደግሞ እነ ዶክተር በዕውቀቱ ለችሎት መቅረባቸውን የሚያሳየው ሌላኛው ሰነድ ነው። ተከሳሾች ማለትም የፋብሪካው ገዢዎች ከከሳሾች ላይ የገዙትን ማህበር በውሉ አንቀጽ 3/1/ መሠረት ርክክብ ከመደረጉ አስቀድሞ የያዙ ሲሆን፤ከተሸጠው ድርጅት አቅራቢያ የሚገኘውን በ3015 ካሬ ሜትር የሆነውን የከሳሾች የግል ንብረት በሕገወጥ መንገድ ጠቅልለው ይዘዋል የሚልም ክስ እንደቀረበባቸው ሰነዱ ያስነብባል።
ፍርድ ቤቱም በዕለቱ በግራ ቀኙ መካከል የተደረጉ ክርክሮችን ካደመጠና የሰነድ ማስረጃዎችን ከመረመረ በኋላ ከሳሾች ውሉ በሕግ ፊት የፀና አይደለም በማለት ያቀረቡት ክርክር የሕጉን መንፈስና ዓላማ ያልተከተለ ነው ሲል ይተቸዋል። በዚህም ውሉ በሕግ ፊት የፀና አይደለም የሚያስብል የሕግ መሠረትም የለም ሲል ይወስናል።ከዚሁ ጎን ለጎን ተከሳሾች በአጠቃላይ በሽያጭ ውሉ ላይ ከሠፈረው ፋብሪካው ከተሸጠበት 22 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ውስጥ ውሉ በተደረገበት ወቅት በድምሩ 4 ሚሊየን 800 ሺህ 48 ብር መክፈላቸውንና ቀሪውን ገንዘብ ያልከፈሉ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙ ባደረጉት ክርክርና ባገላበጣቸው የሰነድ ማስረጃዎች ይገነዘባል። በመሆኑም ተከሳሾች ከሳሾች ግዴታቸውን አልፈፀሙም የሚል ክስ ሳያቀርቡ የቀሩ በመሆኑ በዚህ አግባብ አግባብነት ባለው የሕግ አካሄድ መብታቸውን የማስከበር መብት ያላቸው ሆኖ በተያዘው ጉዳይ ግን ተከሳሾች ፋብሪካውን ከገዙበት አጠቃላይ ዋጋ ላይ የከፈሉትን ብር ተቀናሽ ተደርጎ ቀሪውን ብር ከሕጋዊ ወለድ ጋር የመክፈል ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገልፃል።
ሌላኛው የክርክር ጭብጥ የነበረው ተከሳሾች የድርጅቱ አካል ያልሆነና በ3015 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ይዞታ እንዲሁም በይዞታው የሚገኙ የተለያዩ ንብረቶችን ይዘዋል የሚል ሲሆን፤ ተከሳሾች አጥብቀው የሚከራከሩት ፋብሪካውን ሲገዙ በአጠቃላይ 11 ሺህ 305 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ይዞታ ላይ የተቋቋመን ፋብሪካና ከፋብሪካው ጋር የተያያዙ ንብረቶችን ጭምር ነው የሚል ነው። ይህን በተመለከተም በዚህ ችሎት ላይ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት የፋብሪካው ገዢዎች በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 38398 ክስ አቅርበው ፍርድ ቤቱም በቀን 04/03/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሻጮች ስም በቢሾፍቱ ከተማ ቀበሌ 01 የቦታ መለያ ቁጥር 83/6 በ3015 ካሬ ሜትር የሆነውን ይዞታም የድርጅቱ አካል ሆኖ በሽያጩ ለገዢዎች የተላለፈ መሆኑን እንዳረጋገጠ ያብራራል።
በቦታ መለያ ቁጥር 83/6 በ3015 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ይዞታም ዋናው ፋብሪካ ያረፈበት ሆኖ ለተከሳሾች ማለትም ለገዢዎች የተላለፈ መሆኑን የሚያሳይ የፍርድ ቤት ውሳኔ በማስረጃነት የቀረበ በመሆኑና ከሌሎች ማስረጃዎች ይበልጥ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ ስለተገኘ ከሳሾች ይህን ይዞታ ከሕግ ውጪ በቁጥጥራቸው ሥር አድርገዋል በማለት የቀረቡትን ክርክርና ማስረጃ ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀበለው ያትታል።
ከሳሾች በሌላ በኩል ባቀረቡት ክስ ተከሳሾች ሁለት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶብሶችና አንድ ኤንትሬ ተሳቢ ተሽከርካሪ አለአግባብ በቁጥጥር ስር በማዋላቸው ተሽከርካሪዎቹንና የተቋረጠውን ጥቅም ሊከፍሉ ይገባል የሚል ነው። ፍርድ ቤቱም የሰነድ ማስረጃዎችን አገላብጦ ባገኘው መረጃ መሠረት ድርጅቱ ለተከሳሾች በሽያጭ ከተላለፈ በኋላ ተከሳሾች በተለያዩ ጊዜያት ለከሳሾች ወይንም ለሻጮች በሕዳር 27 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲሁም በሰኔ 16 2006 ዓ.ም የፃፏቸው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች እንዳሉ ይጠቁማል። በደብዳቤዎቹም በፋብሪካው ውስጥ የቆሙት ባሶች የከሳሾች የግል ንብረት ወይም የድርጅቶቹ ንብረቶች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሊብሬ ይዘው በመቅረብ የግል ንብረቶቻው ከሆኑ ማስጠንቀቂያው በደረሳቸው 10 ቀናት ውስጥ ከጊቢው እንዲያስወጧቸው ይጠይቃሉ። አልያ ግን ተሽከርካሪዎቹ በድርጅቱ ውስጥ ለቆሙበት ኪራይ እንደሚከፍሉ መጠየቁን ፍርድ ቤቱ ተገንዝቧል ይላል። በመሆኑም በዚህ ችሎት ላይ ከሳሽ የነበሩት ኢንጂነር ጌታቸው በወቅቱ
ይግባኝና ሰበር
ተሽከርካሪዎቹን መውሰድ አልያም ማስወሰድ እየቻሉ ዝም ብለው ቆይተውና እንደማያውቁ ሆነው ተከሳሾች ያለ አግባብ ተሽከርካሪዎቹን በቁጥጥራው ሥር አድርገው በመቆየታቸው ያቀረቡትን ጥያቄ አልተቀበለውም።
ሕዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም የፋብሪካው ገዢዎች ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ ሌላ የተመለከትነው ሰነድ ነው። በአቤቱታቸውም በስር ፍርድ ቤቶች በዚህ ችሎት ተጠሪ ሆነው የቀረቡት የፋብሪካው ሻጮች ከሳሽ የነበሩና ገዢዎች ደግሞ ተከሳሽ እንደነበሩ ያትታል።በየደረጃው የነበረውን ክርክር በማብራራትም ገዢዎች እንዲሁም ሻጮች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቅረባቸውን ያስረዳል።
የፋብሪካው ገዢዎች በአቤቱታቸው ሻጮች ውሉ እንዲፈርስላቸው መጠየቃቸውን ይህ አይሆንም ከተባለ ደግሞ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እንዲከፈላቸው ጠየቁ እንጂ 17 ሚሊዮን 699 ሺህ 952 ብር እንዲከፈላቸው አልጠየቁም። ይህም ባልተጠየቀ ዳኝነት መጠንና ዳኝነት እንዲከፈል በማለት የተወሰነው ውሳኔ አግባብ ያልሆነና በሽያጭ ውሉ ላይ በግልጽ የተደነገገውን የአከፋፈል ሁኔታ ውጪ በአንድ ጊዜ እንዲከፈል ማለቱ አግባብ አለመሆኑን ያብራራሉ። ይህም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መዝገብ ቁጥር 33945 ባልተጠየቀ ዳኝነት የሚሰጥ ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ነው በማለት የሰጠውን የሕግ ትርጉም የሚቃረን እንደሆነ ያብራራል።
የሰ/መ/ቁ.166294 ሚያዚያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት ሁለቱ ወገኖች ቅሬታቸውን ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ማቅረባቸዉን ይገልፃል። በምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3015 ሜትር ካሬ ይዞታ የፋብሪካው አካል ተብሎ በመዝገብ ቁጥር 38398 የተሰጠው ውሳኔም በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 189908 መሻሩ እንደተረጋገጠም ያስረዳል። በሌላ በኩል ገዢዎች የፋብሪካ ሽያጭ ቀሪ ገንዘብ ብር 17 ሚሊዮን 699 ሺህ 952 ብር ከወለድና ወጪና ኪሳራ ጋር ለሻጭ እንዲከፍሉ የተሰጠው ውሳኔ ተገቢ በመሆኑ ሊፀና ይገባልም ይላል።
ሰበር ችሎቱ፤ ገዢዎች አለአግባብ ከተጠየቀው ዳኝነት ውጪ እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው የገንዘብ መጠንና ከውሉ ውጪ በአንድ ጊዜ ክፈሉ መባላቸው ያቀረቡት ቅሬታ እንዲሁም በሥር ፍርድ ቤቶች ፍሬነገር እንዲሁም ሕጉን ያልተከተለ ባለመሆኑ ሰበር ችሎቱ ተቀባይነት የለውም በማለት ከነወለዱ እንዲከፍሉ መወሰኑን ሰነዱ ያሳያል። በተያያዘ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የካርታ ቁጥሩ 83/6 የሆነው 3015 ሜትር ካሬ ይዞታ የተሸጠው ፋብሪካ አካል አይደለም ብሎ መወሰኑን በመግለጽ፤ ችሎቱ መደምደሚያው ላይ የደረሰው ፍሬ ነገሩን ለማጥራትና ማስረጃውን በመመዘን ውሳኔ ላይ ለመድረስ በሕግ በተሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን መሆኑን ያብራራል። ሰበር ችሎቱም ይዞታው የተሸጠው ፋብሪካ አካል አይደለም በሚል የተሰጠው ውሳኔ ላይ የተፈፀመ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለም በሚል በአብላጫ ድምጽ ይወስናል። ይህም የሆነው ደግሞ በችሎቱ ተሰይመው ከነበሩት አምስት ዳኞች መካከል አንደኛው በሃሳብ ልዩነት በመውጣታቸው ነው።
ሌላኛው ሰነድ ግንቦት ሰባት ቀን 2011 ዓ.ም የሰበር መዝገብ ቁጥር 166294 ደግሞ ችሎቱ ሊቀርብ የቻለው ግንቦት አምስት ቀን 2011 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሻጭና በገዢ መካከል የነበረው የፍትሐብሔር ክርክር ውሳኔ አግኝቶ ከተነበበ በኋላ የፋብሪካው ገዢ የሆኑት ዶክተር በዕውቀቱና ባለቤታቸው ወይዘሮ መሠረት እንዲሁም አራት የቤተሰብ አባላቶቻቸው ከሕግ ውጪ ባደረጉት ድርጊት መሆኑን ያብራራል። በወቅቱ ዳኞች ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ሲመለሱ ባልና ሚስት ሌቦች እያሉ በመሳደብ ሌሎች ቀሪ የቤተሰቡ አባላትም ይህንኑ በሚደግፍ ሁኔታ ‹‹ዕውነት ነው ሌቦች ናችሁ›› በማለት መደገፋቸውን መዝገቡ ይገልፃል። ድርጊታቸውም የችሎቱን ዳኞች እና የፍርድ ቤቱን ክብር ያወረደና ሌሎች ተገልጋይ የማሕበረሰብ አካላት በፍርድ ቤቶች ላይ ዕምነት እንዳይኖራቸውና ዳኞች ላይም ጥርጣሬ እንዲፈጠርባቸው ለማድረግ በማሰብ የተፈፀመ በማለት ይኮንነዋል። በተለይም አንደኛ ተከሳሽ የችሎቱን ክብር በሚጎዳ መልኩ ያንጓጠጡና አልታዘዝም ባይነታቸውን በግልጽ ያሳዩ በመሆኑ ችሎቱን በመድፈራቸው በማረፊያ ቤት ቆይተው ለዚህ ችሎት መቅረባቸውን ያወሳል።
ስድስቱ የቤተሰብ አባላትም ባልና ሚስትን ወይንም የፋብሪካውን ገዢዎች ጨምሮ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 449/2 እንዲሁም በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ/ 480 እና 481 ስር ጥፋተኛ መባላቸውን መዝገቡ ያስቀምጣል። በዚህም ከሌሎች አጥፊዎች በተለየ ሁኔታ ድርጊቱን የፈፀሙት ዶክተር በዕውቀቱና ወይዘሮ መሠረት ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ የሁለቱን ስድብና ማንጓጠጥ በመደገፍ ልክ ነው በማለት እንዲሁም የሚመጣውንም ውጤት አብረው ለመቀበል በማሰብ የፍርድ ቤቱን እና የዳኞችን ክብር ነክተው የችሎት መድፈር ወንጀል እንደፈፀሙ ያረጋግጣል። በመሆኑም ባልና ሚስት ለስድስት ወራት ቀላል እስራት እንዲሁም ሌሎቹ አራት የቤተሰብ አባላት ደግሞ በአንድ ወር ቀላል እስራት እንዲቀጡና ለሌሎችም ማስተማሪያ እንዲሆን ቅጣት ያረፈባቸው መሆኑን መዝገቡ ያስረዳል።
የፍርድ አፈፃፀም
የፍርድ አፈፃፀም ዳይሬክቶሬት መዝገብ ቁጥር 32438 በቀን 20/10/2011 ዓ/ም በዕለት ጉዳዮች መከታተያው ላይ እንዳሰፈረው፤ ውሳኔውን ለማስፈፀም ከስፍራው ቢገኙም ይዞታው ሲለካ ችግር ያጋጠመ በመሆኑ ርክክቡን ሳያስፈፅሙ መመለሳቸውን ሰነዱ ያመለክታል።
ሻጮችስ ምን ይላሉ?
በጉዳዩ ላይ የፋብሪካውን ሻጮች ለማነጋገር በተደጋጋሚ ሙከራ ካደረግን በኋላ ወይዘሮ ሐረግነሽን አግኝተናቸዋል ።በጉዳዩም ላይ የነበረዉን ሂደት አብራርተዉልናል።ሆኖም የተጻፉ ማስረጃዎችንና በጠበቃቸዉ በኩል እንጂ የሰጡንን መረጃ እንድንጠቀም እንደማይፈቅዱልን አሳዉቀዉናል።
የሚመለከተው አካል
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ፈልገን ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቀናን። የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንትም በተለይም ከችሎት መድፈር ጋር ተያይዞ በተወሰነው ውሳኔ ሳቢያ ጉዳዩን በጨረፍታ እንደሚያውቁት በመግለጽ መዝገቡን አገላብጦ በመመልከት ምላሽ እንዲሰጠን ወደ ፍርድ ቤቱ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሠለሞን እጅጉ መሩን። ዳይሬክተሩ በጉዳዩ ላይ የተወሰኑ ውሳኔዎችንና የፍርድ ሒደቶችን የሚያብራሩ መዝገቦችን በማገላበጥ፤ ለሰበር ችሎቱ ገዢዎች ማለትም ዶክተር በዕውቀቱ፣ ባለቤታቸው ወይዘሮ መሠረትና ድርጅቱ ጌት እሸት ዲተርጀንት ኃፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አመልካቾች እንደነበሩ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ሻጮችና አፍሮ ትሮሊ ባስና አፍሮ ኤዥያን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ተከሳሽ ወይንም ተጠሪ ሆነው በመዝገብ ቁጥር 166294 ላይ ይቀርባሉ።
የሰበር ችሎቱም ጉዳዩን መርምሮ የስር ፍርድ ቤት ማለትም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ማፅናቱን ይገልፃሉ። ከዛ ቀደም ብሎ ግን ክርክሩ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች ሲደረግ እንደነበር የመዝገቡን የውሳኔ ግልባጭ በመመልከት ያወሳሉ። ሰበር ችሎቱም በመዝገቡ ላይ የታየ የሕግ ስህተት አለመኖሩን ነው የወሰነው። በየደረጃው በነበረው የፍርድ ሂደት ያረፉት ውሳኔዎች ብዙ ልዩነት የላቸውም። በመሆኑም ፍትሕ ተዛብቷል ለማለት የሚያስችል ውሳኔ ተሰጥቷል የሚል ዕምነት በፍርድ ቤቱ እንዳልተያዘም ያሳውቃሉ።
እኛም ከነበረው አጠቃላይ ሒደትና ከሽያጭና ግዢ ውሉ በመነሳት ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ያረፈው በ3015 ሜትር ካሬው ላይ እንደሆነ እየታወቀ፣ ይህን ይዞታ ለሻጮች ነው የሚገባው ብሎ ውሳኔውን ማፅናት ፋብሪካውን ተመላሽ እንዲሆን ማድረግ በመሆኑ አንድ ድርጅት ከተሸጠ በኋላ ሊመለስ ይችላል ወይ? ከክፍያው ጋር ተያይዞ ባልተጠየቀ ዳኝነት ከነወለዱ 39 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ውሳኔ እንዳረፈባቸው ገዢዎች ቅሬታ ያቀርባሉና ይህ እንዴት ይታያል ስንል የዳይሬክተሩን ምላሽ መነሻ በማድረግ ጥያቄ አቀረብንላቸው።
ዳይሬክተሩ በምላሻቸው፤ ውሳኔው ፋብሪካው ተመላሽ እንዲደረግ እንደማይል ይናገራሉ። ውሉ እንዲፀናና ከውሉ ጋር ተያይዞ ደግሞ የተደረጉ የቃለ ጉባዔ ለውጦች ጋር በተያያዘ ክፍያ በመክፈልና ባለመክፈል የመጣ ክርክር አለ። ይህም አለመግባባት ውሉ ይፍረስ ቃለ ጉባዔውም ይሰረዝ የሚል ጥያቄን አስነስቷል። ፍርድ ቤቱም እነዚህን ጥያቄዎች አልተቀበለም። ነገር ግን ገዢዎች መክፈል ያለባቸውን ክፍያ መፈፀም እንዳለባቸው ውሳኔ ወስኗል። ክፍያውም መክፈል በነበረባቸው ወቅት ባለመፈፀማቸው ሻጮች የደረሰባቸው ኪሳራ ወይም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሊያስተካክል በሚችል መልኩ ዕዳው ከነሕጋዊ ወለዱ እንዲከፍሉ መወሰኑን ትክክል እንደሆነ ያስረዳሉ።
ሌላኛው ጥያቄያችን ችሎት መዳፈር ጋር ተያይዞ የተወሰነው ውሳኔ አስመልክቶ ሲሆን፤ ዳይሬክተሩም ችሎት መዳፈር ማለት ችሎቱ መሠረታዊ ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን ማድረግ እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህም በተለያዩ መንገዶች ሊገለጽ ይችላል። በአንድ በኩል ችሎቱ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ሲሆን፤ ከዚህ በዘለለ ደግሞ ችሎቱ ማግኘት ያለበትን ክብር እንዳያገኝ የሚያደርጉ ማንኛውም ተግባራት እንደ ችሎት መዳፈር ይቆጠራሉ፤ ሲሉም ያብራራሉ። በዚህም ገዢዎች ችሎቱ ያሳረፈውን ውሳኔ ተነቦላቸው ካደመጡ በኋላ ዳኞች ሥራቸውን ጨርሰው በሚወጡበት ወቅት በፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ አላስፈላጊ ንግግርና ዛቻዎችን እንዲሁም ፉከራዎችን ሲያሰሙ ነበር።
አንደኛ ፍርድ ቤት ውስጥ በመሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ዳኞቹ ችሎት ላይ አይሁኑ እንጂ የዳኝነት ሥራቸው ላይ እያሉ የፈፀሙት ድርጊት ፍርድ ቤቱን ያላከበረ ነው ሲሉም ዳይሬክተሩ ተግባሩን ያወግዛሉ። ቃሉ እንደሚለውም በችሎት ላይ ብቻ ሳይሆን ፍርድ ቤቱ የሚገባውን ክብር መስጠት በመሆኑ ይህን የሚጋፋ ድርጊት ተፈጽሞ ከተገኘ ችሎት መዳፈር ይባላል። በችሎቱ የተሰጠው ውሳኔ መተቸት ቢቻልም፤ ትችቱ ግን ችሎቱን ባከበረ ሁኔታ መሆን ይጠበቅበታል። ከዚህ አንፃር ይህን ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉት ግለሰቦች ድርጊታቸው እስከ አምስት ዓመት ሊያስቀጣ የሚችል ሆኖ ሳለ ችሎቱ የሰጠው ቅጣት በጣም አነስተኛ መሆኑን በመግለጽ፤ ውሳኔው ግን ሊከበር እንደሚገባ ይናገራሉ።
በባለሙያ ዕይታ
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ በፌዴራል ማንኛውም ፍርድ ቤቶች ጠበቃና የሕግ ባለሙያ ጉዳዩን አስመልክቶ በሠጡት ማብራሪያ፤ ለዚህ ሁሉ ክርክር መነሻ የሆነው ሕዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም የተደረገው ግዢና ሽያጭ ውሉ ነው ሲሉ ያስረዳሉ። ውሉ ላይ ምን እንደሚሸጥ፣ ይዞታ ይሁን አክስዮን በግልጽ አያስቀምጥም። ይዞታ ከሆነ ካርታ ቁጥሩ ሊካተት ካልሆነና ሰነድ አልባ ከሆነ ደግሞ አዋሳኞቹና ምን ያክል ስፋት እንዳለውና እያንዳንዱ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች ሊጠቀሱ ይገባም ነበር ሲሉ ይጠቁማሉ። በዚህ የውል ክፍተት መነሻነትም ያለአግባብ ተጠቃሚ የሆነ አካል እንዳለ ከሰነድ ማስረጃዎቹ በመመርመር ይተቻሉ።
ዝርዝር ውሳኔዎቹን በተመለከተም ሰበር የተሠጠውን ስልጣን ተጠቅሞ የተወሰነ መሆኑን የሚናገሩት ጠበቃው፤ የመጨረሻ የሕግ አካል የወሰነው ውሳኔ በመርህ ደረጃ ትክክል ነው ይላሉ። አያይዘውም ሰበር ሰሚ ችሎቱ ከተጠየቀው ዳኝነት ውጪ እንደወሰነ ይናገራሉ። ይህም ትክክለኛ አይደለም በማለት ሻጮች የጠየቁት ዳኝነት 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በመሆኑ ዳኝነቱ ሊታይ የሚገባውም ውሳኔ ሊያርፍም ይገባ የነበረው በዚሁ የገንዘብ መጠን ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግን 17 ሚሊዮን ብር በምን መነሻ እንደወሰነ አይታወቅም። ከዚህ ጋር በተያያዘም በወቅቱ በችሎቱ ላይ ከተሰየሙት አምስት ዳኞች መካከል አንዱ ዳኛ በሐሳብ ልዩነት መውጣታቸው ትክክለኛ ነው ሲሉ ይጋራሉ።
የሐሳብ ልዩነት
ሚያዚያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በሰበር መዝገብ ቁጥር 166294 እንደሚያመለክተው፤ በችሎቱ ተሰይመው ከነበሩት አምስት ዳኞች መካከል አንደኛው የሃሳብ ልዩነት ነበራቸው። በዚህም ያልተከፈለውን የሽያጩን ዋጋ 17 ሚሊዮን 699 ሺህ 952 ብር ውሉ ከተደረገበት ዕለት ጀምሮ ከሚታሰብ ወለድ ጋር በአንድ ጊዜ ለሻጮች ይክፈሉ በሚል በአብላጫ ድምጽ በተወሰነ ውሳኔ እንደማይስማሙ በግልጽ ያስቀምጣሉ።
ዳኛው፤ በሃሳብ ልዩነታቸው ላይ በየደረጃው የነበረውን የፍርድ ሂደትና የክርክሩ መነሻ በመመልከት ከሕግ ድንጋጌዎች አንፃር ፈትሸዋቸዋል። በዚህም የስር ፍርድ ቤቶች የደረሱበት ድምዳሜ ‹‹የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተከራካሪ ወገኖች በዝርዝር ባላቀረቡት ወይም በግልጽ ባላመለከቱት ጉዳይ ላይ ፍርድ መስጠት አይችልም›› የሚለውን የፍ/ብ/ሥ/ሥርዓት ሕጉን አንቀጽ 182(2) ድንጋጌ እንዲሁም የገዢና ሻጭን ስምምነት መሠረት ያደረገ እንዳልሆነ ይተቻሉ። የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገዢዎች ገንዘቡን እንዲከፍሉ ሲወስን፤ በሻጭና በገዢ መካከል በተደረገው ውል መሠረት አገናዝቦ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቀሪውን ገንዘብ ከገዢዎችና ከሻጭ ማን ሊከፍል እንደሚገባ ግን አልወሰነም ሲሉም ያብራራሉ።
ገዢዎች ከክፍያው ጋር ተያይዞ ሻጮች በውሉ ላይ በገቡት ውል መሠረት ግዴታቸውን አለመወጣታቸውን አንስተው መከራከራቸውን በሃሳብ ልዩነታቸው ላይ ያሰፈሩት ዳኛ፤ የስር ፍርድ ቤቱ ሻጮች የሚጠበቅባቸውን ግዴታ መወጣት አለመወጣታቸውን አረጋግጦ ውጤቱን መወሰን ሲገባው ገዢዎች ራሱን የቻለ ክስ አቅርበው ዳኝነት አልጠየቁም በሚል ምክንያት ያቀረቡትን ክርክር ውድቅ ማድረጉን ያነሳሉ። ይህም የስር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የደረሰበት ድምዳሜ በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 1757 እና 1771 እንዲሁም ሕግና ግራ ቀኝን ክርክር መሠረት በማድረግ ትክክለኛ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችላቸውን ጭብጥ ይዘው ጉዳዩን ማጣራት እንደሚገባቸው በፍ/ብ/ሥ/ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 246(1) እና 247 ላይ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ያላገናዘብም ነው ይላሉ።
ዳኛው፤ በአጠቃላይ 3015 ሜትር ካሬ የሆነውን ቦታ በተመለከተ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት በፍሬ ነገር ደረጃ አረጋግጦ የሰጠውን ውሳኔ በመቀበል አብላጫው ድምጽ የደረሰበትን ድምዳሜ እንደሚቀበሉት ማስፈራቸው ከመዝገቡ ይነበባል። ገዢዎች እንዲከፍሉ የተወሰነው ገንዘብ ግን የተደረጉ ክርክሮችን እንዲሁም ለጉዳዩ አግባብ ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር ተገናዝቦና በአግባቡ ተጣርቶ ባለመሆኑ እንዳልተስማሙበት በሐሳብ ልዩነታቸው ላይ ያብራራሉ። በመሆኑም ገዢዎች በውሉ መሠረት 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብሩን ለሻጮች ሊከፍሉ የሚችሉበትን ሁኔታ በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 1769፣ 1770 እና 1785(1) በማድረግ እንዲወሰን መዝገቡ ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍ/ብ/ሥ/ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 343(1) መሠረት ሊመለስለት ይገባል ማለታቸው የሐሳብ ልዩነታቸው በመዝገቡ ይነበባል።
ችሎት መዳፈር?
በጉዳዩ ላይ ሙያዊ አስተያየታቸውን የሰጡን ጠበቃ ከፋብሪካው ክርክር ባሻገር ገዢዎች ችሎት ተዳፍረዋል በሚል ያረፈባቸውን ቅጣት ግን በፍጹም ትክክለኛ ያልሆነና የግለሰብ የግል ስሜት የተንፀባረቀበት ነው በማለት ዳይሬክተሩ የሰጡትን አስተያየት ውድቅ ያደርጋሉ። በሰበር መዝገብ ቁጥር 166294 ግንቦት ሰባት ቀን 2011 ዓ.ም በተብራራው መሠረትም ገዢዎች ወይንም ለችሎቱ አመልካች የነበሩት ዶክተር በዕውቀቱ፣ ወይዘሮ መሠረትና አራቱ የቤተሰብ አባላት ፈፀሙት የተባለው ድርጊት የዳኛውን ክብር የሚነካ ነው።
ችሎት መዳፈር በመርህ ደረጃ በችሎት ላይ ተሰይሞ የተቀመጠን ዳኛ ወይም በችሎት ውስጥ የሚደረግ የሥነ ሥርዓት ጥሰት ነው። ይህም ማለት የሚከበረው ችሎት ላይ የሚሰየሙት ዳኞች የሚያደርጉት ካባ ነው። ነገር ግን በግቢው ውስጥ ሁከት ተፈጽሟል ከተባለ የዕውነት ግለሰቦቹ ጥፋቱን ፈፅመዋል ወይንም አልፈፀሙም የሚለውን ጥያቄ ለሕሊናቸው በመተው ከሕጉ አንፃር ግን ችሎት መዳፈር አይደለም ሲሉ ይገልፃሉ።
ችሎቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በግቢው ውስጥ እነዚህ ግለሰቦች በተወሰነባቸው ውሳኔ ስሜታዊ ሆነው ሊናገሩ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ዳኛውን ይሁን አልያም ሌላን አካል ሳያረጋግጡ ይህን መሰል ቅጣት ማሳረፍ ተገቢ አልነበረም። ዳኛውም በግለሰብ ስብዕናቸውና በዳኝነት ስብዕናቸው የተለያዩ ናቸው በማለትም ለዚህ የሚሆን ማሳያ ምሳሌን ይሰጣሉ። ለአብነትም ዳኛው በሕዝብ መገልገያ ትራንስፖርት ውስጥ ወይንም መዝናኛ ስፍራ ከሰዎች ጋር አለመግባባት ቢፈጥሩ ችሎት መድፈር በሚል ሕጋዊ ቅጣት ሊወሰን ነውን? ሲሉም ይሞግታሉ። ለግለሰቡ ሳይሆን ክብር የሚሰጠው ለሥርዓቱና ለተቋሙም ነው ይላሉ።
ፍትሕ አገኛለሁ ብሎ የሄደ አካል ላይ ይህን ያክል በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ሲፈረድ የሕይወት ጉዳይ በመሆኑ ስሜት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። በመሆኑም ዳኛው ይህን ተገንዝበውና ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ ከትተው ሰምተው እንዳልሰሙም ሊያልፉ ይገባ ነበር። በመሆኑም ቅጣቱ በግለሰብ ስሜት የተወሰነ እንጂ ሕግን መሠረት ያላደረገ ተገቢነት የጎደለው ነው ሲሉም ይተቹታል። እንደ አጠቃላይ ጉዳዩም በዚህ ደረጃ ከሚወሰን በሰበር ችሎት ላይ ሐሳብ ልዩነታቸውን ባሰቀመጡት ዳኛ ምክረ ሐሳብ መሠረት ወደ ስር ፍርድ ቤት ሊመለስና ሊታይ ይገባው ነበር ሲሉ በችሎቱ ላይ ልዩነት የነበራቸውን ዳኛ ይጋራሉ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 3/2011
ፍዮሪ ተወልደ