ስልጠናው ሴቶች በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሚኖራቸውን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል

አዲስ አበባ፡- ስልጠናው ሴቶች በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሚኖራቸውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ መሆኑ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ። በቴክኖሎጂ ዙሪያ ለሚሠሩ ከመላው ሀገሪቱ ለተወጣጡ ሴቶች የስታርአፕ ፋውንደርስ ስልጠና መስጠት በትናንትናው እለት ተጀምሯል።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ የሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ እንደገለጹት ፤ መንግሥት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ማጎልበትና ማሳደግ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

ሴቶች ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በስልጠና ራሳቸውን እንዲያበቁ፣ በዘርፉ መንግሥት የሚያቀርባቸውን ድጋፎች ተጠቅመው በተሰማሩበት ዘርፍ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሥራዎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚተገበሩ ሥራዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል።

አቶ ሰለሞን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመደበኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራው ከሚያከናውናቸው ተግባራት ጎን ለጎን ከተለያዩ አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ትኩረታቸውን በሴቶች ላይ ያደረጉ ፕሮጀክቶችንም ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል አሁን እየተሰጠ ያለው ስልጠና አንዱ ሲሆን፤ ስልጠናው በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሴቶች ያላቸውን ውሱን ተሳትፎ በማጎልበት በዘርፉ ሴቶች የላቀ ተወዳዳሪነትን እንዲላበሱ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በስልጠናው 74 ሴቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ስልጠናው የቢዝነስና የኢንተርፕሪነር ክህሎታቸውን የሚያሳድግ መሆኑን አብራርተዋል። በዚህ ስልጠና ወቅትም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ አስር ሰልጣኞች የአንድ መቶ ሺ ብር ሽልማትና በቀጣይም ሥራቸውን ለማስፋፋት የሚያስችል ተጨማሪ የፋይናንስና የክትትል ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻች ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ስልጠናው ሃሳብን ይበልጥ ለማሳደግ፣ ራስንና ሀገርን ለመለወጥ የሚኖርን ተነሳሽነት ለማሳደግ አላማ ያደረገ መሆኑና ለ10 ቀናት የሚቆይ መሆኑን ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፈጠራ ሥራዎች ስነ ምህዳር ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዓለም በቴክኖሎጂ ወደሚመራ ኢኮኖሚ እየተዘዋወረች ነው ያሉት ዶ/ር በይሳ፤ ኢትዮጵያም በቴክኖሎጂና በፈጠራ የተመራ ኢኮኖሚ እንዲኖር በዚህ ዘርፍ ላይ ፍላጎት ላላቸው ወጣቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You