የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ንግድ እንቅስቃሴ በየዓመቱ እድገት እያሳየ ነው

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ንግድ እንቅስቃሴ በየዓመቱ እድገት እያሳየ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ። በፈረንጆቹ የ2023 የሎጂስቲክስ ዘርፍ አፈጻጸም የእውቅና መድረክ “ሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ለዘላቂ እድገትና ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት ተካሂዷል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ንግድ እንቅስቃሴ በየዓመቱ እድገት እያሳየ ነው። በሎጂስቲክስ ዘርፍም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። በዚህም ኢትዮጵያን በሎጂስቲክስ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከነበረችበት 113ኛ ደረጃ ወደ 66ኛ ደረጃ ማድረስ ተችሏል።

ከስድስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ባለሙያዎችን በዓለም አቀፍ መርከቦች ማስቀጠር የተቻለ ሲሆን፤ ከ39 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን ተናግረዋል።

የመርከቦችን አማካይ የወደብ ቆይታ ከነበረበት ከ20 እና 30 ቀናት ወደ 12 ቀናት ዝቅ ማድረግ መቻሉን አውስተው፤ አሁን ላይ የሎጂስቲክስ ዘርፉ አፈጻጸም ኢንዴክስ ከነበረበት 2 ነጥብ 53 ወደ 2 ነጥብ 94 ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

የሎጂስቲክስ መዘመን ለኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመው፤ በዘርፉ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ መስጠት፣ የሎጂስቲክስ ሥርዓቱን ማዘመን እንዲሁም ያሉ ጸጋዎችን በተቀናጀ አግባብ መጠቀም እንደሚገባም ተናግረዋል።

በዓለም ባንክ መመዘኛ መስፈርት መሠረት በፈረንጆቹ 2023 የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ደረጃ በገለልተኛ አካል ተፈትሾ መሻሻሎች ማሳየቱን አውስተው፤ ኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ የሎጂስቲክስ ዘርፍ አጠቃላይ ፖሊሲና ስትራቴጂ ተነድፎ በትግበራ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከተቋማት አደረጃጀት ጀምሮ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሻሻል፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግና የመሳሰሉ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ገልጸዋል።

የሎጂስቲክስ ዘርፍ ቀልጣፋ አፈጻጸም የዓለም አቀፍ ንግድ ተወዳዳሪነት ከማጎልበት ባለፈ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

ሪፖርቱ በሁሉም መስፈርቶች መሻሻሎች ያሉ መሆኑን ያሳየ ነው ያሉት አቶ ደንጌ፤ በቀሩት ዓመታት የታቀደውን የሪፎርም እቅድ ማሳካት እንደሚቻል አስረድተዋል።

ከ90 በመቶ በላይ የጅቡቲ ኮሪደር መንገድ ብልሽት፤ በቀይ ባህር አካባቢ ያለመረጋጋት መፍጠር፤ በሩስያ- ዩክሬን ጦርነት በዘርፉ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ሁኔታን በመፈተሽ፣ ተግዳሮቶችን በመለየት እና መፍትሔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች የተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2016 ዓ.ም የገቢና ወጪ ንግድ እቃ እንቅስቃሴ ከ15 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ መድረሱን ገልጸዋል።

የመልቲሞዳል ትራንስፖርት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት በመደረጉ የገቢ ዕቃዎች ሽፋን ወደ 61 በመቶ ማድረስ መቻሉን አመላክተዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You