አዲስ አበባ፡- ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ5ተኛ ጊዜ የሚካሄደው የሳይበር ደህንነት ወር በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ በማተኮር የሚካሄድ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።
5ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር “የቁልፍ መሠረተ-ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትእግስት ሀሚድ እንደገለጹት፤ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ለ5ተኛ ጊዜ የሚካሄደው የሳይበር ደህንነት ወር በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ በማተኮር ይካሄዳል።
በዚህም ቁልፍ መሠረተ ልማት የሳይበር ደህንነታቸውን ማስጠበቅ ለሀገር ሉአላዊነት ያለውን አንድምታ የሚዳስስ እና የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ከመቀነስ አንጻር በስፋት የሚሠራ መሆኑን አንስተው፤ ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሆነ ቅንጅት በመፍጠር የሀገሪቱን የሳይበር ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሠረት የሚጣልበት መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የዜጎች እንዲሁም የተቋማት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ከማደጉ ጋር ተያይዞ በዜጎች፣ በተቋማት እና ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ከጥቅምት አንድ ጀምሮ የሚከበረው የሳይበር ደህንነት ወር በሚከናወኑ መርሀ ግብሮች የተቋማትን እና የማህበረሰብን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና በማጎልበት ለሳይበር ደህንነት ትኩረት እንዲሰጡና እራሳቸውን ከሳይበር ጥቃት መከላከል እንዲችሉ ያስችላል ብለዋል።
በሳይበር ደህንነት ወር ባሉት ሳምንታትም በሳይበር ደህንነት ፖሊሲ፣ የኮደርስ ኢንሼቲቭ ለሳይበር ደህንነት ሚና፣ በስማርት ሲቲ ጉዞ ላይ የሳይበር ደህንነትና የዲጂታል መታወቂያ ሚና ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
ወይዘሮ ትእግስት እንደገለጹት፤ በዓለም ላይ ከተዘረዘሩ ስጋቶች ውስጥ ከአየር ብክለት፣ ሀሰተኛ መረጃ፣ አክራሪነት እና የኑሮ ውድነት በመቀጠል የሳይበር ደህንነት የሚገኝ ሲሆን በ2022 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ8 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ ያዳረገ ዘርፍ ነው።
በ2027 ጥቃቱ በ282 በመቶ በማደግ ወደ 23 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደሚፈጥር የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁም ጠቅሰው፤ በመሆኑም የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ለመቀነስ ንቃተ ህሊና በማሳደግ መከላከል ይገባል ብለዋል።
በተቋሙ ባለፋት አራት ዓመታት የሳይበር ደህንነት ወሮችን በማዘጋጀት የንቅናቄ ሥራዎች የተሠሩ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም ለሳይበር ደህንነት ትኩረት እንዲሰጡ ንቃተ ህሊናን የመገንባት ሥራን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
የኢንፎርሜሽን ደህንነት ማረጋገጥ ሥራ ለአንድ ተቋም የሚተው ጉዳይ ባለመሆኑ በተለይም ሀገር በቀል የሆኑ እና የኢንዱስትሪ ደህንነት ተቋማት፣ የመንግሥት እና የግል ተቋማት፣ እንዲሁም ህብረተሰቡ ኃላፊነት በመውሰድ ሊቃጡ የሚችሉ ጥቃቶችን መከላከል እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
ተቋማት የሳይበር ደህንነት የማረጋገጥ ሥራ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን በመረዳት የሠራተኞቻቸውን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ ወሩን እንዲያከብሩ የሚጠበቅ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም