መጽሔቱ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሻለ ተግባር ላከናወኑ ተቋማት ዕውቅና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፡- የናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔት 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሻለ ተግባር ላከናወኑ ተቋማት ዕውቅና ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ።

ናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔት ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የመጀመሪያውን የናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔት አዋርድ ሊያካሂድ መሆኑን አስታውቋል።

የናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔት መስራች አቶ ኤሌያስ አድማሱ ጋዜጣዊ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሻለ ተግባር ላከናወኑና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲጎለብት ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት ዕውቅና ይሰጣል።

ናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔት ካለፉት 20 ዓመታት በላይ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲያድግና በዘርፉ ያሉ ችግሮች እንዲቀረፉ እንዲሁም በመረጃው ዘርፍ ግንዛቤ ሲያስጨብጥ ቆይቷል ያሉት አቶ ኤሊያስ፤ የዕውቅና መርሃ-ግብሩ ዘርፉ የበለጠ እንዲያድግ እና ተወዳዳሪነቱ እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል።

እንደ አቶ ኤልያስ ገለጻ፤ የመጀመሪያው አዋርድ በምርጥ ተቋራጭነት ከተመረጡ 42 ተወዳዳሪ ተቋማት ውስጥ ሰባቱ የሚሸለሙ ይሆናል። የምስጋና፣ የእውቅና እና የሽልማት መርሃ ግብሩ ናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔት፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር በጋራ የተዘጋጀ ነው።

በተጨማሪም በዘርፉ ምርጥ ሃሳብ አፍላቂዎች፣ ምርጥ አሰሪዎች፣ ምርጥ ቴክኖሎጂ አላማጆች ለውድድሩ መስፈርት ከማድረግ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምዘናን መሠረት ያደረገም መሆኑን አስረድተዋል።

መጽሔቱ በጀመረበት ጊዜ በሀገሪቱ የነበረው ጦርነት ዘርፉን ያዳከመው ቢሆንም በአጭር ጊዜ ዘርፉ እንዲነቃቃ፣ ከውጭ ብድሮች እንዲለቀቁ፣ የእውቀትና የልምድ ልውውጥ እንዲደረግ ማስቻሉንም ነው አቶ ኤልያስ የጠቆሙት።

አቶ ኤሊያስ አክለውም፤ መጽሔቱ በዘርፉ የመረጃ ክፍተትን በመሙላት እና ጥራት ያለው ሥራ እንዲሠራ በማድረግ እንዲሁም የሙያ ደህንነት እንዲረጋገጥ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

የናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔት ዋና አዘጋጅ አቶ አጥናፉ አለማየሁ በበኩላቸው፤ ሽልማቱ መዘጋጀቱ ከሚኖሩት በርካታ ጠቀሜታዎች ጎን ለጎን በዘርፉ አዳዲስ እይታዎችና ውድድሮች እንዲፈጠሩ ያግዛል ብለዋል።

አቶ አጥናፉ፤ የናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔት በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ከ20 ዓመታት በላይ የሚዲያ ኃላፊነቱን ከመወጣት በላይ በዘርፉ ለጥናት ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን በማቅረብ እያገለገለ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲያድግና የተሻለ ውጤት እንዲገኝ የተለያዩ እቅዶች ነድፎ እየሠራ ይገኛል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You