አዲስ አበባ፡- አፍሪካን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አብዮት ቀዳሚ አህጉር ለማድረግ በትብብር መሥራት ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
3ኛው ፓን አፍሪካን ኤአይ 2024 “አፍሪካን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማላቅ” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት፤ አፍሪካ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አብዮት ግንባር ቀደም አህጉር ለማድረግ በትብብር መሥራት ይጠበቅብናል።
አፍሪካውያን በቴክኖሎጂ አቅምና አጠቃቀማችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንድንችል ሀገር በቀል እውቀቶችንና አህጉራዊ አቅሞችን አሟጦ መጠቀም እንዲሁም በቴክኖሎጂ የሰለጠነ ትውልድ ማፍራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የአፍሪካን ችግሮች ለመፍታት፣ የማህበረሰቡን ኑሮ ለማቃለል፣ ለኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለግብርና፣ ለጤና እና ለሌሎች ዘርፎች የሚያበረክተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በአግባቡ መረዳት እንደሚገባም ተናግረዋል።
አፍሪካ በ2030 ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች ተብሎ ይታመናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ከግብ ለማድረስ አፍሪካዊያን በትብብር መሥራት ይኖርብናል ሲሉ አመላክተዋል።
እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የአፍሪካን የለውጥ ምዕራፍ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መደገፍ የምንችልበት ጊዜ አሁን ነው። ይህን ግብ ለማሳካትም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አቅምና አጠቃቀም ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው 3ተኛው ዙር ፓን አፍሪካን ኤ.አይ 2024 ኮንፈረንስ በግብርና፣ በጤና፣ በሕዝብ አገልግሎቶች፣ በቴክኖሎጂ፣ በሳይበር ደህንነት እና በሌሎች ዘርፎች የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
በተጨማሪም ሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች ልምድና ተሞክሮን ለመለዋወጥ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እና የአህጉሪቱን እድገትና ልማት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የመረጃ አያያዝ ቴክኖሎጂን ማሳደግ፣ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት፣ የማሽን ቋንቋ ያልሆኑ ሀገረኛ ቋንቋዎችን ማሽን እንዲያውቃቸው የማድረግ እንዲሁም የግብርናውን ዘርፍ ችግሮች ከመፍታት አንጻር በርካታ ሥራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የአፍሪካን እድገት እውን ለማድረግ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አቅምና አጠቃቀምን ማሳደግ ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ትኩረት በመስጠት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ካደጉ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ እያደረገች ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ከተሠሩት ሥራዎችም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መቋቋም፣ አምስት ሚሊዮን “ኮደሮች” ይፋ መሆን፣ በፖሊሲ የታገዘ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስትራቴጂ መጽደቅ እና ሌሎች በርካታ ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው ሲሉ አስታውቀዋል።
በዘርፉ ክህሎት ያላቸውን ሙያተኞች ለማፍራት ተከታታይ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለጤና፣ ለግብርና እና ለሌሎችም ዘርፎች ጥቅም ላይ ማዋል መጀመሯን ገልጸው፤ ዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ፣ ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ እና ለቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ትልቅ ሚና የሚጫወት በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አብራርተዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም