አዲስ አበባ:- ቡና ለብልጽግና ጉዟችን ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ዳይሬክተሩ “ቡናችን ለብልጽግናችን” በሚል መሪ ቃል ባለፈው ዓመት በዘርፉ ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አካላት ባለስልጣኑ የእውቅና መድረክ ማዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች ውስጥ ቡና በአማካይ ከ25 እስከ 35 ከመቶ የሚሸፍን መሆኑን ያነሱት አዱኛ (ዶ/ር) ምርቱ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ቀላል የማይባል የውጪ ምንዛሪን እያስገኘ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በቡና አምራችነቷ በዓለም በአምስተኛ ደረጃ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከሰባት እስከ አስር በመቶ የሚሆነውን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ትታወቃለች።
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ከመሆኗ እና ከምርቱ ተፈላጊነት አንጻር የተፈለገውን ያህል ለመጠቀም አልቻለችም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ግን የላቁ አፈጻጸሞች እየታዩ መምጣታቸውን አንስተዋል።
ቡና በሀገራችን ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት የመሪነት ሚና የሚጫወት ወሳኝ የግብርና ምርት ነው ያሉት አዱኛ (ዶ/ር) ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቀድና ለብልጽግና ጉዟችን መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው የተናገሩት።
ዳይሬክተሩ፣ መንግሥት ምርቱንና ምርታማነቱን በመጨመርና ጥራቱን በማሻሻል በዓለም ገበያ ተፎካካሪነታችንን የበለጠ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግሩን እውን ለማድረግ እንዲችል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ሀገራችን የቡናን ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ፍጹም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በባለፈው በጀት አመት 300ሺ ቶን ቡና ተልኮ 1ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱንም ገልጸዋል።
አያይዘውም ባለፈው ዓመት የድሃውን አርሶ አደር የዘመናት እንባ በማበስ ላይ የሚገኘው የባለልዩ ጣዕም ቡናዎች ውድድርም ተካሂዶ አንድ ኪሎ ግራም ቡና በ103 ሺህ ብር ተሸጦ ሪከርድ የተሰበረበት ዓመት በመሆኑ ከሌሎች ጊዜዎች እንደሚለየው አንስተዋል።
ይህም፣ የዘርፉን ተዋናይ እና ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያን ጭምር ያኮራ ተግባር እና የሁሉም የቡና ቤተሰቦች ድምር ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ የእውቅና አሰጣጡ ዋነኛ ዓላማ ለዚህ ስኬት እንድንበቃ ያስቻሉንን ጀግና አርሶ አደሮች፣ ላኪዎች እና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በሚገኙበት እውቅና መስጠት ነው።
በብሔራዊ ሳይንስ ሙዚየም መስከረም 30 ቀን 2017 በደማቅ ዝግጅት ለማካሄድ የታሰበው የእውቅና አሰጣጥ መድረክ ግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበር እና ሌሎችም አጋር ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በቅንጅት በመሥራት ላይ ሲሆኑ፤ በመድረኩ ከ1000 በላይ የሚሆኑ የቡና ቤተሰቦች እንደሚገኙ ይጠበቃል።
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም