አዲስ አበባ፡- በሊባኖስ የተፈጠረውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ በስፍራው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደኅንነታቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ትናንትና 51 ዜጎች ወደ ሀገራቸው ገብተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በሊባኖስ የተከሰተውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ ወደ ሀገራቸው ለገቡት ዜጎች በተደረገው አቀባበል ላይ እንደገለጹት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚያካሂደው የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት እየተከታተለ ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍትሔዎችን እያስቀመጠ ሲሠራ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በሊባኖስ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለችግር ተጋላጭ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩም ይህ ችግር እንደተሰማ በሚኒስትሩ የሚመራ ብሄራዊ ኮሚቴና አፋጣኝ የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በማከናወን ላይ ይገኛል። በዚህም በመጀመሪያው ዙር 51 ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ መቻሉን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
በአካል እና በዲጂታል የምዝገባ ሥርዓት ተዘርግቶ ዜጎች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ያሉት አምባሳደር ነቢያት፤ ዜጎች ሊባኖስ በሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤት አማካኝነት በፈለጉት አማራጭ ተመዝግበው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ አምባሳደር ነቢያት ገለጻ፤ ዜጎችን ለመመለስ እየተደረገ ባለው ጥረት የሚያስተባብር አመራር ወደ ሊባኖስ ተልኮ ሥራውን ጀምሯል። የመጡትንም ሆነ ገና የሚመጡ ዜጎችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማገናኘት የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል።
የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግሥት እያከናወነ በሚገኘው የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ተግባር በየትኛውም ሁኔታ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ በአትኩሮት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በመካከለኛ ምሥራቅ ከተከሰቱ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ተግባር እየተከናወነ ነው ያሉት አምባሳደር ሽፈራው፤ በሌሎችም ሀገራት በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የመታደግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ይህ ተግባር መንግሥት በሀገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጉዳይ የሚያሳስበውን ያህል በተለያዩ ሁኔታዎች ከሀገራቸው የወጡ ዜጎችም ሁኔታ እንደሚያሳስበው ማሳያ መሆኑን በመግለፅ፤ በቀጣይም መንግሥት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ዜጎች የክትትል እና ድጋፍ ሥራ እንደሚያከናውን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ በተጨማሪም በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም ከንግግር ያለፈ ምን እየተሠራ እንደሆነ ማመላከቻ ነው። በቀጣይም የሚኖረው ሁኔታ እየታየ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በሊባኖስ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጽህፈት ቤት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ጋር በመሆን በቅርበት የሚሠራ ይሆናል።
ተመላሽ ዜጎቹ በበኩላቸው፤ መንግሥት ወደ ሀገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ላደረገላቸው ትብብር አመስግነው፤ በተከሰተው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በአስከፊ ችግር ውስጥ እንደነበሩ ገልጸዋል።
ዜጎቹ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው እና የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለዜጎቹ አቀባበል አድርገዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም