በተያዘው በጀት ዓመት ብሔራዊ የግጭት መከላከል ስትራቴጂ በስፋት ተግባራዊ ይደረጋል

አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት በሰላም ግንባታ ዙሪያ የተጠናው ብሔራዊ የግጭት መከላከልና የሰላም ግንባታ ስትራቴጂ በስፋት እንደሚተገበር ተገለጸ።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስድስተኛ የፓርላማ ዘመን፣ አራተኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ትናንት ተካሂዷል።

የማንነት አስተዳደር ወሰን እና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የ2017 በጀት ዓመት እቅድ፤ በሰላም ግንባታ ዙሪያ የተጠናውን ብሔራዊ የግጭት መከላከልና የሰላም ግንባታ ስትራቴጂ በስፋት ወደ ተግባር በማስገባት ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለመገንባትና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ስር እንዲሰድ ይሠራል ብሏል።

የቋሚ ኮሚቴው ጸሐፊ አቶ ፍቅሬ አማን እንደገለጹት፤ በሀገር ደረጃ በጥልቀት ቢሠራ የሰላምና መረጋጋት ችግርን ሊፈታ የሚችል፤ እንደ ሀገር የተጠና ብሄራዊ የግጭት መከላከልና የሰላም ግንባታ ስትራቴጂ ጸድቆ በየክልሎች የደረሰ ሲሆን፤ ከዚህ ዓመት ጀምሮ በተግባራዊ እንቅስቃሴ ወደ ሥራ ይገባል። ይህም በሀገሪቱ የሚታዩ የሰላም ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ይታሰባል።

የወሰንና የማንነት ጥያቄን በተመለከተ በአንድ ጊዜ እልባት የሚያገኝ ጉዳይ አይደለም ያሉት አቶ ፍቅሬ፤ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን፤ በዚህ ዓመት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የማንነት መገለጫ የሆነ “ፕሮፋይል” ጥናት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለማካሄድ መታሰቡንም ገልጸዋል።

የአስተዳደር ወሰን ይገባኛል ጥያቄን የሕዝቦችን ወንድማማችነት በሚያጠናክርና ዘላቂ ሰላምን ሊያሰፍን በሚችል መልኩ እልባት ለመስጠት እንደሚሠራ በእቅዱ ተመላክቷል።

የወልቃይት፣ ራያና ጠለምት ጥያቄዎችን ለመመለስ በቅድሚያ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ሥራ መሠራቱን በማረጋገጥ፤ በቀጣይ ከአካባቢው መስተዳድርና ነዋሪዎች ጋር ውይይት በማካሄድ በአካባቢው ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ መተማመን የመፍጠር፤ ተፈላጊ መረጃዎችን የማጥራት ሥራ ከተሠራ በኋላም የሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ በምክር ቤቱ በኩል ትዕዛዝ እንዲሰጥ ሪፖርት የማቅረብ፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሳኔውን አፈጻጸም በየጊዜው ለምክር ቤቱ እያቀረበ እንዲያስገመግም የማድረግ ሥራዎች በበጀት ዓመቱ እንደሚከናወኑ በእቅዱ ላይ ተገልጿል።

ከዚህም ባሻገር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርበው ውሳኔ ያገኙ ነገር ግን በውሳኔው መሰረት እስካሁን ያልተተገበሩ ጥያቄዎችም እልባት ያገኛሉ ተብሏል። ይህ ሁሉ ሲተገበር የሕዝቦችን ወንድማማችነት በሚያጠናክርና ዘላቂ ሰላምን ሊያሰፍን በሚችል መልኩ እንደሆነ ተገልጿል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንደገለጹት፤ የወሰን ይገባኛል ጥያቄን ተፈናቀዮችን ከመመለስ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ተግባራዊ ተደርገዋል። የማንነት ጥያቄዎች ላይም ጥናቶች ተጠንተዋል። አንዳንዱን ሥራ ለማከናወን እንቅፋቶች ቢያጋጥሙም ምክር ቤቱ ጥብቅ ክትትል እየደረገ ይገኛል። ጥያቄዎችን ለመመለስ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል።

ምክር ቤቱ በትናንቱ ስብሰባው የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ፤ የመንግሥታት ግንኙነት የዴሞክራሲ አንድነትና የሕገ መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ፣ የማንነት አስተዳደር ወሰን እና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ፣ የሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል፣ የሕገ መንግሥት ትርጉምና ውሳኔ አፈጻጸም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት በማድረግ አጽድቋል። በተጨማሪም ከሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የሕገ መንግሥት ትርጉም በሚያስፈልጋቸውና በማያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሃሳብ ምርምሮ አጽድቋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You