አዲስ ዘመን ድሮ

ልክ እንደምን ጊዜውም፣ አምዱን በመሰለና እሱኑ በወከለ አቀራረብ መጥተናል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለይ በ1950ዎቹ፣ በተለይ በተለይ በ1952 ዓ•ም ምን ምን ለየት ያሉ ጉዳዮችን አስተናግዶ እንደ ነበር መለስ ብለን በመቃኘት ለዛሬው የሚከተሉትን ያቀረብን ሲሆን፤ ለሚቀጥለውም ቅኝታችንን በዚሁ አካባቢ ላይ በማድረግ “ለየት ያሉ” ያልናቸውን ይዘን እንቀርባለን።

ሰካራም ምን ይመስላል?

ሰካራም የሀጢያትን በትር ድጋፍ በማድረግ ክብርን በውርደት፤ ትህትናን በድፍርት በመለወጥ ለነፍሱ ወጥመድ የሚያሰናዳ የሰይጣን ፍፁም አገልጋይ ነው።

ከመጽሐፍም በምሳሌ የተፃፈውን ብናስተውል እንዲህ ይላል ወደ መጠጥ አትመልከት፣ መልኩ ባንፀባረቀ ጊዜ እየጣፈጠ ይገባል። ከጠጡትም በኋላ እንደ እባብ ነድፎ መርዙን ያፈሳል፤ አይኖችህም አመንዝሮችን ያያሉ፤ ልብህም ጠማማ ነገርን ይናገራል፤ በባህርም ውስጥ እንደተኛ አሳ ትሆናለህ።

እንዲሁም ስካር የተፈጥሮ መልክን (ውበትን) በመደምሰስ ልዩ ልዩ በሽታን ከመፍጠሩም በላይ የሰውን ጠባይ ወደ አውሬነት የሚለውጥ ጠንቀኛ በሽታ ነው። ለዚህ ምሳሌ ይሆነን ዘንድ የጥንቱን ተረት በማስታወስ ሰካራም በምን እንደሚመሰል ልንገነዘበው እንችላለን።

ኖህ ወይን በሚተክልበት ጊዜ ሰይጣን እንደ ቅን ሰራተኛ ጠጋ በማለት ምን እንደሚሰራ ጠየቀው። ኖህም ወይን መትከሉንና በፍሬው ምን አይነት መጠጥ እንደሚያዘጋጅ ከነገረው በኋላ፤ ሰይጣን እርዳታውን እንደሚያበረክትለት ጠየቀው። ያኛውም በስራው እንዲያግዘው ፍቃደኛ ስለነበር ጥያቄውን ተቀበለው።

ወዲያውኑም ሰይጣን የበግ ግልገል አመጣና በደሙ የወይኑን እግር አላሰው። ቀጥሎም አንበሳን፣ ዝንጀሮንና አሳማን አምጥቶ በተራ እያረደ ደማቸውን ከወይኑ ስር ላይ አፈሰሰበት።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንድ ሰው ትንሽ ሲጠጣ እንደ በግ ግልገል የለሰለሰ ይሆናል። የደጋገመ እንደ ሆነ ስሮቹ በመወጣጠር ሲግሉ ሰውነቱን በኃይል በሞቀው ጊዜ እንደ አንበሳ ጎበዝና ደፋር ይሆናል። ከመጠንም በላይ ሲወስድ የሚያደርገውን አያውቅምና እየተንበላጠጠ ሲወራጭ ከዝንጀሮ ጋር ልናወዳድረው እንችላለን።

በዚያም ሰአት ከመጠጣት ያልታገደ እንደ ሆነ በጭቃ ውስጥ እንደሚንከባለል አሳማ ይሆናል ማለት ነው።

ስለዚህ ሰው አልፎ ተርፎ ዝንጀሮንና አሳማን ለመምሰል ለምን ይፈልጋል?

ንጉሴ ቢተውልኝ

(አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ታህሳስ 23 ቀን 1952 ዓ•ም)

የሮሌክስ ሰአት ታደርጋለህን?

ኢታዋ፣ ሮሌክስ የሚባለው ሰአት ሬዲዮ አክቲቪቲ አለው ተብሎ ስለሚጠረጠር የሚያደርጉት ሰዎች ሁሉ ለካምፓኒው እንዲመልሱለት የአሜሪካን መንግሥት የሳይንቲስቶች ኮሚቴ ተናግሯል።

እስከ 150 የሚደርሱ የኮሚቴው አባሎች ይህ አይነት ሰአት ያደርጉ ይሆናል። በአሜሪካ አገር ያሉት የዚህ አይነት ሰአቶች “እስትሮንቲየም ዘጠና” የሚባለው ሬዲዮ አክቲቭ እንዳላቸውና እነዚህን ሰአቶች የሚያደርጉ ሰዎች ከጊዜ ብዛት ለጤንነታቸው የሚያስፈራ መሆኑን ኮሚቴው ተናግሯል።

(አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ታህሳስ 23 ቀን 1952 ዓ•ም)

“ከቶ መጽሐፍ አላነበባችሁምን?”

በአሁኑ ክፍለ ዘመን አንድ ባንድ ሲፈፀም የሚታየው፣ ቀድሞ በነቢያትና በሀዋርያት ከቶውንም በወንጌል እንደማይቀር ሁኖ የተነገረው ቃል መሆኑን አመዛዛኞች ሳያስተውሉት አይቀሩም።

“አናጢዎች የናቋት ድንጊያ የማእዘን ራስ ሆነች። በአይናችንም ዘንድ ድንቅ ናት” እንዲህ የተባለውን “ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁንምን” ሲል መጽሐፍ ቀደም ብሎ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

የዚህንም ከፍተኛ ሃሳብ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት እንደየ አስተያየታቸው ተርጉመውታል። በየጊዜውም አዲስ አዲስ ነገር እየገጠማቸው በጥቅስነቱና ከሱ በሚገኝ አስተያየት ሲጠቀሙበት ይኖራሉ። በአሁኑም ዘመን የተገኘበት ፍሬ ነገር ባጭሩ እንደሚከተለው ነው።

ኮሎኒያሊስቶች የናቋትና ያጠቋት፣ መከራ ያሳዩዋት የነበረችው አፍሪካ የነፃነት የማእዘን ራስ ለመሆን ከምትችልበት ደረጃ መድረሷ ሲታሰብ የመጽሐፉ ቃል መፈፀሙን ያስረዳል።

አንድ ጠቅላላ ውጤት ያለበት ቃል ሲነገር መፍትሄ ምስጢሩን፣ ዋና ዋና አስተያየቶችን የሚመለከት መሆኑን ይህ አገላለፅ ሊያስረዳ ይችላል።

(አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ታህሳስ 20 ቀን 1952 ዓ•ም)

ተማሮችን ተቀብሎ ማነጋገር

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ ታህሳስ 21 ቀን 1952 ዓ•ም ከቀኑ በአምስት ሰአት ተሩብ በገነተ ልኡል ቤተ መንግሥታቸው ከውጭ አገር ትምህርታቸውን ፈፅመው የተመለሱትን:-

ዶክተር ሥዩም ገብረ እግዚአብሄር

አቶ ካሳ ኃይሌ

አቶ ግደይ እስማኤል ባሕታ

ወይዘሪት ትሁን ኃይሌ ማርያም

አቶ ማሞ ወልደ ሰንበት

የተባሉትን ወጣቶች በአቶ ዘውዴ ገብረ መድህን በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክተር አቅራቢነት ተቀብለው እጅ አስነስተዋቸዋል።

በዚህም ጊዜ ግርማዊ ንጉሰ ነገሥት እያንዳንዱን ወጣት ስለ ተማረው ትምህርት ከጠየቁ በኋላ ወጣቶቹ የትምህርታቸውን ፍሬ በስራ እንዲያሳዩ አባታዊ የሆነ ንጉሣዊ ምክር ሰጥተው ወጣቶቹ እጅ እየነሱ ተመልሰዋል።

ከዚህም በቀር ሀጎስ ገብረ ኢየሱስ የተባለ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪ ስለ ትምህርት አሰጣጥ ጥናት ለማድረግ ወደ ውጭ አገር ስለሚሄድ በዚሁ ሰአት ከግርማዊ ንጉሰ ነገሥት ፊት ቀርቦ ተሰናብቷል። (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ታህሳስ 22 ቀን 1952 ዓ•ም)

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You