ከተማ አስተዳደሩ በ12ኛ ክፍል ከ500 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና ሰጠ

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2016 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና ከ500 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ 484 ተማሪዎች እውቅና ሰጠ። ውጤቱ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተፈጠረውን ስብራት ለመጠገን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ያለው ሥራ ፍሬ ማፍራት እንደሚያሳይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

በ2016 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሀገር አቀፍ ፈተና 500 እና ከዚያ በላይ የሆነ ውጤት ላስመዘገቡ 484 የከተማዋ ተማሪዎች እንዲሁም ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ላሳለፉ የከተማዋ ትምህርት ቤቶች እውቅናና ሽልማት በትናትናው እለት ተበርክቷል።

በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግር፤ ባለፉት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ውጤት በአስደንጋጭ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን አንስተው፤ መንግሥት በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተፈጠረውን ስብራት ለመጠገን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ያለው ሥራ ፍሬ አፍርቷል ብለዋል።

በዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የተገኘው ውጤት ባጋጣሚ የመጣ ሳይሆን በብዙ ልፋትና ትጋት የተገኘ መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ፤ ውጤቱ ከተማዋንም ሆነ ሀገራችንን ያኮራ መሆኑን ገልጸዋል።

ያለንበት ወቅት ለወጣቱ እድልም፤ ተግዳሮትም ያለበት ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ተግዳሮትን አሸንፈው እና ያለውን መልካም እድል ተጠቅመው ስኬታማ የሆኑ ናቸው ብለዋል።

የእውቅና መርሀ ግብሩ በታችኛው የትምህርት እርከን ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን ተነሳሽነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ ከተማ አስተዳደሩም ለትምህርት ሴክተሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

ከንቲባዋ፤ በዘንድሮ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ፈተና የተመዘገበው ውጤት የትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተስፋ እንዳለ ያሳየ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ከንቲባዋ በከተማዋ ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላደረጉ ወላጆች፣ መምህራንና ትምህርት ቤቶች ምስጋና አቅርበው፤ ከተማ አስተዳደሩ ከአንድ እስከ ሦስት ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች ነጻ የውጭ ሀገር የትምህርት እድል (ስኮላርሺፕ) እንዳመቻቸ አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ በ2016 ዓ.ም 21 ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸው፤ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ5 በመቶ እድገት መመዝገቡን ጠቁመዋል።

ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል ሴቶች አብላጫውን ቁጥር እንደሚይዙና ከትምህርት ቤቶች አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ በማሳለፍ እውቅናውን ማግኘታቸውን ገልጸው፤ የማታና የግል ተፈታኞች ላይ የውጤት ማሽቆልቆል ታይቷል ብለዋል።

በዚህ ዓመትም የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ በማቀድ አዲስ የትምህርት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሠራ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።

ዳግማዊት አበበ

 አዲስ ዘመን መስከረም 28/2017 ዓ.ም

Recommended For You