አዲስ አበባ:- የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ትናንት ባካሄዱት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ጉባኤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩትን አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አድርገው ሰየሙ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ጉባኤ በትናንት የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴን ፕሬዚዳንት አድርጎ ሰይሟል።
አምባሳደር ታዬ የተሰየሙት በአምስት ተአቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ ሲሆን፤ ቃለ መሃላም ፈጽመዋል። በእለቱም የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ለአዲሱ ተመራጭ ሕገ መንግሥቱን አስረክበዋል።
አዲሱ ተመራጭ የሁለቱ ምክር ቤቶች 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ መከፈቱን በማብሰር የፕሬዚዳንትነት ሹመታቸውን ሥራ ጀምረዋል። በምክር ቤቶቹ መክፈቻ ላይ የተነበበው ታሪካቸው እንደሚያስረዳው፤ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የተወለዱት በደባርቅ ሰሜን ጎንደር ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አግኝተዋል።
እንግሊዝ ከሚገኘው ላንክስተር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በስትራቴጂ ጥናት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በተለያዩ ሀገራት አጫጭር የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ፖለቲካል ሳይንስ ሥልጠናዎችን እና ኮርሶችን ወስደዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ መምሪያ የሥራ ክፍል ፣የምዕራብ አውሮፓ ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የኢንፎርሜሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር፣ ስቶክሆልም የኢፌዴሪ ኤምባሲ በአማካሪነት፣ በዋሽንግተን የኢፌዴሪ ኤምባሲ በአማካሪነት ማገልገላቸውም ተጠቅሷል።
አምባሳደር ታዬ፤ በሎስአንጀለስ ቆንስል ጀነራል፣ በ1998 ዓ.ም ደግሞ በባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ተሹመዋል። በሎስአንጀለስ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ማዕረግ የቆንስላ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ በአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል፣ በ2008 ዓ.ም ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሠርተዋል።
በግብፅ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር ሆነውም ሠርተዋል።
አምባሳደር ታዬ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመሾማቸው በፊትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2017 ዓ.ም