ዜና ሐተታ
በዓላት ጥላቻን በፍቅር፣ ቂምን በይቅርታ የመሻር ተፈጥሯዊ ኃይል አላቸው። የሰው ልጆች የእርስ በእርስ ግንኙነት ከማጠናከር አኳያም ፋይዳቸው እንዲሁ በገንዘብ የሚተመን አይደለም። ከዚህ ጎን ለጎንም የእውቀት፣ የጥበብ፣ የመደጋገፍ፣ የመቻቻል፣ የመተማመንና የሰብዓዊነት ምንጭ ናቸው።
ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ በዓላት እንዲሁም መልካም ልማዶችና እሴቶች ለሀገር ሉዓላዊነት ምሶሶ ናቸው። ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በዚህ ባለጸጋ ናቸው ቢባል ከእውነት የራቀ አይደለም። የብዝሃ ሃይማኖት፣ ለባህል፣ ማንነት፣ እሴት ወግና ልማድ ባለቤት ናቸው ለሚለው ምስክር አያሻውም።
ለአብነትም በወርሃ መስከረም የሚከበሩ በዓላት አዲስ ዓመት፣ ያሆዴ፣ መስቀል፣ ሄቦ፣ መሰላ፣ ጊፋታ፣ ማሽቃሮ፣ ኢሬቻ ወዘተ መጥቀስ ብቻ ለዚህ ማሳያዎች ናቸው።
ይሁን እንጂ ባህሎቻችን፣ ሃይማኖቶቻችን እንዲሁም መልካም ልማዶቻችን በአግባቡ ባለመረዳት አለፍ ሲልም ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› በሚል የተዛባ አመለካከት በርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሁከትና የብጥብጥ መናኸሪያ ከሆኑ ሰነባብቷል። የሰላም ዋጋ መተመን የሚቻለው ሰላም በጠፋ ጊዜ ብቻ ስለመሆኑ የገሃዱ ዓለም እውነት ነው።
ታዲያ ሰላምን ለማጽናት፣ አንድነትን ለማጠናከር፣ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከየበዓላቱ የሚነፍሱ ሰላማዊ ነፋሳት ማሽተትና ከትሩፋቱም መቋደስ የተሻለ ነው።
የተከፉትን የተገፉትን፣ ያለወላጅ፣ ያለጧሪ የቀሩትን፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ያለ ጥሪት የሚማስኑትን በእኩይ ተግባራቸው የህሊና እስረኛ የሆኑትን ለመታደግ ዛሬም አለመርፈዱን በሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ወቅት ለኢፕድ አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች ይገልጻሉ።
አራርሳ ሙታልኬስ ይባላሉ። የምዕራብ ሸዋ ደንዲ ወረዳ ጊንጪ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ለማክበር በአዲስ አበባ ተገኝተዋል።
በወቅቱ ለኢፕድ በሰጡት ቃል፤ኢሬቻ የሰላም ምልክት የአብሮነት አድማስ በመሆኑ በበዓሉ የታየውን አብሮነት በማጎልበት የሀገሪቱን ሰላም ለማጽናት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ይላሉ።
ኢትዮጵያ የብዝሃ ባህል፣ሃይማኖትና ማንነት መገለጫ በመሆኗ ለሁከትና ለብጥብጥ ከሚጋብዙ ልማዶች ይልቅ ሰላም የሚያጸኑ እልፍ አማራጮች አሏት የሚሉት አቶ አራርሳ፤ እነዚህም በመልካም ልማዶችና በበዓላት የሚገኙ የሰላም እሴቶች መጠቀም ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
ኢሬቻ እርቅ፣ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ምስጋና፣ ጸሎትና ተስፋ እንዲሁም በኢሬቻ የተጣላ ሳይታረቅ ወደ መልካ የማይሄድ በመሆኑ ኢሬቻን የሚያከብር ሁሉ ለሰላም እጁን መዘርጋት እንዳለበትም ያክላሉ።
እንደ አቶ አራርሳ ገለጻ፤በኢሬቻ ማንኛውም ሰው ከጥላቻ ነጻ በመሆን በንጹህ ልብ ወደ መልካው መቅረብ ይኖርበታል፤ይህም ወጣቱ በእለት ተዕለት ህይወቱ ተግባራዊ ሊያደርገው ይገባል። በተለይ በዓሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሁሉም ብሔሮች በጋራ እያከበሩት መሆኑ የበለጠ የሰላም ምንጭ እየሆነ መጥቷል።
በተጨማሪም ወጣቱ የቀደሙ የአባቶቹን ፈለግ በመከተልና በዓሉ የሚያዘውን ትውፊት በትክክል በመገንዘብ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ያሉ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ማስቆም እንደሚገባው ያስረዳሉ።
ኢሬቻ በገዳ ስርዓት የታቀፈ ነው የሚሉት አቶ አራርሳ፤ ኢሬቻ ከመምጣቱ አንድ ሳምንት በፊት የነበረው የእርቅና የይቅርታ ሳምንት ኢሬቻ ሰላም የሚሰብክ መሆኑን ማሳያ መሆኑንም ያብራራሉ።
በክልሉም አባገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ሰላምን ለማውረድ ተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረቡ ያሉ ሲሆን፤ ማንኛውም አካል ያለውን ቅሬታ በባህሉ መሰረት ፊት ለፊት ቀርቦ በመናገር ችግሩን መፍታት እንደሚገባውም ምክረ ሃሳባቸውን ይለግሳሉ።
ሌላኛው የበዓሉ ተሳታፊ አቶ ዋሚ ሙጣል በበኩላቸው፤ ኢሬቻ የሰላም ምንጭ ብቻ ሳይሆን የእኩልነትና የፍትህ ምልክት በመሆኑ ለሀገራዊ መግባባትና ለአብሮነት ሊውል እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
ኢሬቻ ከየትኛውም ብሔርና ሃይማኖት ጋር ተፋቅሮ በአብሮነት የሚከበር ነው የሚሉት አቶ ዋሚ፤በዓሉ ማንም አካል ለፖለቲካ አላማ ሊያውለው እንደማይገባ ይናገራሉ።
የኢሬቻ በዓል የሕዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስርና ለአንድነት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ወጣቱም ይህንን ባህላዊ ትውፊት በመገንዘብ ለሰላም ዘብ ሊያደርገው ይገባል የምትለው ደግሞ ወጣት ሲንቄ ታሲሳ ናት።
በዓሉን ለበርካታ ጊዜ በቢሾፍቱ እንዲሁም በአዲስ አበባ አክብራለሁ የምትለው ወጣት ሲንቄ፤ በዓሉ ለሰላምና ለአብሮነት ያለው እሴት ከፍተኛ መሆኑን ማስተዋሏን ትገልጻለች።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2017 ዓ.ም