“የኢትዮጵያን ወዳጆችና አጋሮች የማበራከት ተግባር በትኩረት ይከናወናል” ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያን ወዳጆችና አጋሮችን የማበራከት እና የማስፋፋት ተግባር በትኩረት ይከናወናል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ። በ2016 በጀት ዓመት የተመዘገበው ዕድገት እና ሀገራዊ ስኬት አመርቂ እና ይበልጥ ኃላፊነትን የሚሰጥ መሆኑ ተመላክቷል።

የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያሏትን ግንኙነቶች በማጠናከር ሀገራዊ ጥቅሞችን ለማሳደግ፣ በኢኮኖሚ፣ በቀጣናዊ ትስስርና በጋራ ጥቅሞች እንዲሁም በሰላምና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ ቆይቷል።

በጀት ዓመቱ የአፍሪካ እና የዓለም አቀፍ ትብብሮች እንዲጠናከር በትጋት የሚሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ወዳጆችንና አጋሮችን የማበርከት እና የማስፋፋት ተግባር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አመላክተዋል። በሁለትዮሽ ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን በማስጠበቅ ከቻይና ጋር ያለንን ግንኙነት በወቅቶች ወደማይለወጥ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ከፍ እንዲል መደረጉንም አስታውቀዋል።

ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ አቅም ካላቸው የባህረ ሰላጤው ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር መቻሉንም ጨምረው ገልጸዋል። በባለብዙ ወገን መድረኮች የኢትዮጵያ ተደማጭነት እና በጎ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሚና እንዲጎለብት ጉልህ የዲፕሎማሲ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው፤ ሀገሪቱ የብሪክስ ሙሉ አባል እንድትሆን የተከናወኑ ሥራዎች ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትሩፋቶች እንድታገኝ እና ሚዛናዊ ግንኙነቶችን ይበልጥ ለማዳበር እድል ፈጥሯል ብለዋል።

የሀገራችን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ መደበኛና ከፍ ወዳላ ደረጃ ለማሸጋገር ስትራቴጂያዊ ግንኙነቶችን የማጠናከር እና አዳዲስ ስትራቴጂያዊ አጋርነትን ከማፍራት አኳያ ውጤት ተገኝቷል ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አማራጭ ወደብና የባህር በር እንድታገኝ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን አስታውሰው፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ገጽታን ለማጠልሸት የተጀመረውን ዘመቻ እና አላስፈላጊ የዲፕሎማሲ ትኩሳት ለማርገብ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። ሀገራችን በአፍሪካ ቀንድ ያላትን የተደማጭነት አቅም በማስፋት በቀጣናው ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጉልህ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።

በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን በተለይ የሱዳን ግጭት እንዲፈታ በኢጋድና በአፍሪካ ህብረት በኩል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አውስተው፤ በሀገራችን አመራር ደረጃም የሱዳን ግጭት እንዲቆም ግልጽና ተከታታይነት ያለው የሰላም ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

በቀጣይም የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ እንዲሆን ሀገራችን ጉልህ ተሳትፎ ታደርጋለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለጋራ ልማትና እድገት በተጀመሩ ትብብሮች የሰጥቶ የመቀበል መርሕ ገቢራዊ እንዲሆኑ እንሠራለን ብለዋል።

በሌላ በኩል በ2016 በጀት ዓመት በጥቅሉ የተመዘገበው ዕድገት እና ሀገራዊ ስኬት በአንድ በኩል አመርቂ በሌላ በኩል የሚያስቆጭና ይበልጥ ኃላፊነትን የሚጥል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የተመዘገበው ዕድገት ሀገራችን በብዙ ፈተና ውስጥ ሆና የተመዘገበ በመሆኑ የውጤቱን ፋይዳ ከፍ ያደርገዋል ሲሉ አንስተዋል።

የሚያስቆጨው እና ይበልጥ ኃላፊነትን የሚጥለው ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ባይኖሩ ከዚህ በላይ ዕድገት ሊመዘገብ እንደሚችል ሲታሰብ መሆኑን ገልጸው፤ ሕዝቡን እየፈተኑት ያሉት የጸጥታ ስጋትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን እንዲሁም ኮንትሮባንድና ሕገወጥነት ካላቸው ስር የሰደደ ሁኔታና ዘርፈ ብዙ መገለጫዎች አንጻር በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ነቅለን የምንጥላቸው አይሆኑም ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመቀነስ እና የእድገታችን እንቅፋት እንዳይሆኑ በርትተን መሥራት ተግባራችን ይሆናል። በሂደትም ኢትዮጵያ ከሙስናና ከብልሹ አሠራር የጸዳች እንድትሆን በርትተን እንሠራለን ሲሉ አስረድተዋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙትን የፍትህ መዛባት እና የመብት ጥሰቶችን በአጭር ጊዜ ለመቋጨት የሽግግር ፍትህ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አመላክተዋል።

የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት ለማስቀጠል እና ብልጽግናን እውን ለማድረግ ቁልፍ መሳሪያ ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆም ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህ ደግሞ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ማስፈን እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቁልፍ ሥራዎች ይሆናሉ ሲሉ አብራርተዋል።

ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ኃይልን በብቸኝነት መጠቀም የመንግሥትና የመንግሥት ጸጥታ ተቋማት ብቻ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ ገልጸው፤ የተያዘው ዓመት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት አፈጻጸም የሚሻሻልበት ይሆናል። ለዚህም ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን መስከረም 28/2017 ዓ.ም

Recommended For You