በ2017 በጀት ዓመት ስምንት ነጥብ አራት በመቶ እድገት ለማስመዝገብ ጥረት ይደረጋል

  • የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ትኩረት ይሰጣል
  • አራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የሥራ ዕድል ይፈጠራል

አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት ስምንት ነጥብ አራት በመቶ እድገት ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚደረግ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ትኩረት እንደሚሰጥ እና ለአራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

ትናንት በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች  ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ፕሬዚዳንት ታዬ የሁለቱን ምክር ቤቶች በይፋ ከፍተው ሥራ አስጀምረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግርም በ2017 በጀት ዓመት ትኩረት የሚደረግባቸው ካሏቸው መካከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ዘርፍ መገንባት ቅድሚያ የሰጡት ነው።

ለትግበራውም የመስኖ ሜካናይዜሽን ሥራዎች እንዲጠናከሩ በማድረግ ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በተለይ የውጭ ምንዛሪና የብድር አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ተግባራዊ የተደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማነትን የማረጋገጥ ሥራ ትኩረት ከሚደረግባቸው አንዱ መሆኑን ፕሬዚዳንት ታዬ ጠቁመዋል።

በተለይም የኮንስትራክሽን ዘርፍን የማስተዳደር፣ የመምራት ጠንካራ ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል፣ ኢንቨስትመንት በሚያበረታታ መልኩ ከባቢን የማሻሻል ሥራ ይሠራልም ነው ያሉት።

እንደርሳቸው ገለጻ፤ በአገልግሎት ዘርፍ የሚታየውን ሰፊ የኢ-መደበኛነት ወደ መደበኛ ሥራ በማስገባት፣ በፋይናንሰ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የታየውን መነቃቃት በማስፋትና በማስቀጠል ብሎም ወደ ጠንካራ ዲጂታል ሥርዓት በማስገባት የ8 ነጥብ 4 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ጥረት ይደረጋል።

የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ ወደታክስ ሥርዓቱ ያልገቡትን በማስገባት፣ አዳዲስ የታክስ አይነቶችን ተግባራዊ በማድረግ፣ የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመንና ታክስ በመሰብሰብ፣ የሚወጣ ወጪን ውጤታማ በማድረግ፣ የታክስ ሥርዓቱንም ወደክልሎች በማውረድ የመንግሥት ገቢን አንድ ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ለማድረስ መታቀዱንም ጠቁመዋል።

ጥብቅ የፊሲካል ፖሊሲ በመተግበር፣ ምርትና ምርታማነትን በማጎልበት፣ በአቅርቦት በኩል ያሉትን ተግዳሮቶች በመፍታት አምራችና ተጠቃሚን የሚያገናኙ የገበያ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋትና የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ጥረት እንደሚደረግም አመልክተዋል።

አዳዲስ ወጪ ምርቶችን በማካተት እንዲሁም ተጨማሪ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋፋት፣ ምርቶችን በጥሬ ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ በመላክ፣ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ወደዘርፉ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ ለዘርፉ ተዋናዮች የሚሰጡ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማጠናከር ከሸቀጦች ወጪ ንግድ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ወሳኝ ሥራ እንደሚከናወንም ነው የገለጹት።

ዘንድሮ ለውጭ ባለሀብቶች ትርፋቸውን ከሀገር የማውጣት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ይሰጣል ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ለኢንቨስትመንታቸውም ዋስትናና ከለላ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል። የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በማሳደግም ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ ይሠራል ብለዋል።

ሰፊና ዘላቂ የሥራ እድል በመፍጠር በሀገር አቀፍ ደረጃ ሥራንና ሠራተኛን ባግባቡ በማስተሳሰር እንዲሁም ገበያው የሚፈልገውን ክህሎት የሚያሟሉ ሠራተኞችን በማቅረብ የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ አብራርተዋል።

አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማስፋፋት፣ ለወጣቶች ተግባር ተኮር ስልጠና በመስጠት እና ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ለማፍራት ይሠራል፣ በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትም ጥራትና ቁጥጥርን በማሳደግ ከብሄራዊ መታወቂያ ጋር ተሳስሮ እንዲሠራ ይደረጋል ነው ያሉት።

ትግበራዎቹም ዘንድሮ ለአራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ እንደሚደረግ እና ከዚህ ውስጥ 700 ሺህ የሚሆነው በውጭ ሀገር የሚፈጠር የሥራ ዕድል እንደሚሆንም አመልክተዋል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን መስከረም 28/2017 ዓ.ም

Recommended For You